ʺደብረ ታቦር በአጅባር ሜዳ ሰማይ ሥር”

310

ታቦር፡ ጥር 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ፈረሰኞቹ በኩራት የሚተምሙባት፣ ጀግኖች በጀግንነት የሚኖሩባት፣ ጠላቶች የሚፈሯት ወዳጆች የሚያከብሯት፣ የሚመኩባት፣ ሩቅ በሚያስበው ንጉሥ ሩቅ የታሰበባት፣ ዘመናዊነት የተጀመረባት፣ ጀግኖች የተወለዱባት፣ ሃይማኖት የታነፀባት፣ ታንፆም የፀናባት፣ መለኮት በተገለጠበት ቅዱስ ሥፍራ ሥም የወረሰች፣ ሌሎች ሳይዘምኑ ዘመናዊነትን የጀመረች፣ የሩቅ ዘመን ራዕይ የጀመረች፣ የነደፈች ቀደምት ከተማ ።

ያቺ የስልጣኔ ማዕበል ሊያጥለቀልቃት፣ ዘመናዊነት ሊያስጨንቃት የነበረች ባለተስፋዋ ከተማ ከአድማስ ባሻገር ያለውን የማለዳ ጀንበር ገልጦ ሊያሳያት የነበረው ታላቁ መሪ ጠፋባት። ባሩድ የሞላውን ሽጉጥ ወደ ጉሮሮው ገልብጦ ተሰናበታት፡፡ አብዝታ አዘነች፣ የነጋጋው ሌሊት ዳግም መሸባት፣ ጎህ ቀድዶ የነበረው ማለዳዋ ደበዘዘባት፣ በጠራው ሰማይዋ ጥቁር ደመና ተጋረደባት፣ ግርማዋን ተነጠቀች፣ ሞገሷን አጣች።

ያ ሩቅ አሳቢ፣ ምቾትና ድሎት የማይሻ ብርቱ ንጉሥ ታይቶ የማይታወቀውን አሳይቷት ነበርና እርሱን ማጣት ከባድ ሀዘን ነበር፡፡ ንጉሧን ብታጣም ታዲያ እምነቷን አላጎደለችም፣ ተስፋም አልቆረጠችም፣ ከጀግንነቷ አልቀነሰችም፣ ጀግናውና ባለ ራዕዩ መሪ በረገጠው ምድር ባለ ራዕይ ይወለዳል በሚል ተስፋ ጠበቀች፣ ጎህ ቀድዶ የነበረው ማለዳ ዳግም እስኪመለስ ድረስ ናፈቀች እንጂ፡፡ ሩቅ አሳቢውን ንጉሥ ብታጣውም ሩቅ ያሰበው ህልሙ ይሳካ ዘንድ የሀገር ደጀን ሆና ፀናች ታላቋ ከተማ ደብረታቦር። ሴባስቶፓል የተሰራባት፣ ኢትዮጵያዊነት የፀናባት፣ የቴዎድሮስ ራዕይ የታየባት፣ ዘመናዊነት ሀገር ንድፍ የተነደፈባት ናት።

“ወተትና ማሩ መጠጡ እያለለት፣
አንበሳው ቴዎድሮስ ለጠማው ጉሮሮ ባሩድ ጨመረበት”
እንደተባለ ራዕይ የተጠማው መሪ፣ አንድነት ተጠምታ የቆየችውን ሀገሩ ኢትዮጵያን አንድ አደረገ። ዘመናዊነት ሊያሳያት ከአድማስ ሊያሻግራት የማይተኛላት ኢትዮጵያን ከፍ ሊያደርግ እንደኳተነ መቅደላ ላይ ባሩድ ተጎንጭቶ አለፈ። ያለፈው ግን ስጋው ነው። መንፈሱና ራዕዩ ዛሬም አላለፈም፣ ነገም አያልፍም፣ አይጠፋም። የቴዎድሮስ አደራ፣ የቴዎድሮስ ራዕይ ዛሬም ሕዝቡን ይቀሰቅሰዋል፣ በእልህ ያስነሳዋል፣ ቴዎድሮስ የማይተኛ መሪ ነበርና፡፡

በአፄ ሰይፈ አርእድ ዘመነ መንግሥት እንደተመሰረተች የሚነገርላት ቀደምቷ ከተማ ጥንተ አመሰራረቷም በኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ መሬት ላይ ነበር ይባላል። ለረጅም ዘመናትም የባላባቶች መቀመጫ ነበረች፡፡ መኳንንቱና መሳፍንቱ፣ ዝናብ ያከበራቸው የሚባሉ ባላበቶች መቀመጫ ሆነች። ጀግኖች፣ ደጎች፣ አይደፈሬዎች ኖሩባት፣ ተወለዱባት፣ ተወልደው በክብር አደጉባት፡፡

ይህች ታሪካዊት ከተማ ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ፣ ለጦር አበጋዞችና ለሊቃውንቱ ተመራጭ ኾነች፡፡ መልካሙ አየሯ ለመልካሙ ሕዝብ ምቹ ነበረና እየተወደደች መጣች። ዘመን ዘመንን እየተካ ሲሄድ ከተማዋም እየሰፋች ሄደች። ንጉሡ ቴወድሮስ መቀመጫው ካደረጋት በኋላ ዘመናዊነትን ጀመረች። ይህች ኢየሱስ ክርስቶስ ግርማ መለኮቱን በገለጠበት ተራራ ሥም የተሰየመችው ደብረታቦር በተቀደሰው ተራራ ስም ፀናች። ጥንታዊቷ ከተማ የባህል፣ የሃይማኖትና የታሪክ መገኛ ናት። ቀዳሚው ኢንዱስትሪ መንደር የተገነባባት ቀዳሚት ናት ደብረታቦር። የነገሥታት ስጦታዎች፣ ቅርሶች፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የመስህብ ቦታዎች መገኛም ናት።

ደብረታቦር ስትነሳ አብያተክርስቲያኖቿ ይነሳሉ። አብያተክርስትያናቱ ሲነሱም ከተማዋ ትነሳለች። መሠረቷን የጣለችበት ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ቀድሞ ይነሳል። ይህ በጥበብ ተሠርቶ በጥበብ የኖረ ቤተመቅደስ በኢትዮጵያ ብቸኛው የተክሌ አቋቋም ዝማሜ ማስመስከሪያ ዩኒቨርስቲ መገናኛ ነው፡፡ የተክሌ አቋቋም ዝማሜ ቢዘያች ከተማ እንደ ዥረት ይፈስሳል፣ ጥበብ ያረሰርሳል፡፡ ጠቢባኑ የተክሌን አቋቋም ዝማሜ በደቀመዛሙርቱ ላይ ይዘራሉ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም መልካም ፍሬ ያፈራሉ፣ ከወተትና ማር የበለጠ የምትጣፍጠውን ጥበብ ይጠጣሉ፡፡ ጠጥተውም ይረካሉ፡፡

በዚህች ከተማ የነገሥታት የስጦታ እቃዎች ቅርሶችም ይገኙበታል። ሰመርነሃ የተሰኘው የአፄ ዩሐንስ አራተኛ ቤተ መንግሥትም በዚህቺው ከተማ ይገኛል። አፄ ዩሐንስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው አገራቸውን እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ ደብረ ታቦር አሁን ሰመርነሃ ከተባለው ቦታ ደረሱ። ቦታውንም ስለ ወደዱት ስሙን ሰመርነሃ ሲሉ ሰየሙት። ቃሉ የግእዝ ነው። ትርጓሜዉም ወደድናት ማለት ነው ይባላል። የተወደደችውን ከተማ እንድትወደድ የሚያደርጋት ብዙ ነገር አላትና። በወረሃ ጥር ደብረታቦር ታቦታቱን እያነገሠች እርሷም ትነግሳለች። ወረሃ ጥር የደብረታቦር መሞሸሪያ ነው። ውብ ኢትዮጵያዊት ሙሽራ። ያልጎደፈች፣ ያላደፈች፣ መልካም ሙሽራ።

ቀደም ባለዘው ዘመን የእግዚአብሔር መላዕክ የሚመራቸው ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ። እነዚያ ወንድማማቾች አምላካቸውን በልባቸው ይጠብቁታል። አብዝተው ያመሰግኑታል። እየፈሩ ይገዙለታል። እርሱም አብዝቶ ይወዳቸዋል። ይጠብቃቸዋል። ልመናና ምሕላቸውን ይሰማቸዋል፡፡ ለእነዚህ ቅዱሳን ወንድማማቾች የእግዚአብሔር መላዕክ ሁለት ፅላት ሰጣቸው። ፅላተ ፅዮንና ፅላተ ማርያምን። በፍርሃትና በምስጋና ተቀበሉት፡፡ በመንገዳቸው ሁሉ ይጠብቃቸውና ይመራቸው ነበር። ወደ መልካሙ ምድር እስኪደርሱ ድረስ ከመንገዳቸው እየቀደመ ይራቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በጥበቡ ይከተላቸው ነበር፡፡ በእግዚአብሔር መላዕክ እየተመሩ በደብረታቦር ደረሱ። ያም ሥፍራ ከመላዕኩ የተሰጣቸውን ቅዱስ ጽላት ያስቀምጡበት ዘንድ የተመረጠ ነበር፡፡ ጽላቶቹ ለዘላለም በዚያ አርፈው፣ ምድርን ይባርኳት ዘንድ ተፈቅዷልና፡፡ በዚያውም በአንደኛው ሥፍራ ቤተመቅደስ አንፀው አንደኛውን ፅላት እንዲያሳርፉ አዘዛቸው። ቤተ መቅደስም ሠሩ። ታቦተ ማርያምን አስገቡ። አንድ ዓመት ከአራት ወራትም ቆዩ። ሌላ ቤተመቅደስ እንዲሰሩ ታዘዙ። ሠሩም። ታቦተ ፅዮንን አሳረፉ። ስያሜያቸውንም አስቀድማ ያረፈችውን መንበረ ብርሃን እናቲቱ ማርያም። ተከትላ ያረፈችውን መንበረ ንግሥት ልጅቱ ማርያም አሏቸው።

ልጅቱና እናቲቱ ማርያም የሚባሉ ታቦታት የሉም። ታዲያ ስያሜው ከዬት መጣ ካሉ ግን አመሠራረታቸው ፊትና ኋላ ስለነበር የቀደመችውን እናቲቱ የዘገየችውን ደግሞ ልጅቱ አሏቸው። ስያሜያቸውንም ይህንኑ ለማመላከት ነው። በዚሁ ስያሜም ዘለቁ። ሌላ ዘመን መጣ። በመንበረ ንግሥት ልጅቱ ማርያም ቤተመቅደስ ውስጥ ተጨማሪ ፅላት ገባ። ይሄም ታቦተ መርቆሬዮስ ነው። መርቆሬዮስ ለዚያች ከተማ ሌላ በረከት ይዞ መጣ። ታላቋ ከተማ ከበረከት ላይ በረከት ተጨመረላት፣ ጸጋና ተድላ በዛላት፣ ቅዱስ መንፈስ አጎናጸፋት፣ በላይዋ ረበበባት፡፡

በወረሃ ጥር በ25ኛው ቀን አጅባር ትጨነቃለች፣ ደብረታቦር በደስታ ትዘላለች፣ ሊቃውንቱ ይዘምራሉ፣ ያሸበሽባሉ፣ ያጨበጭባሉ፣ ፈረሰኞቹ ሽምጥ ይጋልባሉ። ጀግንነታቸውን ያሳያሉ። በዚያች ምድር የሚሆነውን ለማዬት የሄደው ሁሉ በእግሩ ጫፍ እየቆሞ በጉጉት ይመለከታል። በእግሩ ጫፍ ሆኖም ማዬት ያልቻ ረጅም ዛፍ እየመረጠ እየተሰቀለ ያያል። ያን የመሰለ ውብ ዝማሬ፣ ዕፁብ የሆነ ጉግሥ ማሳለፍ አይፈልግምና። ያን ሳያይ ቀረ ማለት ነብሱ ደስታን ስትሻ ከልክሏታል እንደማለት ነው።

በጥር 24 ቀን በመንበረ ንግሥት ልጅቱ ማርያም የሚገኘው መርቆሬዎስ ከመንበሩ ወጥቶ ወደ አጅባር ይወርዳል። አጅባር በእርግብ አምሳል መላዕክት መጥተው እንደሰፈሩበት ሁሉ ነጫጭ የለበሱ ምዕምናን ያለብሷታል። ምድሪቷን ያስውቧታል። የመርቆሬዮስ ዓመታዊ በዓል በደብረታቦር ደማቁ የጥምቀት በዓል ነው ይባላል። ይህ በዓል በተሸለሙ ፈረሶች ወኔ በሚተናነቃቸው ጋላቢዎች ደምቆ ይውላል። በዓሉ በፈረስ እየታጀበ እፅብ እያስባለ መከበር ከጀመረ ረዘም ያሉ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ለዚህ ድንቅ በዓል ቀደም ብሎ ዝግጅት ይደረግለታል፡፡

ቀኑ ሲደርስ የተንጣለለው ሜዳ ነጭ መብሩቅ የለበሰ ይመስላል፡፡ የበዓለ መርቆሬዎስ አጅባርን ያዬ ሁሉ ነገሥታቱ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው ሠራዊታቸውን ያንቀሳቅሱ ይመስላል። ጦርና ጋሻው በላይ የሚደረገው የፈረሰኛ ልብስ ሁሉ የቀደመውን ዘመን መልሶ ያሳያል። ሽምጥ ግልቢያው ሲጀመር የሀገሬው ኃያል ሠራዊት ጠላትን ድባቅ እየመታ ያለ ይመስላል። የጠላትን ሰፈር ረግጦ፣ ግዳይ ጥሎ፣ ምርኮኛ ሰብስቦ፣ ድል ተቀዳጅቶ የድሉን ብሥራት ለንጉሡ ለማሳዬት እሽቅድምድም የሚገጥምም ይመስላል፡፡ ትይንቱ ልዩ ነው። የበረታው ሲማታ የደከመው ሲመታ ሲታይ አጀብ ያሰኛል። የሀገሬውን ፈረሰኛ እያዩ መይሳው ከእነ ገብርዬና ከባለሟሉቹ ጋር ሲያደርግ የነበረው ሁሉ በትዝታ ይመጣል። ያን ዘመን ያዩት ይመስላል።

አባ ታጠቅ በቁጣና በግርማ ጠላቱን ሁሉ እያመሰ፣ ወደ ፊት ብቻ እየገሰገሰ፣ ጠላትን ሲያስጨንቅበት፣ ወዳጅን በደስታ ሲያዘልልበት የነበረው ያ ዘመን ድቅን ይላል፡፡ ፈረስ ለነገሥታቱ፣ ፈረስ ለመኳንንቱና ለመሳፍንቱ፣ ፈረስ ለጦር አበጋዞች፣ ለጀግና ተዋጊዎች፣ ፈረስ ለሀገር አጽኚ ደፋሮች ልዩ ጉዳይ ነበረው፡፡ በፈረስ ሽምጥ ጋልበው፣ በጦርና በጎራዴ ተዋግተው፣ በጋሻ መክተው ሀገር አጽንተዋል፡፡ ድንበር አስከብረዋልና፡፡

ታቦተ መርቆሬዎስ ከመንበሩ ወጥቶ በታላቅ ክብር በደንኳኑ ያርፋል። ፈረስ ጉግሱ ሳይደራ፣ ሰውና መላዕክት፣ ሰውና እግዚአብሔር ሳይደሰቱ ታቦቱ አይነሳም። ፈረሰኛው መርቆሪዮስን በፈረስ ለማስደሰት የወደደው የሀገሬው ሰው ፈረሱን እየሸለመ፣ ዘንጉን እያመቻቸ በጠዋት ይመጣል። አጅባርን ያስጨንቃታል። አጅባር ሜዳ አብሮ ሽምጥ የሚጋልብ ይመስላል። ያን ትዕይንት ያዬ ሁሉ መንፈሱ ትታደሳለች፣ ሀሴትም ታደርጋለች።

ጉግሡ ሲጠናቀቅ አስቀድሞ የሰበሰባቸውን ታቦት ይከባሉ። ፈረሰኛው በፈረስ፣ እግረኛው በሆታና በልልታ ያጅቡታል። አብዝተው እያመሰገኑ ወደ ማደሪያው ይመልሱታል። ዲያቆናቱ ሰማያዊ የሚመስል ዝማሬ ያደርጋሉ። ከበሮው ይቆረቆራል። ፅሕናው ይፀነፀናል፣ ወረብ ይወረባል። ዝማሬ ይደረሳል። ምድር ትደሰታለች። ሰማይ መልካሙን ትመለከታለች። ምን አልባትም ከኢትዮጵያ ውጭ እንዲህ አይነት ነገር የሚገኝ አይመሰልም። አለባበሱ፣ አጨፋፈሩ ሁሉም ባሕላዊ ነው። በበዓለ መርቆርዮስ የበዙ ፈረሰኞች ፈረሶቻውን ሸልመው ይታደሙበታል፡፡ የበጌ ምድር ጀግኖች የቀደመውን ዘመን ያሳዩበታል፡፡ ሀገር ለማጽናት ቃል ኪዳን ያስሩበታል፡፡ ለሀገራቸው ታማኝነታቸውን ይገልጹበታል፡፡

አጅባር ስትጨነቅ፣ ደብረ ታቦር በደስታ ስትዘል ጀንበር ታዘቀዝቃለች፣ እልልታውና ዝማሬው ከዳር ዳር ይሰማል፡፡ ጎበዛዝቱ፣ ወይዛዝርቱና ሊቃውንቱ ሰብሳቢያቸውን ታቦት ወደማደሪያው ሳያስገቡ አይለያዩም። ጨዋታው፣ እልልታው ሁሉም ልዩ ነው።

ኢትዮጵያን አብዝቶ ላያት ሁሉ አንቺስ ድንቅ ነሽ፣ እንከንም የለሽ ማለቱ አይቀርም። የሰማይን በምድር የምትሠራ፣ የፈጣሪዋን ስም አብዝታ የምትጠራ፣ በማንነቷ የምትኮራ፣ የምድርን ችግርና ፈተና የማትፈራ፣ በመልካም ምድር መልካም ፍሬ የምታፈራ፣ በጠላቶቿ ፈጽማ የትፈራ፣ ለጨነቁት ደርሳ የምታኮራ ኢትዮጵያ ናት። የተወደደውን ሁሉ ታደርጋለች። የተጣለውን ሁሉ ታስወግዳለች። የተጠላውን ሁሉ ትጠላላች፣ በምድሯ እንዳይደረግ ታወግዛለች፡፡ በጉያዋ የያዘቻቸው ሁሉ እፁቦች ናቸው። እነሆ ዓለም ይፈልጋታል። እንዲያገኛትና የውስጧን እንዲወስድ ሁሉ ይሻል። ዳሩ ግን ጠባቂዋ ሚስጥር፣ አፈጣጠሯ ዥንጉርጉር ነውና አይቻላቸውም። ስለ ኢትዮጵያ መልካም ልብ ያላቸው ያደንቃሉ። ክፍሉ ልብ ያላቸውም ይወድቃሉ። የማይሸነፈውን ይዛለችና የሚያሸንፋት የለም።

ደግነቱ ዘላለም የሚፈስስ እንጂ የማይነጥፈው የቤጌምድር ሰው ስሞት ብሎ እያጎረሰ፣ የራሱን አውልቆ እያለበሰ፣ ለሥጋ ረሃብ እያረሰ፣ ለመንፈስ ረሃብ እየቀደሰና እያስቀደሰ፣ ወገን ሲደፈር እየተኮሰ ሀገር በክብሯ እንድትፀና ያደርጋል። ሀገር ማጽናትን፣ በአንድነት መነሳትን፣ ለኢትዮጵያዊነት ሁሉንም መስጠትን በጌምድር ያውቅበታል፡፡ ለሠንደቁ ክብር፣ ለሀገሩ ፍቅር መተኪያ የሌላት ሕይዎቱን ይሰጣል፣ አጥንቱን ይከሰክሳል፣ ደሙንም ያፈስሳል፡፡

በዚህቺው ከተማ ሌላ ድንቅ ነገርም አለ። በደብረታቦር መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በቴዎድሮስ እጅ የተሠራ የደወል ቤት ይገኛል። የንጉሡ መኖሪያና የችሎት ሥፍራም በዚሁ ይገኛል። ደብረታቦር ብዙ ያላት ግን ጥቂትም ያልተባለላት። ዕልፍ ሀብት ያላት ጥቂትም ያልታየላት ናት ። ልዩ ነው እርሱስ ፈረሰኛው መርቆሬዎስ ሲነግሥ። በአጅባር ሜዳ ፈረስ ሲገሰግስ፣ ያን ያዬ ሁሉ የማይረሳ ትዝታ፣ ወሰን የሌለው እርካታ፣ ልክ የሌለው ደስታ ያገኝበታል። እነሆ በበዓለ መርቆርዮስ አጅባር እየተጨነቀች፣ ደብረታቦርም በደስታ እየዘለለች ነው፡፡ ጎዳናዎቿ ነጫጭ በለበሱ ምዕምናን ተውበዋል፣ ሁሉም ድንቅ ኾኗል፡፡

እንኳን ለመርቆሬዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ።

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጅግጅጋ ገቡ፡፡
Next articleየአማራ ክልል በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ አደረገ።