“የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር ዳግም ሥራ ይጀምራሉ” ትምህርት ሚኒስቴር

113
ጥር 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ዘረፋና ውድመት የተፈፀመባቸው የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ተማሪዎችን በመቀበል ዳግም ሥራ የሚጀምሩ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአሸባሪው የትግራይ ቡድን ወረራ ተዛብቶ የቆየው የአካዳሚክ ካሌንደር በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ይስተካከላል ተብሏል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ለኢዜአ እንደገለጹት በአማራ ክልል አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በከፈተው ጦርነት ሳቢያ የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሥራ አቋርጠዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው ወራት ዩኒቨርሲቲዎቹን ዘርፎና አውድሞ መሄዱን አስታውሰው በዳግም ጥገና ሥራ እንዲጀምሩ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።
በመንግሥት ድጋፍና ባላቸው አቅም አስፈላጊ ግዥዎችንና ጥገናዎችን እንዲያካሔዱ ከማድረግ ባለፈ አማራጭ የትምህርት ማስኬጃ መንገዶችንም እንዲያስቡና ወደ ሥራ እንዲገቡ አሁንም ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በመሆኑም የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ተማሪዎችን በመቀበል ዳግም ሥራ የሚጀምሩ መሆኑን ዶክተር ሳሙኤል ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ የመጨረሻ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎችን ቀድመው በመቀበል ሌሎችንም በሚያወጡት መርኃ ግብር መሰረት የሚቀበሉ ይሆናል።
በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተዛብቶ የቆየው የአካዳሚክ ካሌንደር በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ይስተካከላል ብለዋል ዶክተር ሳሙኤል።
የአካዳሚክ ካላንደሩን በማስተካከል በዩኒቨርሲቲዎች የተሳካ የመማር ማስተማር ሂደት እውን ለማድረግ አጠቃላይ የትምህርት ማኅበረሰቡ፣ ተቋማት፣ግለሰቦችና ሌሎችም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
Previous articleየማላዊ ፕሬዚዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ አዲስ አበባ ገቡ።
Next articleኢትዮጵያ- የአፍሪካውያን ሕብረት መንገድ ጠራጊ!