
ጥር 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከደሙ ንጹሕ፣ ከበደሉ ሩቅ፣ ለፖለቲካ ባይተዋር፣ በአካል እና በአዕምሮ ገና ልጅ ብትኾንም ከሰውበላ አረመኔዎቹ ጥቃት አላመለጠችም፡፡ ሊያመክኑ ያልሞከሩት ራዕይ፣ ሊያጨለሙት ያልዳዱት ልጅነት፣ ሊፈታተኑት ያልሞከሩት ብርታት እና ሊያቆስሉት ያልከጀሉት ንጹሕ ልብ የለም፡፡ አሸባሪው ትህነግ አማራን ጠልቶ ኢትዮጵያን ረስቶ ተመስረተ፡፡ በከፈተው ጦርነት ጠግበው ያልጨረሱ ሕጻናት፣ መቃብራቸው የተማሰ ልጣቸው የተራሰ አዛውንት፣ ሴቶች እና ነብሰ ጡር እናቶች ላይ ግፍ ፈጽሟል፡፡
የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ቃልኪዳን ተኮላ የኮምቦልቻ መሰናዶ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነች፡፡ ቃልኪዳን አባቷ በሕይዎት የሉም፤ ያሏት መጠጊያ እና ተስፋ አቅመ ደካማ እናቷ ብቻ ናቸው፡፡ ቃልኪዳን ነገን ስለራሷ ብቻ ሳይኾን ለእናቷ ችግር ለመድረስም አጥብቃ ትፈልገዋለች፡፡
የምትደርስለት ሕይዎት፣ እፎይ የምታሰኘው የልብ ሰው እና የምታሳርፈው ድካም ያላት ባለራዕይ ልጅ ነች፡፡ እናቷ የድካማቸው ዘመን ምርኩዝ በቃልኪዳን ተስፋ ላይ የተንጠለጠለ ነበር፡፡ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ ክልል በከፈተው ወረራ እና በፈጸመው ጥቃት ግን የቃልኪዳን የልጅነት ብርታት በእጅጉ ተፈተነ፡፡
ሕዳር 16/2014 ዓ.ም ለቃልኪዳን እና አቅመ ደካማ እናቷ ጥሩ የምትባል ቀን አልነበረችም፡፡ ከእነዚያ እርጉማን በተተኮሰ ጥይት ቃልኪዳን የግራ እጇ ተመታ፡፡ የተመታችው ግራ እጇን ቢኾንም የቀኝ ነርቯም በጉዳቱ ስለተነካ ቀኝ እጇም በቀላሉ የሚታዘዛት አይደለም፡፡
ተማሪ ቃልኪዳን ሕይዎት አብዝታ በፈተነችበት በዚህ ወቅት ለሌላ ፈተና መቀመጥ አልነበረባትም ነበር፡፡ ነገር ግን ባላት ራዕይ፣ ስለእናቷ ስትል ልታጠፋው የምትፈልገው ጊዜ እና ልትንበረከክለት የምትችለው መሰናክል የለምና ለሌላ ፈተና ተዘጋጀች፡፡
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን እሷ እያነበበች ሌላ ሰው እየጻፈላት እንድትፈተን ቃልኪዳን ጥያቄ አቀረበች፡፡ የቃልኪዳን መምህራን ፈተናውን ከሕመምሽ ካገገምሽ በኋላ ሰኔ ላይ ትወስጃለሽ ቢሏትም ስለነገም ርግጠኛ ያልሆነችው ቃልኪዳን ዛሬን ማለፍ አልፈለገችምና ፈተናውን እንድትወስድ ተፈቀደላት፡፡
“ወደፊት የእጄ ሁኔታ አይታወቅም፤ ቀዶ ጥገናም ሊያስፈልገኝ ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ከምጠብቅ ሕመሜን ተቋቁሜ ፈተናየን ብወስድ ይሻላል” ያለችው ተማሪ እሷ እያነበበች ሌሎች እየጻፉላት ፈተናውን መውሰድ መጀመሯን ተናግራለች፡፡
በርታቷን ብዙ ነገሮች የፈተኗት ተማሪ ቃልኪዳን እናቷ እርሷን የማሳከም አቅም እንደሌላቸው ገልጻ ኢትዮጵያዊያን እንዲያግዟትም መጠየቋን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ። https://ameco.bankofabyssinia.com/