የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና ጥቅምት 3 ቀን 2012ዓ.ም ይጀመራል፡፡

265

ባሕር ዳር፡ መስከረም 29/2012 ዓ/ም (አብመድ) ተገቢው እንክብካቤ ሳይደረግላቸው ዘመናትን ካስቆጠሩ የኢትዮጵያ ታሪካዊ የመስህብ ሀብቶች መካከል የጎንደሩ የፋሲል አብያተ መንግሥታት አንዱ ነው። የዚህ ቅርስ የጥገና ሂደቱ በችግሮች የታጠረ ሆኖ መቆየቱንም ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። የመምሪያው ኃላፊ አቶ አስቻለው እንደተናገሩትና እኛም በቦታው ተገኝተን እንደተመለከትነው ሕንጻዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ሕንጻዎች መሠረታዊ ጥገና ሳይደረግላቸው ከነጉዳታቸው ለረጅም ዓመታት መቆየታቸው ደግሞ የችግሩን መጠን ከፍ እንዲል አድርጎታል።

የፌዴራል መንግሥት በከተማዋ የሚገኙ ቅርሶችን በመጠገን በኩል የነበረው ተሳትፎ እና ድጋፍ ዝቅተኛ መሆኑንም መምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በቅርሶቹ ላይ የደረሰውን ከፍተኛ የጉዳት መጠን በትክክል በመረዳት ተገቢውን የሙያ እና የገንዘብ ድጋፍ አላደረገም። በቀጣይ የፌዴራል መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ መቅረቡንም ነው አቶ አቶ አስቻለው የገለጹት።

የአማራ ክልል መንግሥት እና የከተማ አስተዳደሩ ቅርሱ የተጋረጠበትን የመፍረስ አደጋ በመረዳት እና ልዩ ትኩረት በመስጠት በተወሰነ መልኩ ጥገና ማድረጋቸውን ተመለክተናል። ነገር ግን ከችግሩ አንጻር የተሠራው ጥገና በጣም ዝቅተኛ ነው። በሕንጻዎቹ ላይ በከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ጉዳቶች እና ሥጋቶች ቅርስ አደጋ ላይ መሆኑን አመላካች ናቸው።

ቅርሶቹ የከፋ ችግር ሳይደርስባቸው ጥገና ለማድረግ በተያዘው ዓመትም በከፍተኛ ደረጃ የጥገና ሥራ ለመሥራት ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን የከተማ አስተዳደሩ ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አስታውቀዋል። የክልሉ መንግሥትም ለጥገናው ድጋፍ መድረጉን ተናግረዋል። ከገብኝዎች ከሚገኘው ገቢ መካከል 70 በመቶ የሚሆነውን ለቅርስ ጥገናው አገልግሎት እንዲውል መወሰኑን አንዱ ማሳያ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኃላፊው እንደተረናገሩት ለጥገናው ወደ 36 ሚሊዮን ብር እንዲመድብ የአማራ ክልል ቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ተጠይቋል። ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም የነበረው ተሳትፎ አነሳ ቢሆንም ዘንድሮ በሚሠራው ጥገና ላይ ጥሩ ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ እንደሚታሰብም አቶ አስቻለው አመልክተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም በሙሀዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የሚመራ የፈረንሳይ መንግሥት የቅርስ ጥገና ቡድን ልኳል። ቡድኑም ጉዳት የደረሰባቸውን የቅርስ አካል ዓይተው የጉዳቱን መጠን ተረድተው ተመልሰዋል ነው ያሉት። ይህም በቀጣይ የተሻለ ሥራ ይኖራል ተብሎ በተስፋ እንዲጠበቅ አድርጓል።

ቅርሱ በዓለም የቅርስ መዝገብ ውስጥ የተካተተ እንደመሆኑ መጠን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለጥገናው ድጋፍ ለማድረግ እንዲያግዘው የድርጅቱ ተወካይ በ2012 ዓ.ም ወደ ጎንደር ከተማ አቅንተው የጉዳቱን መጠን ዓይተው መሄዳቸውንም አስታውቀዋል። በቀጣይም ዩኔስኮ ለቅርስ ጥገናው ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቅ የሚያስችል ዓውደ ርዕይ እንደሚዘጋጅ ነው የመምሪያ ኃላፊው የገለጹት።

የጎንደር ከተማ አስተዳድር ጥገናው በፍጥነት እንዲሠራ እየሠራ ይገኛል። ጉዳት የደረሰበትን የቅርስ ክፍል እየተከታተሉ የጥገና ሥራውን የሚያከናውኑ ሦስት መሐንዲሶችም መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። ከዚህ በፊት ለነበረው የኖራ አቅርቦት ችግርም መፍትሔ መገኘቱን እና ሦስት ቢያጆ ኖራ መቅረቡን ነው የገለጹት መምረያ ኃላፊው። ከፊታችን ሰኞ ጥቅምት 3/2012 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የጥገና ሥራው ተግባራዊ መሆን ይጀምራል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleበጎንደር አካባቢ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር የቱሪስት ፍሰቱ ላይ የጎላ ተፅዕኖ አለማሳደሩ ተገለጸ፡፡
Next articleየዚያ ዘመን ቅርሶች በዚህ ዘመን አይጠፉም!