
ባሕር ዳር፡ ጥር 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ እንቁ የቱሪዝም ሃብት፣ እልፍ ታሪካዊ መዳረሻዎች፣ ቱባ ባህል እና ውብ መልከዓምድራዊ አቀማመጥ የታደለው የአማራ ክልል ቱሪዝም ላይ ሕይዎታቸውን የመሰረቱ ዜጎች እና አካባቢዎች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እስከ ሕግ ማስከበር ዘመቻው፤ ከሕልውና ትግሉ እስከ ውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ የቱሪዝም ዘርፉ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሳንካ ገጥሞት ቆይቷል፡፡
ልደትን በላልይበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ ጥርን በባሕር ዳር እና መሰል በዓላት ከፈጠሩት ምጣኔ ሃብታዊ እና የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት ባሻገር የክልሉን ገጽታ በበጎ ጎኑ በመገንባት በኩል ድርሻቸው የጎላ ነበር ተብሏል፡፡
ያለፉት ጊዜያት ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት የታለመላቸውን ምጣኔ ሃብታዊ እና የገጽታ ግንባታ ግብ አሳክተዋል ያለው የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ የቀጣይ ጊዜያት ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት መርኃ ግብርን ይፋ አድርጓል፡፡ በቀጣይ ወራት ቢሮው እያስተባበረ የሚከበሩ በርካታ በዓላት እንዳሉ የገለጹት የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን ናቸው፡፡
በቅርቡ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ በዓል፣ የአስተርዮ ማሪያም ንግሥ በተለያዩ አካባቢዎች እና የመርቆሪዮስ ንግሥ በደብረ ታቦር ይከበራሉ ብለዋል፡፡ በዓላቱ በስኬት እንዲከናወኑ ቢሮው እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ እንደገለጹት
• 82ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ከጥር 22/2014 ዓ.ም እስከ ጥር 23/2014 ዓ.ም ይከበራል፤
• ጥር 22/2014 ዓ.ም የፓናል ውይይት እና የመጽሐፍ ምረቃ ይከናወናሉ፡፡
• ጥር 23/2014 ዓ.ም ደግሞ ዋናው እና ልዩ የኾነው የፈረስ ትርዒት ይከበራል፡፡ በዓሉ የአካባቢው ቱባ ባህላዊ እና ታሪካዊ ኹነቶች ለሕዝብ በሰፊው እንዲተዋወቁ እድል ይፈጥራል ነው የተባለው፡፡
በቀጣይም የአስተርዮ ማሪያም ዓመታዊ የንግሥ በዓል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚከበር የገለጹት አቶ ኤርሚያስ በግሸን ደብረ ከርቤ እና በመርጡ ለማሪያም ሰፊ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ከጥር 24/2014 ዓ.ም እስከ ጥር 25/2014 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የመርቆሪዮስ ንግሥ በፈረስ ጉግስ ታጅቦ በደብረ ታቦር ከተማ በድምቀት ይከበራል ተብሏል፡፡ በዓላቱ በተለያዩ ችግሮች ተዳክሞ የቆየውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን ነው አቶ ኤርሚያስ የገለጹት፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን እና አንድነትን በማጠናከር በኩልም ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው ብለዋል፡፡
ያለፉት በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ድጋፍ ላደረጉ ወጣቶች፣ የፀጥታ ኃይሎች እና ሕዝቡ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ለቀጣይ ጊዜያት በዓላትም ተመሳሳይ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችም ቀሪ ጊዜያቸውን እነዚህን በዓላት ላይ በመታደም እና በማድመቅ እንዲያሳልፉ ምክትል ኀላፊው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ። https://ameco.bankofabyssinia.com/