የአፄ ቴዎድሮስ መናገሻ የሆነችውን ደረስጌ ማርያምን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

538

ደባርቅ፡ ጥር 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በታሪካዊቷ መንበረ መንግሥት ፀርሓ ፅዮን ደረስጌ ማርያም ቤተ ክርስቲያን የአሥተርዮ ማርያም ዓመታዊ በዓል በድምቀት ተከብሯል፡፡ በበዓሉ የፌደራል፣ የክልልና የዞን የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በበዓሉ ላይ ተገኝቶ የበዓሉን ታዳሚዎችም አነጋግሯል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ካሣልጅ መልካም የደረስጌ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከ5 መቶ ዓመታት በላይ የቆየች፤ በዘመነ መሣፍንት የሰሜኑና የትግራይ ገዥ የነበሩት ደጃዝማች ውቤ ለንግሥና በአማረና በተዋበ መንገድ ያሳደሷት፤ አፄ ቴዎድሮስ ደጃች ውቤን ቧሂት ከምትባል ቦታ አሸንፎ የካቲት 11 ቀን 1847 ዓ.ም “አፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው ዘውድ የጫኑባት ታሪካዊት ቦታ መሆኗን አብራርተዋል፡፡መምህር ካሣልጅ አፄ ቴዎድሮስ ንግሥናቸውን በዚህ ያደረጉበት ምክንያት ለንግሥና የሚያስፈልጋቸው ጳጳስ፣ ዘውድና ሌሎች ነገሮች በቤተ ክርስቲያኗ በመኖራቸው ነው ብለዋል፡፡

ይህችን ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን እስከ ቅርሶቿ ለትውልድ እንዲተላለፍ የደብሩ የሃይማኖት አባቶችና ማኅበረሰቡ የቻለውን እያደረገ ከዚህ አድርሷል ያሉት መምህር ካሣልጅ መንግሥት ለአካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራና ማኅበረሰቡን ሊያግዝ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ማኅበረሰቡን ለማገዝና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በአግባቡ ለመጠቀም በአካባቢው ያለውን የመንገድ ችግር መፍታት ለማኅበረሰቡ ትልቁ እገዛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው በበዓሉ ላይ የተገኙት ጃናሞራን ወክለው የፌዴራል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የጃን ሕብረት ፕሬዝዳንት ባያብል ሙላቴ ጃናሞራ ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የደረስጌ ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በርካታ አስደማሚ የሆኑ የቅርሶች ባለቤት መሆኑን አንስተዋል፡፡

አቶ ባያብል የኢትዮጵያ አንድነት መሐንዲስ አፄ ቴዎድሮስ የነገሡባት ደረስጌ ማርያም ኢትዮጵያዊያን ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከባርነት ወደ ነፃነት፤ ከመከፋፈል ወደ አንድነት የተመለሱበት ዘመነ መሣፍንት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቀበረባት ጥንታዊ፣ ታሪካዊና መንፈሳዊ ቦታ መሆኗን ነው የተናገሩት፡፡

ይህን ታሪክ የያዘችው ደረስጌ ማርያም ቤተክርስቲያን በሚገባት ልክ አልታወቀችም ያሉት አቶ ባያብል ይህ በመሆኑም ማኅበረሰቡ ከቱሪዝም ማግኘት የሚገባውን ጥቅም አላገኘም ብለዋል፡፡

በዞኑ ያሉ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችንና ትውፊቶችን በማስተዋወቅ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ወደ አካባቢው መጥተው ደረስጌ ማርያምን በመጎብኘት የአንድነት ምንጩን እንዲረዱና የአካባቢው ማኅበረሰብም ከሚመጣው ጎብኝ ተጠቃሚ እንዲሆን የተለያዩ ሥራዎች እንደተጀመሩ ጠቁመዋል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ አሥራት ክብረት የትግራይ ወራሪ ቡድን በከፈተው ጦርነት የዞኑ ሕብረተሰብ ተጎጅ ሆኖ መቆየቱን አውስተዋል፡፡መምሪያው በዞኑ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ፣ ከክልሉ ቱሪዝም ቢሮ በተገኘ በጀት ሙዚየም በመገንባትና ቅርሶችን በአግባቡ በማስቀመጥ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ አሥራት በጦርነቱና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሙሉ በሙሉ ቆሞ የነበረው የቱሪዝም አገልግሎት በዞኑ በመጣው አንፃራዊ ሰላም የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችቹ ለጎብኝዎች ክፍት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

ጎብኝዎች ወደ ሰሜን ጎንደር መጥተው የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ የብዙ ጥንታዊ ቅርስ ባለቤትና የአፄ ቴዎድሮስ መናገሻ የሆነችውን ደረስጌ ማርያም ቤተክርስቲያንን፣ የአባ ማርቆስአቡነ አረጋዊ የዋሻ ገዳምን፣ ደብረ ይባቤ ሠረባር ውቅር አብያተ ክርስቲያንን፣ አብሃን ፃድቃን ገብርኤል ገዳምን፣ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዓመታዊ ክብረ በዓል የሚፈፀምበትን ሰለምጌንና መሰል ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦች መጎብኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ:–አድኖ ማርቆስ–

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ውድመት የደረሰባቸው ሁሉም ትምህርት ቤቶች ስራ ጀምረዋል” የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር
Next article“ለትርፍራፊ ጁንታ የሰጠነው የመጨረሻ ሥራ ራሳቸውን ኦዲት እንዲያደርጉ ነው” የአፋር ክልል ርእሰ መሥተዳድር አወል አርባ