
ባሕር ዳር፡ ጥር 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አነሳሽነት በመካከለኛ የአመራር ደረጃ የሚገኙ ተተኪ ሴት አመራሮችን ለማፍራት የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ስልጠና በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ እየተሰጠ ነው፡፡
በስልጠናው ከሁሉም ክልሎች፣ ከመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም ከሲቪል ማኅበራት የተውጣጡ 60 በመካከለኛ አመራርነት ደረጃ ያሉ ሴቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በስልጠናው መክፈቻ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማሳካት የሴቶች ተሳትፎን ማሳደግ ወሳኝ ሚና አለው።
በልማት ፣ በሰላምና ደኅንነት፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃና በተቋማት ግንባታ እንዲሁም አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፖሊሲና ፕሮግራሞች ላይ የሚሳተፉ ሴቶች እንዲበዙ መስራት ይኖርብል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመረው ድህነትን የማጥፋትና ሰላምን የማረጋገጥ ጥረት እውን እንዲሆን ብቁ የሴት አመራሮችን ማፍራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ለመካከለኛ ሴት አመራሮች የመሪነት ስልጠና እንዲሰጥ ሃሳብ ያመነጩት በሴቶች ችሎታ ላይ ያላቸውን ሙሉ መተማመን መሰረት አድርገው መሆኑንም ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል።
“በቂ ሴት አመራሮችን ከታች ጀምሮ ማብቃት ካልቻልን በኛ የተከፈተው በር ከእኛ በኋላ ሊዘጋ ይችላል” በማለት የስልጠናውን አስፈላጊነት ተናግረዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በቆይታቸው የሚያገኙትን የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና በመጠቀም በሚፈልጉት የመሪነት ደረጃ ላይ ለመድረስ እንዲተጉም ፕሬዝዳንቷ መክረዋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ዑሙድ ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት አካታች የሆኑ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በስልጠናው መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከግሉ ሴክተር የመጡ ሴቶች እንዲሳተፉ መደረጉን ደግሞ በማሳያነት አንስተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ጉዳይ የኢትዮጵያ ተወካይ ሌቲ ችዋራ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሴቶችን የአመራርነትና የውሳኔ ሰጭነት ሚና ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያደንቁ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቀጣይ የኢትዮጵያ መንግስት የሴቶችን የአመራር ሰጪነት ሚና ለማሳደግ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ በአጋርነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የአመራርነት ስልጠናው ለ10 ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ በዋናነት የአመራርነት ክህሎት፣ ሴቶችና አመራርነት በሚሉ ሌሎች ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሏል፡፡ ዘገባው የኢዜአ ነው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/