
ባሕር ዳር: ጥር 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኤፍ. ኤች ኢትዮጵያ እና አመልድ ኢትዮጵያ ከዩ ኤስ ኤድ ባገኙት የገንዘብ ድጋፍ በአማራ ክልል በ18 ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረግ ከ10 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የተመደበለት ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ፡፡ በፕሮጀክቱ በ18 ወረዳዎች የሚኖሩና በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ ግማሽ ሚሊየን የሚጠጉ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡
የዩ ኤስ ኤድ (USAID) ሚሽን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሶን ጆንስ ዛሬ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት በክልሉ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እና በችግሩ ሰለባ የኾኑ ሰዎችን ራሳቸውን በምግብ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ ዩ ኤስ ኤድ በአማራ ክልል በርካታ ተግባራትን አከናውኗል ያሉት ሚስተር ሶን ጆንስ በቀጣይ አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክትም በትምሕርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር ) ክልሉ በርካታ ችግሮችን ማስተናገዱን ገልጸዋል፡፡ ዶክተር ይልቃል ዛሬ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች መልሶ መቋቋም ድርሻው ከፍተኛ ነው፤ ይህን ላስተባበሩ አካላትም ምስጋና ይገባል ነው ያሉት፡፡
ፕሮጀክቱ የታለመለትን ዓላማ ይመታ ዘንድ ክልሉ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ፕሮጀክቱን በኤፍ. ኤች ኢትዮጵያ እና በአመልድ ኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚደረግ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን በ18 ወረዳዎች የሚኖሩ ግማሽ ሚሊየን የሚጠጉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በልማታዊ ሴፍትኔት መርኃግብር በክልሉ የምግብ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች መሠረት ተደርጎ የሚሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ባደረሰው ውድመት ለችግር የተጋለጡ ሰዎችን ለማቋቋም እና ወደ ቀድሞ ሕይዎታቸው ለመመለስ ፕሮጀክቱ ድርሻው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በትምሕርት፣ በጤና፣ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ እና በሥራ እድል ፈጠራ ላይ የጎላ ድርሻ እንዳለውም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/