ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተቻለ ፍጥነት ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሀገራቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ መምከሩ ተገለጸ፡፡

209
ባሕር ዳር፡ ጥር 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ እና ከመንግስት የሥራ ኀላፊዎችና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የተውጣጣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርጓል። የልዑካን ቡድኑ የጉዞ ዓላማ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ስለሚጠናከርበት እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ወገኖች የአጭር ጊዜና ዘላቂ መፍትሔዎች ስለሚያገኙበት ሁኔታ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ለመምከር ነው፡፡
ቡድኑ ባለፉት አራት ቀናት በነበረው ቆይታ በሪያድ ከኢትዮጵያ ኮሙኒቲ አመራሮች እና አባላት፣ ከሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር የተወያየ ሲሆን ከሳዑዲ መንግስት በኩል ደግሞ ከሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል አብዱል አዚዝ ቢን ሳዑድ ቢን ናየፍ፣ ከሳዉዲ ሮያል ፍርድ ቤት አማካሪ እና የንጉስ ሰልማን የሰብዓዊ እርዳታ ማዕከል የበላይ ተቆጣጣሪ ከሆኑት ከዶክተር ቢን አብዱልአዚዝ አል ራቢህ፣ ከእስላማዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አልዱልላቲፍ አልዱልአዚዝ አል-ሼይክ፣ ከፋይናንስ ሚስትር ሞሃመድ ቢን አብዱላህ አልጀዳን እንዲሁም ከሳዉዲ የልማት ፈንድ የኦፕሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከሆኑት ከኢንጂነር ፈይሰል መሀመድ አል-ቃህታኒ ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አያያዝ ስለሚሻሻልበት፣ የመኖሪያ ፈቃዳቸው የተቃጠለና የተለያዩ ቅጣቶች የሚጠብቋቸው ነገር ግን በራሳቸው ገንዘብ ተሳፍረው ሀገራቸው መግባት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ቅጣት ተነስቶላቸውና ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ሀገራቸው መመለስ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች፣ ፈቃድ እያላቸው የተለያየ ወከባ ይደርስብናል የሚል ስጋት ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ስለሚሰማ ይኸው ሁኔታ ስለሚሻሻልበት መክረዋል፡፡
እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተቻለ ፍጥነት ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሀገራቸው በሚመለሱበት እና ይህንን ችግር በመፍታት የሁለቱን ሀገሮች ስትራቴጂካዊ ትብብርና ግንኙነት ወደላቀ አጋርነት ማሸጋገር በሚቻልበት አግባብ ላይም ጠቃሚ እንዲሁም ለቀጣይ መተማመንና ትብብር አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መገኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ለቅድመዝግጅት እንዲያግዝ በኢትዮጵያ በኩል ቅድሚያ የሚሰጣቸዉን ተግባራት የመለየት ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
የሉዑካን ቡድኑ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ በሳዑዲ አረቢያ የኢፌዲሪ ባለ ሙሉስልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ እንዲሁም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር ዶክተር ጀይላን ከድር የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እና ከስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት እንዲሁም ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተውጣጡ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተ ነው።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
Previous articleግዳጃቸውን በጀግንነት ለተወጡ 150 የምዕራብ ዕዛ አባላት እና አሃዶች የሜዳይ ሽልማት ተበረከተ።
Next article“በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን የአማራና የአፋር ክልሎች መልሶ ለማቋቋም ኹሉም ክልሎች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል”የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን