
ባሕር ዳር: ጥር 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የብቸኝነትን መጥፎ ጥግ ኢትዮጵያ ጠንቅቃ ታውቀዋለች፡፡ በዓለም የመንግሥታቱ ማሕበር ቋሚ ስብሰባ ውስጥ በአውሮፓውያን ጠረንጴዛ ዙሪያ ሰፊዋን አህጉር ወክላ ብቻዋን ለዘመናት ታድማለች፡፡
የብቸንነትን አስከፊነት ያየችው ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ባርነት ባይጫንባትም አፍሪካውያን ለነጻነታቸው በሕብረት ይቆሙ ዘንድ አጥብቃ ትሻ ነበር፡፡ ነጻዋ ሀገር ነጻ አህጉር ለመመስረት ከፍላጎት ያለፈ ጥረት ደጋግማ አሳይታለች፡፡ እውን እስኪሆንም ዘርፈ ብዙ ዋጋ ከፍላለች፡፡
ኢትዮጵያ ፍላጎቷ እውን ሆኖ 32ቱ ነጻ የአፍሪካ ሀገራት አህጉራዊ አንድነትን እና ሕብረትን ለመመስረት ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ገና አላለቀም፤ ውጣ ውረዱም ገና አልተቋጨም ነበር፡፡
የመግባቢያ ቻርተሩን ማን ያርቅቀው? የድርጅቱ መቀመጫ የት ይሁን? እና መሰል ጥያቄዎች መሪዎቹን የፈተኑ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ሀገራትም ምንም እንኳን ከቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ነጻ ይሁኑ እንጂ የቅኝ ግዛት ዳፋው ገና አልለቀቃቸውም ነበርና ስጋት እና ፍርሃት ጨምድዶ ይዟቸዋል፡፡
በዚህ የድርጅቱ የምስረታ ዋዜማ ወቅት ነበር ኢትዮጵያ የአፍሪካውያንን ሕብረት መንገድ ለመጥረግ ቀናዒ ልቦና እና ቁርጥ ውሳኔዋን ያሳወቀችው፡፡
ግንቦት 19/1955 ዓ.ም ለሚካሄደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመጀመሪያ ስብሰባ ኢትዮጵያ ለማስተናገድ ፍላጎት አሳየች፡፡
በወቅቱ በመሰረተ ልማት ከአዲስ አበባ የተሻሉ ከካይሮ እስከ ሌጎስ፤ ከናይሮቢ እስከ ትሪፖሊ ዓይነት ከተሞች እያሉ በወጉ የአውሮፕላን ማረፊያ የሌላት ሀገር ርዕሰ መዲና የአህጉራዊውን የብኩርና ስብሰባ እንዴት ማስተናገድ ይኖርባታል የሚሉ ቅሬታዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡
ስብሰባው የሚካሄድበት ጊዜ ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ ነው የቀረው፡፡ ለዝግጅት የሚሆነው ጊዜ ከሚታሰበውም ሊሆን ከሚችለውም ያነሰ ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሚኒስትሮቻቸውን ይዘው መከሩ፡፡ ቀን ከሌሊት ሠርተን ታሪካዊውን ስብሰባ በአዲስ አበባ እናካሂድ ወይስ እኛ ያመጣነውን የነጻነት ሃሳብ አሳልፈን እንስጥ? ሲሉም ጃንሆይ መከሩ፡፡
ከ10 ወራት የዝግጅት ጊዜ በቀረው ስብሰባ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የመሪዎቹ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ሆቴል እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መሟላት ነበረባቸው፡፡ በወቅቱ የሲዳማ ጠቅላይ ገዥ የነበሩት እና በንጉሠ ነገሥቱ የሥራ እና መገናኛ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው የመጡት ደጅ አዝማች መንገሻ ሥዩም “ገንዘብ ከተሟላልኝ ከተሰጠው ጊዜ ቀድሜ ሠርቸ ማስረከብ እችላለሁ” ሲሉ የመሪዎቹን ጭንቅ አቃለሉት፡፡ እርግጥ ነው አይቻልም ያሉት ቢበዙም በደጅ አዝማቹ እምነት የነበራቸው ንጉሠ ነገሥቱ ይሁንታን ሰጧቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከውስጥ ለሥራ እየመከረች እንዳለመታደል ሆኖ ከውጭ በሴራ የሚመክሩባት ነበሩ፡፡ በተለይም በወቅቱ ከአፍሪካ ሀገራት ተፅዕኖ ፈጣሪ መሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት የግብጹ ጋማል አብድል ናስር ኢትዮጵያ እንዳታዘጋጅ ሌሎቹን ሀገራትም ያነሳሱ ነበር፡፡
ከጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተ ወልድ እስከ ከተማ ይፍሩ፣ ከዶክተር ተስፋየ ገብረግዚዕ እስከ ዶክተር ምናሴ ኃይሌ፣ ከአቶ ሰይፈ ማሕተመ ሥላሴ እስከ አፈ ንጉሥ ተሾመ ወደ ተለያዩ ሀገራት በማቅናት መሪዎቹን ማግባባት ጀመሩና ተሳካላቸው፡፡ ኢትዮጵያ የዛሬው ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን የ11 ሰዎች ሕይዎት ተገብሮበት እና በአንድ ቀን በሦስት ፈረቃ 24 ሰዓት እየተሠራ በተባለለት ጊዜ ተጠናቀቀ፡፡
ግዮን፣ ኢትዮጵያ፣ ጣይቱ፣ ሂልተን እና መሰል ውስን ሆቴሎች ብቻ የነበሯት አዲስ አበባም ለ32ቱ የአፍሪካ መሪዎች ማረፊያ አይመጥኑም ነበርና ግዮን ሆቴል ላይ ለመሪዎቹ የሚመጠን ቅጥያ ሕንጻ ተሠርቶ ተጠናቀቀ፡፡
አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ የ32 ሀገራት ሰንደቅ ከፍ ብሎ በየጎዳናዎቿ ተውለበለበ፡፡ አፍሪካ ከባርነት፣ ከፍርሃት እና ከቆፈን ወጥታ በነጻነት ለመምከር እና ስምምነቱን ለመፈራረም ድቅድቁን ጨለማ እና አስፈሪውን እኩለ ሌሊት ትጠባበቅ ነበር፡፡ ይህንን መሰሉን ትልቅ የነጻነት ሁነት በቀጥታ ለሕዝብ ዐይን እና ጆሮ ለማቅረብ ታሪክ አጋጣሚ የፈጠረለት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እውን መሆን ከውጭው ዓለም ጋዜጠኞች ጋር እኩል ለማቅረብ ታደለ፡፡
የያኔውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እና የአሁኑን የአፍሪካ ሕብረትን ምስረታ በስላቅ ያዩት ምዕራባዊያን ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ሳይወዱ በግድ ኢትዮጵያን “የአፍሪካውያን ሕብረት መንገድ ጠራጊ!” ለማለት ተገደዱ፡፡
ኢትዮጵያም ለ35ኛ ጊዜ መሪዎቹን ለማሰባሰብ እድሜ ያገኘው ሕብረት እውን ይሆን ዘንድ ዋጋ ከፍላለች፡፡
“የኢትዮጵያ ታሪክ” በአንድርዜይ ባርትኒስኪ እና “የኢትዮጵያ የመከራ ሥርዓት…” በፕሮፌሰር ላጵሶ ጌ ድሌቦ በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/