ሀገሪቱ ካለችበት አንጻራዊ ሰላም ጋር ተያይዞ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ከተቀመጠለት የስድስት ወር ገደብ ቀድሞ ማንሳት አስፈላጊ ኾኖ መገኘቱን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

103
አዲስ አበባ፡ ጥር 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ኹነቶች የምታጌጥበት የጥር ወር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዓለም ደምቃ እንድትታይ በሚያደርግ መልኩ በዓላትን አክብራለች ብለዋል። በዓላቱ ከመንፈሳዊ ፋይዳቸው ባለፈ የኢትዮጵያን ሰላማዊ ሁኔታ ለዓለም ያሳየ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል። በወይብላ ማሪያም የተፈጠረውን ችግር መንግሥት እያጣራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤን በተመለከተ ዶክተር ለገሰ እንደገለጹት 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሄድ በመሆኑ ለጉባኤው ተገቢዉ ዝግጅት ተደርጓልም ብለዋል።
በጉባኤዉም ኢትዮጵያ የራሷን ችግሮች በራሷ እንደፈታች የምታሳይበት ይሆናልም ነው ያሉት፡፡ የጉባኤዉ ተሳታፊዎችም በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰናቸዉ አጋርነታቸዉን እንደሚያሳይም ጠቅስዋል።
በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ዉጭ የቱሪዝም መዳረሻ የሆኑ ከተሞች ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች በኢትዮጵያዊ እንግዳ አቀባበል ባህል እንግዶችን እንዲያስተናግዱ ጥሪ ቀርቧል።
በተጨማሪም ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ነጻ በወጡ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ ወደ ተሟላ እንቅስቃሴ መግባታቸዉን በመግለጫቸዉ አንስተዋል። በአማራ ክልል የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን እንደተፈታም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የመልሶ ግንባታዉም በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን የገለጹት ሚኒስትሩ በዘላቂነት የተፈናቀሉ ወገኖችን በማቋቋም በኩል በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።
ዶክተር ለገሰ በኦሮምያ፣ በደቡብ እና በሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ባጋጠመዉ የድርቅ አደጋ ዜጎች እንዳይሞቱ የዕለት ደራሽ ድጋፎች እየተደረጉ ነዉ ሲሉም ጠቅሰዋል።
በትግራይ ክልል ስላለዉ አሁናዊ ሁኔታ የተናገሩት ዶክተር ለገሰ ቱሉ ወደ ክልሉ ድጋፍ እንዲገባ እየተደረገ ነዉ ብለዋል፡፡ በአባላ የሚደረገዉ ጉዞ ግን የሽብር ቡድኑ በዚህ አካባቢ በከፈተዉ ትንኮሳ ምክንያት ተቋርጧልም ብለዋል፡፡
አሸባሪዉ ትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ እና በአፋር ክልሎች እያደረገ ያለዉ ትንኮሳ ወደ ትግራይ ሰብዓዊ እርዳታ አልደረሰም የሚለውን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ለመንዛት መሆኑን ገልጸዋል። በበራህሌ በኩልም ለማጥቃት የሞከሩ የሽብር ቡድኑ አባላት በአየር ኃይል ተደምስሷልም ሲሉ ጠቅሰዋል።
ሀገሪቱ ካለችበት አንጻራዊ ሰላም ጋር ተያይዞ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ከተቀመጠለት የስድስት ወር ገደብ ቀድሞ ማንሳት አስፈላጊ ኾኖ መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ እንዲነሳ የሚኒስትሮች ምክርቤት ዉሳኔ አስተላልፎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ኤልሳ ጉዑሽ-ከአዲስ አበባ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ። https://ameco.bankofabyssinia.com/
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተሳተፉበት የፌደራልና የክልል መንግሥታት የሕግ አስፈጻሚዎች ግንኙነት መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
Next article“የአምባሳደሮች ሹመት ሙያዊ ብቃት እና ሀገራዊ ለውጥን መሰረት ያደረገ ነው” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ