
ባሕር ዳር: ጥር 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ንጉሥ ሚካኤል በሳል እና ተራማጅ፣ ሩህሩህ እና ቆራጥ፣ ሀገር ወዳድ እና ስልጡን ኢትዮጵያን የሚመስሉ እና ወሎን የሚወክሉ ንጉሥ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ አይጠየፍ አዳራሹ የንጉሡን ማንነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ከመቅደላ አምባ አሻጋሪ ከከፍታው አናት ላይ የከተመችው ተንታ የንጉሡን የከፍታ ዘመን ታመላክታለች፡፡
ንጉሥ ሚካኤል የወሎ፣ የትግሬ፣ የበጌምድርና ጎጃም ንጉሥነትን ያጣመሩ የክርስትና ጠበቃ እና የእስልምና መከታ ነበሩ፤ ሁሉንም የታደሉ ከምንም በላይ ደግሞ ጀግና ንጉሥ ነበሩ፡፡ ወሎን ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ያስተዳደሩ እና በአድዋ ጦርነት በሦስት አውደ ውጊያዎች ጦር መርተው ለድል ያበቁ ናቸው፡፡
የልጅ ኢያሱ እና የወይዘሮ ስሂን አባት፣ የእቴጌ መነን አያት፣ የጃንሆይ አማት፣ የአፄ ምኒልክ ባለሟል እና ቀኝ አጅ፡፡
የደስ ደስ ያላትን የደሴ ከተማን የቆረቆሯት የወሎው ንጉሥ ሚካኤል እንደሆኑ ይነገራል፡፡ የአሁኗ ደሴ ንጉሥ ሚካኤልን ትመስላለች የሚሉትም ብዙ ናቸው፡፡ ከየት መጣችሁ ሳይሆን እንኳን ደህና መጣችሁን የተካነችው ደሴ አዎ! ንጉሷን አብዝታ ትመስላለች፡፡ የግብር አዳራሻቸው እንኳን ከነስሙ “አይጠየፍ” ነው፡፡
በጦሳ እና በአዝዋ ተራሮች ከተከበበችው ደሴ አናት ላይ የበቀለው አይጠየፍ ከደሃ እስከ ሃብታም፣ ከሙስሊም እስከ ክርስቲያን፣ ከባላባት እስከ ጭሰኛ፣ ከሴት እስከ ወንድ፣ ከልጅ እስከ አዛውንት፣ ከእንግዳ እስከ ቤተኛ፣ ከንጉሥ እስከ አሽከር፣ ከእመቤት እስከ አገልጋይ አኩል የንጉሥ ማዕድ የሚጋሩበት ነበር፤ ይህ ታላቅ አዳራሽ የተገነባው በንጉሥ ሚካኤል ነው፡፡
በ1907 ዓ.ም እንደተሠራ የሚነገርለት ይህ ግዙፍ የግብር አዳራሽ አይጠየፍ የሚለው ስያሜ የተሰጠው በራሳቸው በንጉሥ ሚካኤል ነው፡፡
የልጅነት ዘመናቸው መጠሪያ ሙሃመድ አሊ ሲሆን የኋለኛው እና የንግሥና ዘመናቸው መጠሪያ ደግሞ ንጉሥ ሚካኤል ይባላል፡፡ የወረሂመኖው ባላባት እና ገዥ ከነበሩት አባታቸው አሊ አባ ቡላ እና ከእናታቸው ጌይቲ ገባቤ ጥር 27/1842 ዓ.ም እንደተወለዱ ታሪክ ይነግረናል፡፡ የአባታቸው የሕግ ሚስት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ገናና ሥም ያላቸው እና አፄ ቴዎድሮስን ሳይቀር እስከ ሕልፈታቸው ዘመን ድረስ የፈተኑት የወሎዋ ንግሥት ወርቂት ናቸው ይባላል፡፡
ንጉሥ ሚካኤል ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በየወቅቱ እየመጣ ከሚፈትናቸው የሴራ ፖለቲካ መቅሰፍት በርካቶቹን በብስለት አንዳንዶቹን ደግሞ በጀግንነት ካሻገሩት ነገሥታት መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ንጉሥ ሚካኤል ከሌሎች የሚለያቸው የምዕራባውያኑን የከፋፍለህ ግዛ ስልት ቀድመው ያወቁ በመሆናቸው ነው፡፡ ንጉሡ ኢትዮጵያ የውጭ ጠላት ባጋጠማት ጊዜ ሳይቀር የውስጥ ቅራኔያቸውን አቆይተው ለሀገር እና ለሕዝብ ክብር ሲሉ ሀገራቸውን ከአደጋ መታደጋቸው ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በወሎ ሕዝብ ልብ ውስጥ ምንጊዜም የማይጠፉት እና ኢትዮጵያውያን አባ ሻንቆ የሚሏቸው ባለውታቸው እና አይጠየፌው ንጉሥ ይህችን ምድር የተቀላቀሉት የዛሬ 172 ዓመታት በፊት በዚች ቀን ነበር፡፡ መልካም ልደት ለአይጠየፌው ንጉሥ!
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/