
ባሕር ዳር፡ ጥር 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) 35ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ በኢትዮጵያ መዲና መካሄድ የአፍሪካውያንን አንድነትና ወንድማማችነት ያረጋገጠ ነው ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ። የአፍሪካውያን አንድነት ለሀገራዊና አህጉራዊ ጠላቶች ትልቅ መልዕክት አስተላልፏል።
ዶክተር ቢቂላ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በኢትዮጵያ መዲና መካሄድ የአፍሪካውያን አንድነትና ወንድማማችነት የሚያጠናከርና ለውጭ ኃይሎች ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈ ነው።
ሀገር በማዳን ዘመቻ መንግሥት ጦርነት ውስጥ በገባበት ጊዜ የኢትዮጵያ ጠላቶች ከውስጥና ከውጪ ተደራጅተው በሚዲያ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ መስክ ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ አካሂደዋል።
ሚዲያቸውን በመጠቀም ከወራት በፊት ኢትዮጵያ ልትበተን ነው፤ የውጭ ሀገር ዜጎች አፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ መጠነ ሰፊ የተዛባመረጃ አሰራጭተዋል ብለዋል። ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን የልማትና የዲፕሎማሲ ሥራዎቻቸውን አቋርጠው እንዲወጡም ጥረት ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በአንድነት በመቆም በከፈሉት መስዋእትነት ሀገራዊና አህጉራዊ ጦርነቱን በሚገባ መቀልበስ ተችሏል ያሉት ዶክተር ቢቂላ፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት ያጣችውን ንብረት ወደ መገንባት እየተጓዘች ትገኛለች ብለዋል። ድሉ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ መዲና እንዲካሄድ በማስቻሉ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አህጉር ለውስጥና ለውጭ ጠላት ትልቅ መልዕክት አስተላልፏል ብለዋል።
የአፍሪካውያን አንድነትና ወንድማማችነትም የጥንካሬ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
እንደ ዶክተር ቢቂላ ገለጻ፤ ይህ ሁሉ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ በተከፈተበት ወቅት አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ድምፃቸውን በማሰማት ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው አሳይተዋል። ኢትዮጵያ የገጠማትን የውስጥ ችግር በራሷ አቅም መፍታት እንዳለባት ያሰሙት ድምፅም በተዘዋዋሪ አፍሪካውያን የራስን ጉዳይ ያለማንም የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት መፍታት እንደሚችሉ ትልቅ ትርጉም ያለው መልዕክት አስተላልፈዋል ብለዋል።
አፍሪካውያንና ኢትዮጵያውያን በከፈሉት መስዋእትነት የኢትዮጵያ እውነታ ለዓለም ማኅበረሰብ ተገልጧል። በኢትዮጵያ የሰላምና የጸጥታ ችግር አለመኖሩ በአፍሪካ ኅብረት ተቀባይነት አገኝቶ 35ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ መወሰኑ ለዚህ ትልቁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል። ድሉ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን ድል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ጥንካሬውን ለማስቀጠል የውጭ ጣልቃገብነትን በመቃወም የአፍሪካውያንን አንድነት ለማጠናክር የጀመረውን ፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ ለማጠናከር ይሠራል ያሉት ዶክተር ቢቂላ፤ ለወደፊት አፍሪካዊ አንድነትን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ትስስሮች ለማጠናከር እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።