በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከተሰነዘሩ 3ሺህ 406 አደገኛ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ከ96 ከመቶ በላይ የሚሆኑትን ማክሸፉን ኤጀንሲው ገለጸ።

67
ባሕር ዳር፡ ጥር 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ በ2014 በጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዉስጥ ከ3400 በላይ ‘አደገኛ’ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መከሰታቸዉን እና ከዚህ ውስጥ ከ96 ከመቶ በላይ ያህሉን ማክሸፉን ገልጿል።
ቀሪዎቹ ከ4 ከመቶ በታች የሚሆኑትን የጥቃት ሙከራዎች ደግሞ ምላሽ በመስጠት ሂደት ላይ መሆናቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ አስታዉቋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በ2014 ዓ.ም የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ 3ሺህ 406 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መፈጸማቸዉን ጠቁመዋል፡፡
ካለፈው የ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በዚህ በጀት አመት የተሞከረዉ የሳይበር ጥቃት ሶስት እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ይህም ጥቃቱ ከዓመት ወደ ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ለጥቃቱ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ዓለም አቀፍ የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚነት ማደግ፣ በዘርፉ ወንጀልን ለተለያዩ ዓላማዎች የሚጠቀሙ ተዋኒያን መበራከት፤ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና የጂኦ-ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች መጨመር እንዲሁም ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በስድስት ወራት ከተሞከሩ ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹን ጥቃቶች የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ማክሸፍን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህ ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ በግለሰብ ፣ በተቋማት እና በሀገር ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ክስረት በጣም ከፍተኛ ይሆን ነበር ብለዋል።
አብዛኛዎቹ ጥቃቶች ትኩረታቸዉን በፋይናንስና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም በመንግስት መስሪያቤቶች ላይ ያነጣጠሩ እንደነበር ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ በስፋት የተሞከሩት የሳይበር ጥቃት አይነቶች ዉስጥም የድረ-ገጽ ጥቃት ፣ የማልዌር ጥቃት እና የመሠረተ-ልማት ቅኝት ጥቃቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
እነዚህ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በተለያዩ ህገወጥ አካላት የተሰነዘሩ መሆናቸው የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ጥቃቶቹ በተለይም ከህልውና ዘመቻ ጋር በተያያዘ በሀገር ውስጥ ካሉ ሀገር የማፍረስ ተልእኮ ካላቸው አካላት እና በሀገራችን ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ እጃቸውን ማስገባት በሚፈልጉ ምእራባዊያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በሚገኙ የሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች መሆኑን አብራርተዋል።
ኤጀንሲው በየጊዜው ባህሪውን የሚለዋውጠውን የሳይበር ደኅንነት ዘርፍ ታሳቢ ያደረገ ሀገራዊ ፣ ቀጠናዊ እንዲሁም አለምአቀፍ የሳይበር ምህዳሩን ላይ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማጥናት፣ ቀድሞ የመዘጋጀት፣ የማቀድና በጥብቅ ዲሲፕሊን ስራዎችን በመሰራቱ አሁን ባለው ነበራዊ ሁኔታ የሳይበር ጥቃትን የማስጠበቅና የመጠበቅ ቁመናው አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
“የሳይበር ደኅንነት የሁሉም ኃላፊነት ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ተቋማት ስነ-ምግባር የተላበሱ ሙያተኞችን እንዲኖራቸው በመሥራት፣ የሳይበር ደኅንነቱ የተጠበቀ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ ፣ የሚጠቀሙባቸውን ሲስተሞች ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ኦዲት በማስደረግ እና የአሠራር ሥርዓቶችን በአግባቡ በመተግበር የሳይበር ደኅንነት ሊያረጋግጡ ይገባል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ሹመቴ አሳስበዋል፡፡ መረጃው የኢመደኤ ነው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
Previous articleየኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረገ፡፡ ድጋፉ የሚዲያዎችን እርስ በርስ መደጋገፍና ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆምን የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዙሪያ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡