በጎንደር አካባቢ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር የቱሪስት ፍሰቱ ላይ የጎላ ተፅዕኖ አለማሳደሩ ተገለጸ፡፡

154

ስለ ጎንደር የፀጥታ ሁኔታ በሩቁ የሚወራው የተጋነነ እንደሆነም ጎብኝዎች ተናግረዋል፡፡

ባሕር ዳር፡ መስከረም 29/2012 ዓ/ም (አብመድ) ከሰሞኑ በጎንደር እና አካባቢዋ የተወሰነ ግጭት ተፈጥሮ የነበር መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህ ደግሞ ጎብኝዎች የመስህብ ስፍራዎችን ተረጋግተው እንዳይጎበኙ ስጋት መፍጠሩ ሲወራ ነበር፡፡ የጎንደር ከተማ አስገብኚዎች ማኅበር አባሉ አቶ ተሻገር ሰርፀድንግል ‹‹ከሰሞኑ በጎንደር ከተማ በማኅበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ግጭት እንዳለ ተድርጎ የሚወራው ወሬ በቱሪስት ፍሰቱ ላይ ጉልህ ጫና አላሳደረም›› ብለዋል፡፡ በነበረው ግጭት ከባሕር ዳር ወደ ሌላ ቦታ ተንቀሳቅሰው የነበሩ ቱሪስቶችም የፀጥታ ሁኔታውን ዓይተው ወደ ጎንደር ከተማ ተመልሰው ታሪካዊ ቦታዎችን እየጎበኙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የጎንደር አብያተ መንግሥታትን ሲጎበኙ ያገኘናቸው ትውልድ የመናዊው አህመድ ጋላወ “ጎንደር ለጎብኚዎች የሚማርኩ ብዙ ታሪካዊ ቅርሶች አሏት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ በኤምባሲው በኩል ማስጠንቀቂያ ደርሶኝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጎንደር ከተማ በተወሰነ ደረጃ ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር እየተስተካከለ ነው፤ ያለምንም ችግር እየጎበኘን ነው፤ ሰውም እንግዳ አክባሪ ነው” ብለዋል፡፡ ሌሎችም ጎንደርን እንዲጎበኙም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ደግሞ ወይዘሮ ሕይወት ገብረሥላሴ እና አቶ ካሳ ጎዳና “ስለ ንደር ከተማ በርቀት ሆነው ለሚሰሙ ሰዎች ሠላም ያላት አይመስልም፤ በአካል ተገኝተን ያየነው ግን ከሰማነው ፍፁም የተለየ ነው” ብለዋል

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ የነበረው አለመረጋጋ በቱሪዝም ፍሰቱ ላይ ተፅዕኖው የከፋ አለመሆኑን እና የቱሪስት ፍሰቱም አለመቀነሱን አረጋግጠዋል፡፡ ቅርሶች እንዳይጎዱና የአካባቢውን ሠላም በመጠበቅ ረገድ የፀጥታ አካላት፣ ወጣቶች እና ኅብረተሰቡ ተገቢውን እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከሐምሌ ወር ጀምሮ 3 ሺህ 950 የውጭ ሀገር እና 32 ሺ 124 የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ጎንደርን እንደጎበኙም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleምን ጎደለው? የባሕር ዳር ዓለም እቀፍ ስታዲየም
Next articleየጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና ጥቅምት 3 ቀን 2012ዓ.ም ይጀመራል፡፡