
ጥር 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በከፈተው ጦርነት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል። አሸባሪ ቡድኑ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) መሰረተ ልማቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት አንዱ ነው፡፡ ይህን የተረዱ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት ከአሚኮ ጎን በመቆም ድጋፋቸውን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ለአሚኮ ዛሬ የተለያዩ ድጋፎችን አድርጓል።
ኢዜአ ለአሚኮ የተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አበርክቷል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ የተገኙት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ አሚኮ ላለፉት አንድ ዓመት ተኩል ገደማ ግንባር ላይ ሕዝቡን በማንቃትና ከመንግሥት ጎን ቆሞ እንዲታገል በማድረግ ለድል እንድንበቃ ጉልህ ድርሻ ያበረከተ ሚዲያ ነው ብለዋል፡፡
ከጦርነቱ በፊትም ቢሆን ሚዲያው በኹሉም መስክ የሕዝብ ሐሳቦችንና ብሶቶችን በማሰማት የቆየ የሕዝብ ሚዲያ ነው መሆኑን ሚኒስትሩ መስክረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያደረገው ድጋፍ የሚመሰገን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአሚኮን የጎላ ሥራ አሸባሪው ትህነግም የመሰከረው ነው ያሉት ሚኒስትሩ ከተለያ ስሁት ትርክቶች የተነሳ ብዙ ችግሮች በየአካባቢው ይፈጠራሉ፤ በጣም ብዙ የሚያግባቡን ነገሮችን ነቅሶ በማውጣት እነዚህን ትርክቶች ተከትሎ የሚመጡትን ጥፋቶችና የአንድነት ስጋቶች በመቀነስና በማስተካከል በኩል ሚዲያዎች ትልቅ ሚና አላቸው ነው ያሉት። ለጋራ ተጠቃሚነት፣ አንድነትና ፍትሐዊነት በጋራ ሊቆሙ ይገባል፤ አሚኮም በዚህ ረገድ ሚናውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስተባባሪ ሚኒስትሩ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እንደተናገሩት አሸባሪ ቡድኑ ካወደማቸው ተቋማት መካከል አንዱ ሚዲያ ነው። አሚኮ ደግሞ ለአንድነ፣ ለሕዝቦች ወንድማማችነት ሲሠራ የነበረ የኢትዮጵያውን ሚዲያ ነው፤ ለድሉ መገኘት ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረገ ሚዲያ ነው ብለዋል።
እንደ ኢዜአ ያሉ የሚዲያ ተቋማት ደግሞ የአንዱ ሚዲያ መጎዳት ለሌላውም ነው ብለው የደረሰውን ተረድተው ሚዲያው ተመልሶ ወደ ሥራ እንዲገባ ለማድረግ ካላቸው ላይ ቀንሰው የሰጡት ድጋፍ ለሌሎች አርዓያነትን የሚሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ የዛሬው ድጋፍ ለረጅም ጊዜ ከአሚኮ ጋር ከነበረን የሥራ ግንኙነት የመነጨና የደረሰውን ውድመት በጋራ ለመመለስ የሚያስችል አጋጣሚ ነው ብለዋል። 80ኛ ዓመታችንን እያከበርንበት ባለው በዚህ ወቅት ደግሞ ከአሚኮ ጋር በጋራ መቆማችንን ለማሳየት ድጋፍ አድርገናል ነው ያሉት። የዜና ሽያጭ ወጪን ጨምሮ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን የያዘ ድጋፍ አድርገናል ብለዋል፡፡
የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ ድጋፉን ሲረከቡ እንደተናገሩት በምሥራቅ አማራ ከስድስት በላይ ጣቢያዎቻችን ጉዳት ደርሶባቸዋል። ❝የብቻ ምቾት የብቻ ጉዳት የለም ብሎ ኢዜአ ስላበረከተልን ድጋፍ እና በአብሮነት ስለቆመ እናመሰግናለን❞ ብለዋል፡፡ ወደፊትም ለሀገራችን በጋራ በመተባበር ስሜት እንሠራለን ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።