ጥር እና ቱሪዝም በአማራ

265

ጥር 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጥር በውብ እና አጓጊ ትዕይንቶች ይደምቃል። ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ከወሩ ዋዜማ ታኅሣሥ 29 የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ጀምሮ የጥምቀት እና አስተርዮ በዓላት በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በልዩ ድምቀት የሚከበሩ በዓላት ናቸው። ሕዝባዊ በዓላት እና ኹነቶችም የወሩ ድምቀቶች ናቸው። በጥር ወደ አማራ ሲዘልቁ ደግሞ በእጅጉ የተለዬ ወር ነው። የወሩ ቀናት ኹሉ እንደ ክብረ በዓል የሚናፈቁም ናቸው።

ከመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ 30 ዎቹም ቀናት ልዩና አጓጊ ድባብ አላቸው።

ጥርን በባሕር ዳር

በታንኳ ቀዘፋ እና ጀልባ ትዕይንት አይረሴ ትዝታዎች፣ በደብረማርያም ገዳም እና ሰባሩ ጊዮርጊስ የጣና ላይ ጥምቀት እና ልዩ የንግሥ አከባበሮች የምትደምቅባቸው ውብ የቱሪዝም ሀብቶች ናቸው። ለጥምቀት በዓል የሚደረጉ ዝግጅቶች ከወሩ መግቢያ ጀምሮ በሽርጉድ የተሞሉ ናቸው።

ጥምቀትን በጎንደር

ሽቅርቅሯ ጎንደር በጥር ወር ትደምቃለች። በቃ ትሞሸራለች ! በሰንደቁ ተሞሽራ፣ በጃኖ አጊጣ እዩኝ እዩኝ እያለች የምትጋብዝበት ፍቅር የምታስይዝ ከተማ ናት- ጎንደር። ለጥምቀት በዓል በእንግድነት ወደከተማዋ የሚገቡትን ጨምሮ ከሕጻን እስከ አዋቂ በውብ የባሕል አልባሳት ይዋባሉ። መንፈሳዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎችም ልዩ ናቸው። ከዓመት ዓመትም ጥምቀትን ጠብቀው በከተማዋ ለመታደም የሚናፍቁት በርካቶች ናቸው።

ጥምቀትን በኢራንቡቲ

የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው ኢራንቡቲ ፡፡

በበዓለ ጥምቀቱ 44 ታቦታት በአንድላይ ተሰባስበው ነው የተከበረው፡፡

በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በኢራንቡቲ ቀበሌ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ዘንድሮ ለ620ኛ ዓመት በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ ‘ዳግማዊ ዮርዳኖስ’ በዓለ ጥምቀት በተለየ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥነ ሥርዓት በደመቀ መልኩ ተከብሯል፡፡

ግዮንን በግዮን

የዓባይ ወንዝ መነሻዋ ሰከላ የምትደምቀው በጥር ወር ነው። የግዮን በዓል በየዓመቱ ጥር 13 በዓባይ ወንዝ መነሻ ስፍራ በልዩ ድምቀት ተከብሯል፡፡ ግዮንን በግዮን ወደፊት የአፍሪካዊያን እና የግዮናዊያን (በግዮን ተፋሰስ የሚኖሩ ሕዝቦች) ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ ክብረ በዓል እንደሚኾን አያጠራጥርም። ኃይማኖታዊ ክዋኔ እና ባሕላዊ ክዋኔዎች ልዩ የበዓሉ ትውስታዎች ናቸው።

አስተርዮን በመርጡለ ማርያም

በኦሪት ዘመን መስዋእት ከሚሠዋባቸው 4ቱ እጅግ ጥንታዊ ገዳማት አንዷ መርጡለማርያም ገዳም ናት። በ333 ዓ.ም በሕገ ኦሪት ፀንታ የዘለቀች፣ ውብ እና ምስጢራዊ ምልክቶችን የያዘ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ባለ ዐሻራ የኾነች፣ የበርካታ ሰማእታት፣ ነገሥታት እና ታዋቂ ሰዎች የክብር ልብሶችና ጌጣጌጦች፣ ቅርሶች ባለቤት የኾነችው ይች ገዳም ጥር 21 ልዩ ክብረ በዓሏ ነው። በተለይ በንግሥ ቱሪዝም ትልቅ እድገት ያላት በመኾኑ በየዓመቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ እንግዶች ወደከተማዋ ያቀናሉ። አስተርዮን በመርጡለማርያም ታቦተ ሕጉ ሊቀ ጳጳሳት እና ምዕመናን ታጅቦ የሚከበር በመሆኑ፣ የቅርስ ጉብኝቶች እና ባሕላዊ ክዋኔዎች አጓጊ በመኾናቸው በዓሉን ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾን አስችሎታል።

አስተርዮን – በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም

ግሸን ደብረ ከርቤ ማሪያም ገዳም በደቡብ ወሎ ዞን በአምባሰል ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ከቀደምት ገዳማት ውስጥ አንዱ ነው። ከአምባሰል ከፍተኛ ተራሮች ውስጥ በአንዱ የሚገኘው ግሸን ደብረ ከርቤ የተራራው አናት (አምባ) መስቀለኛ ቅርጽ ያለው ነው። ይህ ቦታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል የሚገኝበት ነው።

ግሸን ደብረ ከርቤ ማሪያም ገዳም በዓመት ሁለት ጊዜ መስከረም 21 እና ጥር 21 በሚከበሩት በዓላቶቿ በርካታ ቁጥር ያለው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እና ጎብኚዎች ከተለያዩ አካባቢዎች ይታደማሉ።

ጥር 21 የተከበረው የአስተርዮ ማርያም የንግሥ በዓል በግሸን አምባ በግሸን ደብረ ከርቤ ማሪያም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

የአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓል

ክብረ በዓሉ ባሕል፣ ጥበብ፣ ውበት እና ታሪክ በአንድ መድረክ የሚቀርቡበት ልዩ ትዕይንት ነው። የፈረሰኞች ጥበብ በእጅጉ ያስደምማል። ፈረስ ለአዊ ሕዝብ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡ የጥበብ ማሳያውም ኾኖ የሚታይበት በዓል መኾኑ ተመስክሮበታል። የአዊ ሕዝብ ባሕል በውብ አለባበስና አጨፋፈር የሚደምቅ ቀንም ነው። ክብረ በዓሉ የታሪኩ መነሻም የአገውን ሕዝብ ጀግንነት የሚያወሳ በመሆኑ ድባቡን የተለየ ያደርገዋል። የበዓሉ ታሚዎች ክብረ በዓል አይረሴ እና ድንቅ ትውስታዎችን የሚጎናፀፉበት በመኾኑ የአገው ፈረሰኞች ክብረበዓል ወደፊት ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ የሚኾን ነው። ዘንድሮውም 82ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በዓል በድምቀት ተከብሯል፡፡

መርቆሬዎስን በደብረታቦር

ፈረሰኛው ሰማእት ቅዱስ መርቆሬዎስን ለመዘከር የሚከበረው የንግሥ በዓል ደብረታቦርን ከሚያስናፍቁ በዓላት አንዱ ነው፡፡

በበዓሉ የፈረስ ጉግስ ትርዒት ክብረ በዓሉን በጉጉት እንዲጠበቅ የሚያደርግ ኹነት ነው። ይህ በየዓመቱ ጥር 25 ቀን በድምቀት የሚከበር ክብረ በዓል ሃይማኖታዊ ክንውኖቹ፣ ባሕላዊ ወጉ ሳቢ ኾኖ ከዓመት አመት የታዳሚዎቹም ቁጥር እያደገ የመጣ ትልቅ የቱሪዝም ሀብት ነው።

ጥር በአማራ በእነዚህ እና በሌሎችም ደማቅ ትዕይንቶች ልዩ ወር እንድትኾን አስችሏታል። በርካታ ኢትዮጵያውያንም በጥር ወር ወደ ክልሉ በመዝለቅ ይታደማሉ። የውጭ ሀገር ዜጎችም በብዛት ይመጣሉ። የቱሪዝም ድምቀት ወርም ነው። በቀጣዩ ዓመት በጥር ወር እነዚህን ክብረ በዓላት ለማሳለፍ ከወዲሁ እቅድ ይያዙ።

በሀብተጊዮርጊስ አበይ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነሮች ላይ የሕዝብ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ይፋ አደረገ፡፡
Next articleበሁለተኛ ዙር ሲሰጥ የነበረው የ2013 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።