“የሐይቅ ዳሩ ባለ ግርማ የባሕር ዳር ምልክት”

169
ባሕር ዳር፡ ጥር 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በመዓልትና በሌሊት አመሥጋኝ የማይታጣበት፣ ሕዝብ የሚሰባሰብበት፣ ምልጃና ጸሎት በሰርክ የሚደርስበት የፈጣሪ ስም ዘወትር የሚጠራበት፣ ከመንገድ የመጡ፣ መንገድም ያሰቡ፣ በዙሪያው ያለፉ ያገደሙ ኹሉ ከደጁ ዝቅ ብለው ምህረት የሚለምኑበት፣ ነብስን በሐሴት ይዞ የሚጠፋ የካህናት ዝማሬና ምሥጋና ዘወትር የሚሰማበት፣ ያማረ፣ የተዋበ። ከጣና ዳር፣ ከገደማቱ በአሻገር በክብር ይኖራል። በማዕበል እየተገፋ የሚወዛወዘው ጣና ለጥንታዊ ደብር ምስጋና እያቀረበ የሚመለስ ይመስላል። በማለዳና በማታ ሳያቋርጥ እየተወዛወዘ ዘመናትን ኖሯልና።
በአፀዱ ዙሪያ ያሉ ዛፎችን ጎንበስ ቀና ሲሉ እነርሱም ምስጋና እያቀረቡ ይመስላሉ። በሐይቁ ዙሪያ፣ በደብሩ አፀድ አዕዋፋት ልዩ ሕብር ባለው ዝማሬ ያደምቁታል፡፡ የተጨነቀ ጭንቀቱ ይርቅለታል፣ ያዘነ ይጽናናበታል፣ የደከመው ያርፍበታል፣ ነብሱ የተራበች፣ መዳረሻ አጥቶ የተቅበዘበዘች ለነብሱ ምግብ ያገኝባታል፣ ተስፋ ያጣ ተስፋ ያገኝበታል፣ የጨለመበት ብርሃን ያይበታል፣ በሐሴት እልም ጭልጥ ይልባታል፡፡
ካሕናት ዘመሩ፣ አሸበሸቡ፣ ጎበዛዝቱ ዘለሉ፣ ወይዛዝርቱ እልል አሉ፣ ውቢቷ ከተማ በእልልታ በደስታ ደመቀች፣ ደስታ በዛ፣ ምስጋናው ከፋለ፣ ነጫጭ የለበሱ ምዕምናን በዘንባባው ግርጌ በተሠራው መንገድ መሉ። እልልታው ዳር እስከ ዳር አስተጋባ፣ ፈረሰኛው ጊዮርጊስ ከመንበሩ ወጥቷልና። በፅሕናው የሚወጣው መልካሙ እጣን ወደ ሰማይ እየሰገረ፣ ምስጋናና ክብሩን እያቀረበ ከተማዋን በመልካም መዓዛ አወዳት፣ መልካም መዓዛ ቅዱስ መንፈስ አላበሳት፣ የባሕር ዳር ጎዳናዎችን እየተመላለሰ ላያቸው ኹሉ የሰማይ ከዋክብት ከሰማይ የወረዱ፣ መላእክት በነጭ ልብስ አጊጠው ምድርን የመሏት፣ በጎዳናዎቿ ላይም የተመለላሱባት፣ ይመስላሉ እንጂ ሰዎች ብቻቸውን አይመስሉም።
ያን ዓይቶ ያልተደሰተ፣ ሐሴትስ ያላደረገ ማን ይኖራል? ግሩም ድንቅ ነውና፡፡ በሐይቅ ዳር የሠፈረችው፣ ራሷም ሐይቅ የሆነችው ባሕር ዳር ደስታዋ ናኘ፡፡ ዘንባባዎቿ እንደ ሊቃውንቱ ኹሉ የሚያሸበሽቡ፣ እልልም የሚሉ መሰሉ፣ ኹሉም ልዩ ኾነ፡፡ ጣና የሚያስጌጣት፣ ግዮን የሚከባት፣ ጌጥ፣ ዝናር፣ የሚኾናት፣ አረንጓጌ ካባ የለበሰች፣ ከውቦች ውብ የኾነች ባሕር ዳር ደስታዋ ወደር አጣ፡፡ መለከቶች ተነፉ፣ ጽሕናጽሕኖች ተጸነጸሉ፣ ከበሮው ተመታ፣ እልልታው ደመቀ ምድሯን ደስታ ከበባት፣ ሐሴት ረበበባት፡፡
ከጣና ሐይቅ ዳርቻ፣ የለመለሙ ዛፎች የከበቡት፣ አዕዋፋት በድንቅ ዝማሬ የሚያዜሙበት አበው በልባቸው የሚጠብቁት አንድ ሥፍራ ነበረ፡፡ ያም ሥፍራ ደብር ሊደበርበት፣ የፈጣሪ ስም ሊጠራበትና ሊመሰገንበት፣ ሕዝብ ሊሰባሰብበት፣ በረከት ሊወርድበት አስቀድሞ የተዘጋጀ ነበር፡፡ አበው በልባቸው የጠበቁት ሥፍራ እውን ሊሆን ታላቅ ነገር ይቀመጥበት ዘንድ ዘመኑ ደረሰ፡፡ ታላቁ ንጉሥም በምድረ ኢትዮጵያ ነግሠው ነበር፡፡ እኒያም ንጉሥ በጣና ውስጥ ገዳማትን ያስገድሙ ነበር፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም እንዲሁ፡፡ ደጋግ ነገሮችንም እየፈጸሙ ነበር፡፡ አበው ባደነቋቸው፣ የታሪክ ድርሳናት አሳምረው በቀረጿቸው፣ አሻራዎቻቸው ምስክር በሚሆኑላቸው በዘመነ አምደ ጽዮን ተመሠረተ፡፡ የሐይቅ ዳሩ ባለ ግርማ፣ የሕዝብ መሰባሰቢያ፣ የባሕር ዳር ምልክት፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለፀናች እውነት፣ ለተከበረች ሃይማኖት የከፈለውን መስዋእትነት የሚያስቡ፣ ለምሥጋና የተዘጋጁ፣ በረከትን የሚሹ ክርስቲያኖች በፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ዙሪያ ተሰባስበዋል፡፡ ካሕናቱ በሚስረቀረቅ ድምጻቸው ያዜማሉ፣ መዘምራኑ ይዘምራሉ፣ ወይዛዝርቱ እልል ይላሉ፡፡ ዲያቆናቱ ለአገልግሎት ይፋጠናሉ፡፡ ከኤደን ገነት የሚፈስሰው ግዮን በቅርቡ አለና ፈለገ ገነት ይሉታል፡፡ ባለ ግርማውን ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራልን፡፡ ታቦቱ በጳጳሱና በሊቃውንቱ ታጅቦ ሲወጣ ምድር በእልልታ ተመላች፡፡
ሰማእትነት ማለት ምስክርነት ነው ይላሉ አበው። ሰማእትነት ክርስቶስ ከሰጣቸውና ካሳያቸው ግብራት አንደኛው ነው። በገዳም ተገኝቶ ለመነኮሳት ድንግልናንና ብሕትውናን አሳይቷል፣ ለሰማእታት ከአላውያን ነገሥታት ፊት ቆሞ ስለ እውነት መስክሮ አርዓያ ኾኗል። ስማእትነትንም አሳይቷል፡፡ እውነትን ለመመስከር ወደ ሐሰተኞች አደባባይ አመራ። እውነትን ወደ ማያውቁ ነገሥታት ሲሄድ ነገሥታቱ ደነገጡ። ፍርሃት ያዛቸው፣ እውነተኛው አምላክ እውነትን ይዞ ሲቀርብ የውሸት አደባባይ ተጨነቀች፣ ማምለጫ አጣች፣ ውሸት ከእውነት የምታመልጥበት የለምና መግቢያ ጠፋባት።May be an image of one or more people, people standing, sky and tree
ቅዱስ ጊዮርጊስም በዘመነ ሰማዕታት ተነስቶ፣ ምስክርነት ሰጥቶ፣ ነብሱን ለእውነት፣ የእውነት፣ ለእውነተኛው ሥርዓት አሳልፎ ክብር አገኘ። የምድር ነገሥታት ሲያዳፉት፣ የሰማይ መላእክት ደገፉት፣ የምድር ነገሥታት ሲገርፉት፣ የሰማይ መላእክት አበረቱት፣ የሚመሰክርለት ክርስቶስ የባርያውን፣ የአገልጋዩን መልካሙን ተጋድሎ ተመለከተ፣ የክብር አክሊል አቀዳጀው፣ በክብር ከፍ ከፍ አደረገው። ከፀሐይ ድምቀት አላቀው፡፡ የማያረጀውን፣ የማያልፈውን፣ በሰው ልጆች እጅ ያልተመረመረውን ክብር አላበሰው፡፡
በደብረ ይድራስና በሌሎች በጽናት ስለላደረገው ተጋድሎ፣ ስለተቀበለው መከራ፣ በጸናው ሃይማኖቱ ስለፈጸመው ሰማእትነት ክብር ተሰጥቶታልና ሰማእቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያመሰግኑታል፡፡ አማላጃችን እያሉ ያመሰግኑታል፡፡ ሊቃውንት የሚፈልቁበት፣ ምስጢራት የሚመሰጠሩበት ታላቁ ካቴድራል ለባሕር ዳር ብዙ ነገሯ ነው፡፡ እርሱን ተጠግታ ተመስርታለች፣ በእርሱ ውበት አጊጣለች፣ በእርሱ ግርማ ተላብሳለች፣ በእርሱ በረከት በረከት አግኝታለችና፡፡ ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ባሕር ዳርን ለረገጡ ኹሉ እንደኔ ያሉ ገዳማት ጣና ውስጥ አሉና ሂዱና እዩአቸው እያለ ያመላክታል፣ መግቢያ በር ይሆናል ይሉታል፡፡
በጥር 18 በሰባሩ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ታቦቱ ከመንበሩ ወጥቶ፣ ከተማዋን እያወደ ወደ ተዘጋጀለት ማረፊያ አመራ፡፡ አጀባው ብዙ ነው፣ እልልታውና ዝማሬው ድንቅ ነው፡፡ በተዘጋጀለት ድንኳን አረፈ፡፡ አያሌ አስደናቂ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተከናወነ፡፡ አጀባው ቀጥሏል፡፡ ታቦቱ ከድንኳኑ ወጥቶ በታላቅ አጀብ ወደ ጣና ሐይቅ ወረደ፡፡ በጀልባ ኾኖ ጣናሐይቅን ባረከ፣ ገሚሱ ሕዝብ ከጣና ዳርቻ ኾኖ ታቦቱን እልል እያለ ከበከበ፡፡ ባለ ጀልባዎች በታቦቱ ዙሪያ እየተመላለሱ ታቦቱን አጀቡ፣ ታቦቱ በሐይቁ ላይ ሲመላለስ፣ የእጣኑ ጭስ ሲጨስ፣ ምሥጋና እና ዝማሬ ሲደረስ ላየ ኹሉ ነብሱ በደስታ ትዘልላለች፡፡ በዚህ ሥፍራ የተገኘ ኹሉ ደስታው ወደር ያጣል፡፡
በአንድ ዕለት አንድ ኹነት ብላ በወርሃ ጥር ጥርን በባሕር ዳር እያለች የተለያዩ ክዋኔዎችን የምታሳየውና የምታየው ባሕር ዳር አብዝታ ትደምቃለች፣ የጎብኝዎችን ቀልብም ትስባለች፡፡ ከሌሎች ቀናት በተለየ ደግሞ በጥር 18 በሰባሩ ጊዮርጊስ ትደምቃለች፡፡ ጎብኚዎቿንም ትጣራለች፡፡ ሰባሩ ጊዮርጊስን የባሕር ዳር መገለጫ፣ የጎብኚዎችም መዳረሻ ለማድረግ ቤተክርስቲያኗ ከባሕልና ቱሪዝም ጋር እየሠራች መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ባሕል ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አብርሃም አሰፋ ሰባሩ ጊዮርጊስ ጥርን በባሕር ዳር አንዱ አካል እንደኾነም ነግረውናል፡፡ ሰባሩ ጊዮርጊስ ጥርን በባሕር ዳር ከኹሉም ደማቁ በዓል መሆኑንም ገልጸውልናል። ሰባሩ ጊዮርጊስ በዓል ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱን እንደጠበቀ የባሕር ዳር መገለጫ የኾነ በዓል እንዲሆን እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
ከቻሉ በኹሉም ወራት፣ ካልኾነለዎት ግን ጥርን በባሕር ዳር ያሳልፉ፣ በወርሃ ጥር ባሕር ዳር በልዩ ልዩ ኹነቶች ትደምቃለችና፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ። https://ameco.bankofabyssinia.com/
Previous articleበአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ መልሶ ለመገንባት የስዊድን መንግሥት እንዲደግፍ ትምህርት ሚኒስቴር ጠየቀ።
Next articleአሸባሪው ህወሓት እንደ አዲስ ከወረራቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ እንዲወጣና በቀጣናው የከፈተውን ጦርነት እንዲያቆም የአፋር ክልላዊ መንግስት አሳሰበ፡፡