ʺከአምሳለ አንበሳው እስቴ ዴንሳ ተራራ ግርጌ”

547
ባሕር ዳር፡ ጥር 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በዚያ ጀግኖች በሚፈጠሩበት፣ ልበ ሙሉዎች በሚኖሩበት፣ ተኩሶ መሳት በማይታወቅበት አያሌ ነገሮች ሞልተዋል።
ከዘመን ዘመን እንደጠበቀ የሚኖር ጀግንነት፣ በመከራ የተፈተነ ጽኑ ኢትዮጵያዊነት፣ ጠላት የማይነጣጥለው አንድነት እስከ መቃብር የሚዘልቅ ታማኝነት፣ ቃል ኪዳን አክባሪነት፤ ክፉ ቀን ሲመጣ ዘራፍ ብለው ጠመንጃቸውን እያነሱ፣ ተመልከት ብለው እየተኮሱ፣ ጠላትን በአሻገር እየመለሱ፣ ምሽግ ተራምደው ምሽግ እያፈረሱ፣ አጥንት ከስክሰው ደም እያፈሰሱ ሀገር ያጸናሉ፣ ክብርን ያስጥብቃሉ፡፡
ሀገር ሰላም ሲሆን ቀዬው አማን ውሎ ሲያድር፣ ንጉሡ ከወንበሩ፣ ሠራዊቱ በድንበሩ በሰላም ውሎ በሰላም ሲያደር ደግሞ ወይኖ እና ኮሎን፣ ጀንበርና ዘገርን፣ ፈንዛና ይመርቀንን፣ ኳሊና ገድፍን ጀንበር ስትዘልቅ ጠምደው ሲያርሱ ውለው፣ ጀንበር ስትጠልቅ ፈትተው ነጭና ጥቁር ያመርታሉ፣ በሰፊ አውድማ ያፍሳሉ፣ ጎተራውን ይሞላሉ፣ የተራበውን ያጎርሳሉ፣ በላሞቻቸው ወተት የተጠማውን ያጠጣሉ፣ በቤታቸው ዙሪያ ገብ በመላው የንብ ቀፎ ማር እየቆረጡ በፍርንዱስ ያቀማጥላሉ፡
የደከመውን ያሳርፋሉ፣ የታረዘውን ያለብሳሉ፣ ፈጣሪ ለምድር ረዴትና በረከት፣ ፍቅርና አንድነት እንዲሰጥ በየገዳማቱና በየአድባራቱ አጥብቀው ይጸልያሉ፣ ምልጃና ጸሎት ያቀርባሉ።
ጀግንነት በሚያስፈልግበት ወቅት ልባቸው የማይሰጋ ጀግኖች፣ ጸሎት ሲያስፈልግ አንደበታቸው ከምስጋና ውጭ ሌላ የማያውቅ አባቶችና እናቶች፣ ማረስና ማፈስ ሲያስፈልግ አርሰው የማይደክሙ ገበሬዎች፣ ንግድም ሲያስፍልግ በረሃ የሚያቆራርጡ ገበያ አዋቂ ነጋዴዎች ሞልተዋል፡፡ ሁሉም አላቸው፡፡ በሁሉም ነው መገኛቸው፣ ግሩም ነው ጀግንነታቸው፣ ድንቅ ነው አንድነታቸው፣ እጹብ ነው ኢትዮጵያዊነታቸው፡፡
ʺበጀግኖቹ ሥፍራ ሰሜን በጌ ምድር፣
ወዳጅ ዘመድ እንጂ ጠላት ውሎ አያድር” እንደተባለ በሰሜን በጌምድር ወዳጅ እንጂ ጠላት ውሎ አያድርም፣ ጋራና ሸንተረሩ ለጠላት አያረማምድም፡፡ ምድሩ ለጠላት እሳት፣ ለወዳጅ ገነት ነው፡፡ በጀግንነት መላቅ፣ በበዓላት መድመቅም ይችሉበታል፡፡
ጀግንነት፣ ሃይማኖት፣ አንድነት፣ የጸና ኢትዮጵያዊነት በሞላበት በዚያ ሥፍራ በአምሳለ አንበሳ የተቀመጠ፣ ለበረከት ለቅድስና የተመረጠ፣ ሊቃውንት የሚፈልቁበት፣ ምስጢራት የሚመሰጠሩበት፣ ጥበብ የሚዘራበት፣ ቅዱሳን የሚኖሩበት፣ በረከት የማይታጣበት፣ ጠቢባን በጥበብ የሚመላለሱበት ውብ ሥፍራ አለ፡፡
በተኛ አንበሳ አምሳል ተፈጥሯል፣ በቅድስና ተከብሯል፣ በክብር ኖሯል፣ እልፍ ጠቢባንን ለኢትዮጵያ ሰጥቷል፡፡
ከተራራው ጫፍ ገዳመ ዮሐንስ፣ ከተራራው ግርጌ ደግሞ ታላቁ ደብር ኢየሱስ አሉበት፡፡ በተራራውና በተራራው ዙሪያ ምስጋና ይቀርብበታል፣ ቃለ እግዚአብሔር ይነገርበታል፣ ጥበብ ይፈልቅበታል፣ መጻሕፍት ይመረመሩበታል፡፡
ታላቁ ንጉሥ አድያም ሰገድ ኢያሱ በዚያ ሥፍራ ጉልት ነበራቸው፡፡ በዚያ የጉልት ሥፍራም 150 ባዝራዎች ያስረቡ ነበረ፡፡ ባዝራዎቹን የሚያስረቡትም መኳንንቱና መሳፍንቱ፣ የጦር አበጋዞቻቸው፣ የእልፍኝ አስከልካዮቻቸው፣ ቆራጥ ተዋጊዎቻቸው ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበት እንዲኖራቸው ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ሀገር የሚቀናው፣ የሚነገደው፣ ዘመቻ የሚሄደው በፈረስ ነበርና፡፡
ታላቁ ንጉሥ ባዝራዎቹን የሚያረቡት በእስቴ ዴንሳ ተራራ ግረጌ በተንጣለለው ሜዳ ነበር፡፡ ያም ሥፍራ ነገሥታቱ የሚያርፉበት፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ የሚመክሩበት፣ የጦር አበጋዞች፣ ጦረኞች በጀግንነት የሚመላለሱበት፣ የፈረስ ጉግስ የሚለማመዱበት ነበር፡፡ በንጉሡ የሚረቡት ፈረሶች የእሰቴ ዴንሳ አጋም እንደ ጥላ ኾኗቸው የሚያርፉበትም ነበር፡፡ አድያም ሰገድ ኢያሱ አለፉ፡፡ በእርሳቸው ዙፋንም ነገሥታቱ እየተተኩ በመናገሻዋ ከተማ በጎንደር እየተቀመጡ ኢትዮጵያን ያስተዳድራሉ፡፡
ፍጻሜ መንግሥት እየተባሉ የሚታወቁት ዘመነ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ደረሰ፡፡ በዚያ ዘመን አቡነ ዮሳብ የሚባሉ ጳጳስ ነበሩ፡፡ የንጉሥ እንደራሴ የነበሩ ደጅ አዝማች ኃይሉ እሸቴ የሚሰኙ ጀግናና ሃይማኖተኛ ሰውም ነበሩ፡፡ እርሳቸውም ደብር መደበር፣ ታቦት ማክበር ይፈልጉ ነበርና ደብር ይደብሩ ዘንድ ወደዱ፡፡
ደጅ አዝማች ኃይሉ እሸቴ ግርማቸው የሚያስፈራ፣ መጡ ሲባል ገና የሚያስደነግጡ ነበሩ ይባላል፡፡ እኒያ ደጅ አዝማች በእሰቴ ዴንሳ ተራራ ደርሰው ደብር የት ላይ ልደብር ሲሉ አሰቡ፡፡ ፈጣሪያቸው ይገልጽላቸው ዘንድ ጸለዩ፡፡
በአምሳለ አንበሳ በተሠራው ተራራ አናት ላይ መናኔ መንግሥት እየተባሉ በሚታወቁት በጻዲቁ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የተመሠረተ የዮሐንስ ቤተክርስቲያን አለ፡፡ የመጥምቁ ዮሐንስ ደብር በተኛ አንበሳ አምሳል በተቀመጠው ተራራ አናት ላይ ያረፈ፣ አዕዋፋት በዝማሬ የሚጅያቡት፣ የዱር አራዊት የሚጠለሉበት፣ ቅዱሳን አበው በቅድስና የሚመላለሱበት ነው፡፡ እኒያ ደጅ አዝማች የፈጣሪያቸው ፈቃድ ኾኖ ደብር የሚደብሩበት ቦታ የት ይሆን ሲሉ አብዝተው ተጨነቁ፡፡ ዴንሳ ማለት የሚያምር፣ ዓይነ ግቡ፣ መልከመልካም፣ የሚያስደስት ነው ይላሉ አበው፡፡May be an image of 5 people and people standing
ደጅ አዝማች ኃይሉ እሸቴም መናኔ መንግሥት ጻዲቁ ዮሐንስ ባሠሩት የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን አጸድ ሥር ሱባኤ ያዙ፡፡ ሱባኤያቸውም ሠመረ፣ ፈጣሪያቸው ልመናቸውን ሰማ፡፡ በቅዱስ መንፈስም ነገራቸው፡፡ የሚሠራው ቤተክርስቲያን ታላላቅ ሊቃውንት የሚፈልቁበት፣ ሚስጥራት የሚመሰጠሩበት፣ ቅዱሳን የሚኖሩበት፣ እስከ ዘመነ ምጽዓት ድረስ የፈጣሪ ክብር የሚነገርበት፣ ጉባኤ የማይታጎልበት፣ እንደሚሆን ተነገራቸው፡፡ የእርሳቸው ስምም ደብሩ በጠራ ቁጥር ገንኖ ይኖራል ተባሉ፡፡
አበው ለደጅ አዝማቹ የተነገራቸውን ቃል ሲናገሩ ዙሪያውን በአጋም የተከበበ ዱር አለልህ፤ አጋሙን ቆርጠህ ስተገባ በመካከሉ አንድ የግራር ዛፍ ታገኛለህ፡፡ በዚያ የግራር ዛፍ ሥርም አርባ ዓመት ዘግቶ የኖረ ቅዱስ አባት አጽም ታገኛለህ፡፡ አጽሙንም በክብር በብረት ሳጥን አስቀምጥ፣ ብረቱንም በብር ለብጠው፣ ቀጥለህም በወርቅ ለብጠው፣ ከዚያም ግራሩን ቆርጠሕ ግራሩ ከነበረበት ላይ የቅዱሱን ሰው አጽም ቅበረው፡፡ በቀበርክበት ሥፍራም መንበሩን አስቀምጥ፡፡ ያም ሥፍራ የበረከት ቦታ ይኾናል ተባሉ፡፡ ደጅ አዝማች ኃይሉ እሸቴም የተባሉትን አደረጉ፡፡ ደብሩን ደበሩ፡፡
ይሕም ደብር ካልዕት እስክንድሪያ እንተ ይእቲ ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ነው፡፡
የሃይማኖት መናገሻ፣ የሊቃውን መዳረሻ ነው ይሉታል፡፡ እሰቴ መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን እየተባለ በብዙዎች ይታወቃል፡፡ ደጅ አዝማች ኃይሉ እሸቴ በ150ዎቹ ባዝራዎች ፋንታ ለደበሩ 150 ሊቃውንትን መደቡ፡፡ እርስትና ጉልትም ሰጡት፡፡
ሊቃውንት እየፈለቁበት፣ ጠቢባን እየተገኙበት፣ ምስጢር እየተመሰጠረበት ዘመናት ተሻገረ፡፡
የኢጣልያን ወረራም ደረሰ፡፡ ኢትዮጵያውን አርበኞችም ከጠላት ጋር መተናነቅ ጀመሩ፡፡ የሰሜን በጌ ምድር አርበኞችም በጀግንነት ጠላትን ያሰጡት ነበር፡፡ በጀግኖቹ አልበገር ባይነት የተበሳጨው የኢጣልያን ሠራዊትም ሕዝብ የሚመካባቸውን፣ አምልኮት የሚፈጽምባቸውን አድባራትና ገዳማት ያወድም ጀመር፡፡ በበጌምድር ጀግኖች የተበሳጨው ጣልያን ታለቁን ደብር ሊያፈርስ ተነሳ፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪና የድጓ መምሕር መላከ ሃይማኖት መምህር ሲሳይ አሰፋ እንደነገሩኝ በወረራው ዘመን በታላቁ ደብር የሚኖሩ አንድ የበቁ አባት ነበሩ፡፡ እኒያ አባትም ደብሩ ይቃጠላልና ቅዱሳት መጻሕፍትን፣ ታቦታትን እናሽሽ አሉ፡፡ አበውም የተባሉትን አድርገው ወደ ዋሻ ማርያም አቀኑ፡፡ የኢጣልያ ወራሪም ደብሩን አቃጠለው፡፡May be an image of 5 people, people standing and outdoors
በዚያ ደብር እንደ መንበር የሚያገለግል አንድ ከዝሆን ጥርስ የተሠራ መንበር ነበር፡፡ ይህም መንበር ታቦቱ የሚያርፍበት ነበር፡፡ ሊቃውንቱ እቃ አሽሽተው ወደ ዋሻ ማርያም ሲሄዱ ያን መንበር ረስተውት ነበር፡፡ የኢጣልያ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ ሲወጣ፣ ቀሳውስቱ ከዋሻ ወጥተው ወደ ቀደመው ተመለሱ፡፡
የጥምቀት ጊዜም ደረሰ፡፡ መንበሩን ሳይወጣ ቀርቶ በዚያው ተቃጥሎ ነበርና ታቦቱን የት እናሳርፍ አሉ፡፡ ወደ ሥፍራው እንውረድና ለጊዜው ድንጋይ አነባብረን በዚያ ላይ እናሳርፋለን አሉ፡፡ ወደ ሜዳውም ወረዱ፡፡ በዚያ በደረሱ ጊዜም ሰው ያልሰራው፣ ፈጣሪ በጥበቡ ያስቀመጠው ለመንበር የተመቸ ድንጋይ አገኙ፤ ፈጣሪ ድንቅ ነገርን አደረገልን ሲሉ ሀሴትን አደረጉ፣ አመሰገኑም፡፡ በዚያ ላይም ታቦቱን አሳረፉ፡፡ ይህ በፈጣሪ ፈቃድ የተቀመጠ የድንጋይ መንበርም እስከዛሬ ድረስ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡
በዚሕ ሥፍራ በጥር 25 ቀን ዓመታዊ የመርቆርዮስ በዓል ይከበርበታል፤ የእስቴ ዴንሳ ተራራ ግርጌ ትጨነቃለች፣ በደስታ ትዘላለች፣ ሀሴትን ታደርጋለች፣ አምቦሜዳ በሰው ትመላለች፣ ቀሳውስቱ፣ ዲያቆናቱ ምድራዊ በማይመስል ሕብረ ዝማሬ ምስጋና ያቀርባሉ፣ ያሸበሽባሉ፡፡ የጥናፋ፣ የፋርጣና እስቴ ፈረሰኞች ፈረሶቻቸውን ሸልመው፣ ወኔያቸውን ተላብሰው፣ መርቆሪዮስን ሊያነግሱ፣ በፈረስ ሊገሰግሱ፣ ሜዳውን በሽምጥ ሊያዳርሱ ይመጣሉ፡፡
አምሳለ አንበሳ የዴንሳ ተራራ ግርጌ በእልልታና በሆታ ይደምቃል፡፡ ተራራው ይጨነቃል፡፡ ጎበዛዝቱና ወይዛዝርቱ በሜዳው ይደምቁበታል፡፡
በዚያ ሲገኙ ዛሬም ንጉሠ ነገሥቱ፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ በተራራው ግርጌ በሚከበረው፣ እጅግ በሚደምቀው የንግሥ ቀን ተቀምጠው የሚታደሙበት ይመስላል፡፡ ፈረሰኞቹ በንጉሡ ፊት ልቀው ለመገኘት፣ ከንጉሡም ሽልማት ለማግኘት እንደሚፋጠኑ የጦር አበጋዞችና ጀግና ጦረኞች ይመስላሉ፡፡
በእሰቴ ዴንሳ ተራራ ግርጌ ሲገኙ የአድያም ሰገድ እያሱ ባዝራዎች የሚመጡ፣ በሜዳውም ያለ ከልካይ የሚፈረጥጡ፣ በደስታ የሚሸመጥጡ፣ አድያም ሰገድ እያሱም በዙፋናቸው ተቀምጠው ክብሩን የሚከታተሉ ይመስላል፡፡ መኳንንቱና መሳፍንቱም በንጉሡ ግራና ቀኝ ተቀምጠው በዓሉን የሚያደምቁት፣ መርቆርዮስን የሚከበክቡት ይመስላል ትእይንቱ ልዩ ነውና፡፡May be an image of 2 people and outdoors
እነሆ ጊዜው ደርሷል፣ መርቆርዮስ ወደ አምቦ ሜዳ ሊገሰግስ፣ የጥናፋ፣ የፋርጣና የእሰቴ ፈረሰኞች፣ ፈረሶቻቸውን አስጊጠው፣ በሕብረ ቀለም አንቆጥቁጠው ሊወርዱ፣ አምቦ ሜዳ በፈረሶች፣ በጀግኖች፣ በሊቃውንቱ፣ በዲያቆናቱ፣ በወይዛዝርቱና በጎበዛዝቱ ሊሞላ ነው፡፡
ድንቅ ነገር ሊደረግ ነው፡፡
ካልዕት እስክንድሪያ ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን የብራና መጻሕፍት፣ ነገሥታቱ ያበረከቷቸው ታሪካዊ መንፈሳዊ ስጦታዎች፣ በብር የተለበጡ፣ በወርቅ ያጌጡ ንዋየ ቅድሳትና ሌሎች ቅርሶችን አቅፎ ይዟል፡፡ በዚያ ሥፍራ የአድያም ሰገድ እያሱ ስም ያረፈበት ደወልም ይገኛል፡፡
ይሂዱ በአምሳለ አንበሳው እስቴ ዴንሳ ተራራ ግርጌ በበዓለ መርቆርዮስ ድንቅ ነገርን ይመልከቱ፡፡ በጀግና ፈረሰኞች ትንንቅ፣ በሊቃውንቱ ድንቅ ዝማሬ፣ በበዓሉ ድምቀት ይደመሙ፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
Previous article“የአምባሳደሮች ሹመት ሙያዊ ብቃት እና ሀገራዊ ለውጥን መሰረት ያደረገ ነው” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
Next article“በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ውድመት የደረሰባቸው ሁሉም ትምህርት ቤቶች ስራ ጀምረዋል” የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር