የማትታጠፈው ኢትዮጵያ!

137

ባሕር ዳር: ጥር 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም የፍትህ አደባባይ ብቻዋን ቁማለች። በጥቁሮች የነጻነት ተጋድሎ አርአያ እና ምሳሌ ሆና ብቅ ብላለች። ፓን አፍሪካኒዝምን ለመመስረት ምሳሌዋ ሀገር ኢትዮጵያ ነበረች። ጥቁሮች በተገለሉበት እና ፍትህ በራቀበት የስፖርት ውድድር መድረክ ሳይቀር ኢትዮጵያ ለድምፅ አልባዎቹ ጭቁን የአፍሪካ ሀገራት ድምፅ ሆና አገልግላለች።

ያኔ ገና የጥቁር አፍሪካዊያን የነጻነት ትግል መሠረት ሳይዝ ብቅ ያሉ አፍሪካዊያን አብዮተኞች የምዕራቡ ዓለም ሀገራት የጉዞ እገዳ ሲጣልባቸው ምላሻቸው “ወደ ኢትዮጵያ እንዳንጓዝ ብትከለክሉን ነበር የሚቆጨን” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ እስከ ኔሰን ማንዴላ ለአብዮታዊ ትግላቸው ጉልበት ኢትዮጵያ ነበረች።

ኢትዮጰያ የአፍሪካዊያን ችግር በራሳቸው አፍሪካዊያን ምላሽ እና መፍትሔ ማግኘት ይኖርበታል የሚል የጸና አቋም አላት። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት ላይ ከድሮም ጀምሮ የማይናወጥ እና ወጥ እምነት ነበራት። ኢትዮጵያ የምትተማመንባቸውን ያክል በኢትዮጵያ ላይ የጠነከረ እምነት እና የልብ ፍቅር ያላቸው አፍሪካዊያን ሀገራትም ብዙ ናቸው።

የውስጥ ግጭታቸው እና የድንበር ውዝግባቸውን ኢትዮጵያ እንድታሸማግላቸው የሚጠይቁት ሀገራት ቀላል ቁጥር አልነበራቸውም። ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ሰላም አስከባሪዋን እንድታስገባላቸው እና ወታደራዊ ድጋፍ እንድታደርግላቸው ይጠይቁ የነበሩት ሀገራት ቁጥር ቀላል አይደለም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት የውስጥ እና የርስ በእርስ ግጭቶች የመፍትሔ አማራጭ ሆና ያልቀረበችበት ጊዜ ነበር ማለት ይከብዳል።

ከሞኖሮቢያ እስከ ካዛብላንካ የአፍሪካዊያንን ልዩነት ወርዳ የምታሸማግለው ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ዛሬም ከጁባ እስከ ካርቱም፣ ከትሪፖሊ እስከ ኪጋሊ፣ ከማሊ እስከ ሱማሊ ቀና ቀናውን በማሰብ እና በማሰባሰብ የአፍሪካዊያን የፍትሕ እና የሽምግልና አድባር ሆና እንደቀጠለች ናት።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ነጻነት ጥብቅና ስትቆም ውስጣዊ ሰላም እና መረጋጋት ባላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በፈተናዋም ወቅት ነበር። በየጊዜው ቅስም የሚሰብር እና አንገት የሚያስደፋ ውስጣዊ ፈተና የሚገጥማት ኢትዮጵያ በነዚያ ወቅቶች እንኳን ከአፍሪካዊ እሳቤዋ ሸብረክ የማትል እና የማትታጠፍ ሀገር መሆኗን ደግማ እና ደጋግማ አስመስክራለች።

ኢትዮጵያ በፈተና እና በውጣ ውረድ መካከልም ሆና እንዲመሠረት ትልቁን ድርሻ የወሰደችለት የስድስት አስርት ዓመታት የእድሜ ባለጸጋው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት ኢትዮጰያ ለአፍሪካ ሀገራት የነበራትን የጸና አቋም ያንጸባረቀ ገጸ በረከት ነው። የሕብረቱን መቀመጫ ከኢትዮጵያ ለመነጠል ግን ያልተሰራ ሴራ እና ሸፍጥ አልነበረም።

ገና በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የምስረታ ወቅት ጃንሆይ የሚመሯት ኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ ለድርጅቱ መቀመጫነት አትመጥንም ሲሉ ያጉረመረሙ ጥቂት ሀገራት ነበሩ። ዳሩ በንጉሱ ብስለት እና በሚኒስትሮቻቸው ብስለት አዲስ አበባ የሕብረቱን መቀመጫነት በጥረት አረጋገጠች።

በፕሬዚዳንት መንግስቱ ዘመንም አፍቃሪ ሶሻሊስትነቱን አጥብቀው የጠሉ ምዕራባዊያን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መቀመጫ ከአዲስ አበባ ለማውጣት ያልሞከሩት ሴራ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።

በዘመነ ኢህአዴግ ደግሞ ትሪፖሊን በረብጣ ገንዘብ ያስዋቡት ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ አዲስ አበባን የጸጥታ ችግር አለባት በማለት ወደ ሊቢያ ለመውሰድ ብዙ ጥረው ነበር። ዳፋው እስከ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ዘልቆ ለሕዝብ ይፋ ያልተደረጉ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል።

የዘመድ ባንዳ እና የጠላት እንግዳ የማይነጥፍባት ኢትዮጵያ 35ኛውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በጊዜያዊነት እንዳታካሂድ እና በዘላቂነትም የሕብረቱ መቀመጫ ከአዲስ አበባ እንዲነሳ ሸገርን በሃሰት ፕሮፖጋንዳ የናጡት ምዕራባዊያን ብዙ ነበሩ።

ከኮሮኖ ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዳራሽ ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘው የመጀመሪያ ስብሰባ አዲስ አበባ እንዳታስተናግድ ሴራ የተጎነጎነባት ኢትዮጵያ ምክንያቱ ደግሞ የሽብር ቡድኑ የፈጠረው ግጭት ነበር።

የማትታጠፈው ኢትዮጵያ ግን ሟርቶቿን እየሻረች ፈተናዎቿን እየተሻገረች መሪዎቹን ከአዳራሽ አውጥታ በአደባባይ አሰማርታ ጋቢ አልብሳ አሳየችን።

ይህ ከዲፕሎማሲም ከፍ ያለ ታሪካዊ ድል ነው። ኢትዮጵያም ያለፈተና ሳይሆን በፈተና ውስጥ እየተመላለሰች ዳግም የነጻነት መምከሪያ ነጻ ምድር ትሆናለች።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የወባ በሽታን ለመከላከል ቁርጠኝነታቸውን እያሳዩ መሆኑን የኬንያ ኘሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ገለጹ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከናይጄሪያ እና ዚምባቡዌ ፕሬዚዳንቶች ጋር በኹለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ።