
አዲስ አበባ: ጥር 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በመሠረተችው መድረክ ያልተሳካላት፣ የባለቤት እንግዳ፣ በራስ ድግስ ተመልካች የኾነችው ኢትዮጵያ ከዓመታት በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ መድረክ ብትቀርብም ሳይሳካላት ቀርቷል፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ታላቅ ሠንደቅ ወክለው ካሜሮን የደረሱት ዋልያዎቹ ውጤቱ ባልጠበቁት መንገድ ኾኖ በጊዜ ከአፍሪካ ዋንጫ ተሰናብተዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የዋልያዎቹን መድመቅ ለማየት የጓጉና የተመኙ ኢትዮጵያውያንም ከምድብ ጨዋታዎች በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን በካሜሮን ሰማይ ሥር መመልከት አልቻሉም፡፡
በካሜሩን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ይዞ በጊዜ መሰናበቱ ይታወሳል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ከ8 ዓመታት በኋላ ወደ ውድድር ከተመለሰበት መድረክ ሳይቀናው ተመልሷል።

ገና በመጀመሪያው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወሳኙን ተከላከይ በቀይ ካርድ ያጡት ዋልያዎቹ የእቅዳቸው መሰናክል እንዲጀምር አድርጓል፡፡ በምድብ ጨዋታዎች ሁለት ግብ ያስቆጠሩት ዋልያዎቹ በአንጻሩ 6 ግቦች ተቆጥረውባቸዋል፡፡ በኬፕቨርዲ 1ለ0 ፣ በካሜሩን 4 ለ1 ሲሸነፉ ከቡርኪናፋሶ ጋር 1አቻ ተለያይተዋል።
የብሔራዊ በድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎና ውጤትን አስመልክቶ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን መግለጫ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በመግለጫቸው የፌዴሬሽኑ እቅድ ከምድብ ማለፍ እንደነበር ገልጸዋል። ይህ መሳካት ባለመቻሉም የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል።
የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የተጫዋቾች በኮሮናቫይረስ መጠቃትና ከኬፕቨርዲ ጋር በነበረው ጨዋታ የተከላካዩ ያሬድ ባየህ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣት የታሰበው ውጤት እንዳይመጣ ዋና ምክንያት አድርገው ጠቅሰዋል። ብሔራዊ ቡድኑ ከውድድሩ በፊት በርከት ያሉ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ አቅዶ እንዳልተሳካም አስታውሰዋል። ይህም ለውጤቱ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩም ነው የገለፁት። ብሔራዊ ቡድኑ የተገኙትን የግብ እድሎች በመጠቀም በኩልም ክፍተት እንደነበረበት የተናገሩት አሰልጣኝ ውበቱ ይህ ደግሞ ከተጨዋቾች የልምድ ማነስ የመጣ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ዋንጫ መሥራቿ ኢትዮጵያ ከካሜሮኑ ድግስ በጊዜ ተሰናብታ ሌላ የአፍሪካ ዋንጫ እንድትጠብቅ ተገድዳለች፡፡
ዘጋቢ:- ባዘዘው መኮንን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።