የኢትዮጵያ መሪዎች አፍሪካዊነት ሲታወስ።

306

ባሕር ዳር: ጥር 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ጽኑነት መሪዎቿ ቢቀያየሩም የማይናወጥ አንድነታዊ አቋም እንዳላት በተለያየ ጊዜ አሳይታለች፡፡ ላለፉት 60 ዓመታት መሪዎቿ አፍሪካዊነትን በማቀንቀን ለሕብረቱ መጠናከር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል::

ያኔ ምእራባዊያን አፍሪካን ተቀራምተው አህጉሪቱን የመጋለቢያ ሜዳ ሲያደርጉ እነርሱን ለመሞገት፤ አፍሪካንም ወደ አንድ ለማምጣት ሩቅ አሳቢ ልጆች ቆርጠው ሲነሱ ዛሬ ለተሰጣቸው የአፍሪካዊ አባትነት የበቁት የሃበሻዊቱ ምድር መሪ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አንደኛው ነበሩ፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በዚያን ወቅት በተለያ ቡድኖች ተከፋፍለው የነበሩት ካዛ ብላንካ እና ሞኖሮቪያ ቡድኖች ወደ አንድ በማምጣት አፍሪካዊ ማንነትን የመፍጠር ሂደት ላይ ትልቅ የመሪነት ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡

ድርጅቱ ሲመሰረት ዋነኛ ዓላማው በቅኝ ያደሩ የአፍሪካ ሀገራትን ነጻ ማውጣት ነበር፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ህልም እና ሥራቸው ተሳክቶላቸው የተለያዩ አፍሪካዊ ቡድኖቹን ወደ አንድ በማምጣት የአፍሪካን አንድነት ደርጅት መመስረት እውን አድርገዋል፡፡ ንጉሱ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ውስጥ እጅግ ረዥም የሆነ የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን በአግባቡ ተጠቅመውበታል፡፡

ከድርጅቱ መመስረት ቀደም ብሎም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዲስ አበባ ውስጥ በራሷ በኢትዮጵያ ገንዘብ እንዲገነባ ማድረጋቸው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን ትልቁን ሚና ተጫውቶላቸዋል፡፡

እኒያ ባለትልቅ ህልመኛ አፍሪካዊ አባት እንዳሉትም አደረጉት፤ ሀገርን ሳይሆን አህጉርን አንድ የሚደርግ ታላቅ ድርጅትን በታላቅ የነጻነት ተምሳሌት ምድር አዲስ አበባ ላይ ተከሉ፡፡ አፍሪካዊያን ከጨለማ ዘመን ወጥተው የነጻነትና አንድነት ጎህ ስለመቅደዱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለዓለም አበሰሩ፡፡ እነዚያ አፍሪካን በእግራቸው እረግጠው የማያውቁት ባዕዳን እንኳ አፍሪካን የጨለማ ምድር ብለው መሰየማቸውን እንቀይራለን አሉ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፡፡

የንጉሱ አፍሪካዊ እሳቤ በድርጅቱ በኩል ብቻ አይደለም በግላቸውም ድንቅ አፍሪካዊ ክዋኔዎችን ፈጽመዋል፤ የማይታረቁ የሚመስሉ አፍሪካዊ ልዩነቶችን አስማምተዋል፡፡

ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማሪያምም በሀገር ውስጥ ጉዳይ ብዙ የሚኑሳባቸው ቅራኔዎች ቢኖሩም በአፍሪካ ጉዳይ ግን ወደ ኋላ ያሉበት ጊዜ እንደሌለ ይነገራል፡፡ የያኔዋ ሶሻሊስት ሀገር ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግሰቱ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለአህጉራችን ከፍተኛ ተቆርቆሪነት ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ ለዚህ ማሳያው ነፃ ያልወጡ የአፍሪካ ሀገራትን በመርዳት አኳያ ብርቱ ድጋፍ እያደረግን ነበር፡፡ አሁንም እያረግን ነዉ፡፡ ዝምባቡዌ ነፃ እንድትሆን ጥረናል ፤ ለዚህም የዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ አስረጅ ነው ሲሉ መናገራቸው ይታወሳሉ፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን ካልነኩን አንነካም ከነኩን ግን አንደፈርም እስከመጨረሻው የሀገራችንን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስከበር የማንከፍለው መስዋዕትነት የለም፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን እኛ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረን የሠመረ ግንኙነት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት መስፈን የሚኖረው አወንታዊ ሚና ጉልህ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ከ53 የአፍሪካ እህት ሀገራት ጋር በአብሮ አቀፍ መርህ ተባብሮ ለመስራት ቀድሞም በነበሩት መንግስታት አቋም አንፃር ይሁን አሁንም ለወደፊት የአፍሪካ ጉዳይ ጉዳይዋ አድርጋ ትመለከታለች በማለት ጠንካራ አፍሪካዊ አቋም እንዳላቸው አሳይተዋል ኮሎኔል መንግስቱ፡፡

በውስጥ ጉዳይ ኢትዮጵያዊያንን በዘር ፖለቲካ በመከፋፈል ሀገራዊ አንድነት ማስጠበቅ የተሳናቸው፣ መለስ ዜናዊም ለአፍሪካዊያን አንድ መሆንና ለሕብረቱ መጠናከር ጥረት አድርገዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2009 የኮፐን ሃገን ስብሰባ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ኃያላኑ ሀገራት አፍሪካን ለበደሏት መካሻ ከ50 ቢሊየን ዶላር በላይ በየዓመቱ እንዲከፍሉ ማስማማት ችለው ነበር፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ህብረት ሲቀየር የአዲስ አበባ መቀመጫነትን ለማንሳት የነበረውን የሌሎች ሀገራት ፍላጎት ያከሸፉበት ንግግር ዛሬም ድረስ ዓመታትን ተሻግሮ እንዲታወሱ ያደርጋቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝም ቀጠሉ በእኔ እምነት ኢትዮጵያ የብዙ ጥቁር ሕዝቦች ምሳሌ ከመሆን ባሻገር አያሌ ሀገራት የኢትዮጵያን ባንዲራ መጠቀማቸው ሀበሻዊቱ ምድር የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት አርአያ መሆኗን ያሳያል በሚል ንግግራቸው አፍሪካዊ አቋማቸውን ገልጠው አሳይተዋል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት በሕበረቱ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) በሚኒልክ እልፍኝ አፍሪካ መሪዎችን እራት ጋብዘው አንዲህ የሚል ንግግር አደረጉ “ኢትዮጵያ እናንተ የተከበራችሁትን የአፍሪካ ልኡካን ስታስተናግዳችሁ ከፍ ያለ ኩራት ይሰማናል፡፡ እኛ አፍሪካውያን ከ60 ዓመታት በፊት ነበር ለሰላምና እድገት እጅ ለእጅ ተያይዘን ለመሥራትና ለአህጉሪቱ እድገት የበኩላችንን መወጣት የጀመርነው፡፡ ያኔ በአህጉሪቱ የሚከናወኑ ጦርነቶችን እስከ 2020 ለማስወገድ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን አባቶቻችን እቅድ ነድፈው በመንቀሳቀስ ዛሬ ላይ የቤት ሥራውን ለእኛው ትተው አልፈዋል፡፡ ስለዚህም የዚህ ዓመት መርሐችን ከጦርነትን ነጻ ሆነን የተቀናጀች አፍሪካ እውን እንድትሆን ማድረግ ቀዳሚው አህጉራዊ አጀንዳችን ሊሆን ይገባል” ሲሉ ለአፍሪካዊነት አንድነት ያላቸውን አቋም አሳይተዋል፡፡

ዛሬ አፍሪካ እንደ አህጉር በተለያዩ ሂደቶች ዓለም አቀፍ ውክልናን እንድታገኝና ከምእራባውን አመለካከትና ተጽእኖ ነጻ በመውጣት ራሷን የቻለች አህጉር እንድትሆን የዛሬዎች መሪዎቿ ትልቁን ኀላፊነት ወስደዋል፡፡ ከትላንት ታላቅ አፍሪካዊ ተቋም ከመፍጠር የተነሱት ኢትዮጵውያን መሪዎች አሁንም በአንድነቷ ወደኋላ ብለው አያውቁም፡፡ አፍሪካ አንድ እንድትሆንና በቀጣይ በአህጉራዊ ትብብር የተሻለች አፍሪካን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት አጀንዳ 2063 ትልቁ ማሳያ ተደርጎ ሲወሰድ ኢትጵያውያንም ለዚህ አህጉራዊ ስኬት ሚናቸውን በተግባር ለማሳየት ወደ ኋላ ብለው አያውቁም፡፡

ዛሬም ምድረ ነጻዋ ሀገር በሚደርስባት ውጫዊ ጫና ሳትበገር መስራችነቷ ዋስትና ሆኗት አፍሪካውያንም ኮርተውባት ትልቁን የአፍሪካውያን መሪዎች ጉባዔ እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ ይህ ነው የኢትጵያውን አፍሪካዊ ውለታ፡፡ ታላቋ የነጻነት ምድር ተምሳሌት ኢትዮጵያ፡፡

ዘጋቢ፡- አንዷለም መናን- ከአዲስ አበባ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሃመድ ሽታይ አዲስ አበባ ገብተዋል።
Next article35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መካሄድ ጀመረ።