❝እንሂድ አምባሰል በሽሎን እንሻገር ግሸን እንገናኝ ግማደ መስቀሉ ካረፈበት ሀገር❞

248
ጥር 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም የዳነበት፣ እርቅ የተፈፀመበት፣ ጠላት የተሸነፈበት፣ ፍጹም ፍቅር የታየበት መስቀል በክብር አርፎበታል፣ በመስቀል አምሳል የተቀመጠ ባለ ግርማ ነው፣ የፈጣሪ ስም ሳይጠራበት፣ በንጽሕና ሳይመሰገንበት፣ ጽድቅና በረከት ሳይለመንበት፣ በረከትም ሳይወርድበት የዋለበት ቀን ያለ አይመስልም፡፡ ተፈፀመ እንዳለ የጨለማው ዘመን የተፈፀመበት፣ የብርሃን ዘመን የተጀመረበት፣ ክርስቶስ ፍፁም ፍቅሩን ያሳየበት፣ ራሱን አሳልፎ የሰጠበት፣ የሰው ልጆች መዳኛቸውን የተቀበሉበት፣ ታላቁ መስቀል በሥፍራው ጸልሎበታል፡፡
የዓለም ዓይኖች ኹሉ ግማደ መስቀሉን ያገኙ ዘንድ ያማትራሉ፣ ግማደ መስቀሉ ወደ አለበት ሥፍራ ይቀርቡና ይመራመሩ ዘንድ ይሻሉ፣ የእነርሱ ይሆን ዘንድም ይመኛሉ፣ ዳሩ ግማደ መስቀሉ ይቀመጥ ዘንድ የተመረጠው፣ አስቀድሞ የተዘጋጀው በመስቀለኛው ተራራ ላይ እንጂ ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ፈጣሪ ከድንቁ ላይ ድንቅ ነገር ሲጨምርበት ከመስቀለኛው ተራራ ላይ መስቀሉ ይቀመጥ ዘንድ ፈቀደለት፡፡ ድንቅ ጥበብ፣ ድንቅ ምስጢር፣ ድንቅ ስጦታ፡፡
በመስቀል አምሳል በተቀመጠው በዚያ የተቀደሰ ተራራ ጥበብ ሰፍሮበታል፣ ቅዱስ መንፈስ ሞልቶበታል፣ በረከት ተርፎበታል፣ ፈጣሪ ለኢትዮጵያ ፀጋና በረከት ይሰጥ ዘንድ ይለመንበታል፣ ዳሯ እሳት መሐሏ ገነት ትሆን ዘንድ ይጸለይበታል፡፡ ፈጣሪም በመስቀለኛው ተራራ አናት ላይ ከተቀመጠው መስቀል ግርጌ ኾነው የሚማፀኑትን ይሰማቸዋል፣ የሚሹትን ኹሉ ይሰጣቸዋል፡፡
ከተራራዎች ኹሉ የከበረች፣ ለመስቀሉ ማረፊያ የተመረጠች፣ ከዘመን ዘመን እንድትመረመር፣ ሕዝቡ ኹሉ እንዲጓዝባት የተዘጋጀች፣ እግሮች ኹሉ ወደ እርሷ እንዲሄዱ፣ ጀሮዎች ኹሉ ወደ እርሷ እንዲያዘነብሉ የታደለች፣ ጥበባትን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን፣ ታቦታትን ታቅፋ የኖረች፣ ዛሬም ታቅፋ ያለች ድንቅ ምድር፡፡ መስቀል አድርጎ የፈጠራት፣ መስቀሉን ያኖረባት፣ በረከቱን ያስቀመጠባት፣ ተስፋና በረከት የሰጠባት የበረከት ማደሪያ የቅዱሳን መናኸሪያም ናት።
የእስራኤላውን የባርነት ዘመን ሊፈፀም ሲል ደግ መሪ ተገኘ፡፡ ይህም ሰው ሙሴ ነው፡፡ ሙሴም በፈጣሪው እየተመራ ሕዝበ እስራኤልን ከባርነት ወደ ርስት ያሻገር ዘንድ ታዘዘ፡፡ የሕዝበ እስራኤላውያን የባርነት ዘመን ሊፈፀም ቀረበ፡፡ እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት ከግብፅ ባርነት ወጥተው ወደ ምድረ ርስት ተጓዙ፤ ፈጣሪም በተራራ ላይ እየተገለጠ ያናግራቸው ነበር። የሲና፣ የጽዮንና የታቦር ተራራዎችም ፈጣሪ ድንቅ ነገርን ያደረገባቸው የተመረጡ ሥፍራዎች ናቸው። በሲና ተራራ ተገለጠ፣ ትዕዛዛቱንም ለሙሴ ሰጠ፣ በታቦር ተራራ መለኮቱን ገለጠ፣ በግሸን ደብረ ከርቤ አምባሰል ተራራ መስቀሉን አስቀመጠ፣ ብርሃንንም ገለጠ። ለኢትዮጵያም የጠላቶችን ማሸነፊያ የሆነውም መስቀል ሰጠ፡፡ ከተራራዎች ኹሉ ለክብሩ መዘከሪያ፣ ለመስቀሉ ማደሪያ ግሸን ደብረ ከርቤን መረጠ፡፡
እግዚአብሔር ከባረካቸው፣ አስቀድሞ ለቅዱሳን መቀመጫ፣ ለቅድስና ካዘጋጃቸው ተራራዎች አንደኛዋ ናት ግሽን ደብረ ከርቤ፡፡ ኹሉን የሚያድርግ ጌታ የሰውን በደል ይሽር ዘንድ ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፣ መስቀሉም በደም ተሸፈነ፣ ደሙን አፈሰሰ፣ ስጋውን ቆረሰ፡፡ በደሙ መፍሰስ፣ በስጋው መቆረስ ታዲያ የሰው ልጅ የሕይወት መሠረት ኾነ፡፡ በመስቀል ተሰቅሎ ለሰው ልጆች ብርሃንን ሰጣቸው፡፡ ከመስቀሉ ብርሃን ወጣ፣ ለዓለም ኹሉ በራ፡፡ የብርሃን ጌታ፣ ብርሃን የኾነ አምላክ ዓለምን በብርሃን መላት፣ የመከራዋን ዘመን በተቀበለው መከራ ሻረላት፣ መልካሙን ዘመን አመጣላት፡፡ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀሉ የፈሰሰውን ቅዱስ ደም የጠጡ፣ የተቆረሰውን ስጋ የበሉ ኹሉ መልካሟን ርስት ይወርሳሉ፤ ወደ እርሷም ይቀርባሉ፡፡ የድል ነሽዎች ምልክት፣ የአሸናፊዎች አርማ፣ የክርስቲያኖች መመኪያ ነው መስቀል፡፡
ግማደ መስቀሉ ከዚያ ስፍራ ውጭ በየትኛውም ሥፍራ ያርፍ ዘንድ አልተፈቀደም፡፡ የመስቀሉ ማረፊያ መስቀለኛው ተራራ ብቻ ነበር እንጂ፡፡ ታላቁ ንጉሥ ዘርዓያዕቆብ መስቀሉን በመረጡት ሥፍራ ሊያስቀምጡት ፈልገው ነበር፡፡ ዳሩ ፈቃደ እግዚአብሔር ካልተጨመረበት እርሳቸው በፈለጉት ሥፍራ አይቀመጥም፡፡ መስቀሌን በመስቀለኛው ተራራ ላይ አስቀምጥ አላቸው፡፡ እርሳቸውም ያ ቃል ኪዳን ይፈፀም ዘንድ መስቀለኛውን ተራራ ፈለጉ፡፡ በቀላሉ ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ የኢትዮጵያ አውራጃዎችን በመስቀል እያስባረኩ ዞሩ፡፡ ሱባኤም ያዙ፣ ፈጣሪም መስቀለኛውን ተራራ ግሸን ደብረ ከርቤን ገለጠላቸው። መስቀሉንም በመስቀለኛው ተራራ ላይ አስቀመጡ፡፡
መከራ የጠናባቸው እስራኤላውያን ከሀገራቸው ተሰደው በየመን ይኖሩ ነበር፡፡ ሮማውያንን የሸሹት የሀገረ እስራኤል የኢየሩሳሌም ሰዎች በየመን በሀገረ ናግራን ይኖሩ ነበር። በዚያ ምድር ዓለምን ንቀው የሰማዩን ርስት፣ ጸጋና በረከት፣ የማያልፍ ዓለም የሚሹ አንድ ፃዲቅ መነኩሴ ነበሩ። እኒህም ሰው የቀደመ ስማቸው ፍሊክስ የኋለኛው ስማቸው ደግሞ ፈቃደ ክርስቶስ ይባሉ ነበር። እኒህ ሰው አንደበታቸውንና ልባቸውን ለምስጋና አዘጋጅተው ፈጣሪያቸውን ይማጸኑ ነበር፡፡ ያለ ምስጋና የሚያሳልፏት ጊዜ አልነበረቻቸውም፡፡ ከቅዱሱ መናኝ ጋርም ሁለት ጽላቶች ነበሩ፣ የእግዚአብሔር አብና የቅድስት ድንግል ማርያም ጽላት። ማርያምም ለቅዱሱ አባት በራዕይ ተገለጠችላቸው። ጽላቶቹን ይዘው የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ ወደሚታይበት ሀገር ይሄዱ ዘንድ ነገረቻቸው። መነኩሴው የተባሉትን አደረጉ።
በራዕይ እየተመሩ 12 መነኮሳትን አስከትለው ገሰገሱ፡፡ ተራራና ሸንተረሮችን አቋረጡ፣ ወንዞችን ተሻገሩ፡፡ የተባለው እስኪፈፀም እውነተኛው ሥፍራና እውነተኛው ምልክት እስኪመጣ ድረስ ተጓዙ፡፡ ከእውነተኛው ሥፍራም ደረሱ፡፡ የብርሃን አምድ ከተተከለባት ጸጋና በረከት ከመላት ምድር ደረሱ። ያም ምድር ተራራማ ነበር፡፡ እኒያ አባት ተከታዮቻቸውን አስከትለው የበሽሎን ወንዝ ተሻግረው ወደ ተራራው ወጡ፡፡ በተራራው የንብ መንጋ ሰፍሮበት ነበር፡፡ የማሩ ሰፈፍ ያስደንቅ ነበር፡፡ አካባቢው ደን የበዛበት አራዊት የሚኖሩበት ነው፡፡ እኒያ ቅዱስ መነኩሴ ባዩት ኹሉ ተደነቁ፡፡ ተራራው ከኹሉም ተራራዎች ይለያል። የንቡ ብዛት የማሩ ሰፈፍ ያስደነቃቸው ቅዱስ መናኝ ይህስ አምባአሰል ነው አሉ። አሰል ማለት በአረበኛ ማር ነው። የማር አምባ ሲሉ አምባሰል አሏት። በመስቀል የተቀረጸ ምድር፣ የመናንያን፣ የባሕታዊያን የቅዱሳን፣ የበረከት ሀገር አምባሰል።
ፈቃደ ክርስቶስ ወደ ተራራው የምታስወጣቸው አንዲት መንገድ አግኝተው ተከታዮቻቸውን አስከትለው ወደ ተራራው ወጡ። በድንግል ማርያም አማካኝነት የተነገረው ራዕይ ይፈፀም ዘንድ ፈቃዱ ኾኗል፡፡ በዚያ መስቀለኛ ተራራ ላይም ጎጆ ቀለሱ፡፡ ጽላቱንም በክብር አስቀመጡ፡፡ በዘመኑ በኢትዮጵያ ላይ ነግሠው የነበሩት አጼ ካሌብ መስቀለኛው ተራራ ላይ ቤተ መቅደስ አሠርተው ገዳም ገደሙ፡፡ ራዕዩ ኹሉ ተፈፀመ፡፡
ፈጣሪም ቅዳሴ ቤቱ ሲከብር ኢትዮጵያን ባረካት፣ ከፍ ከፍ አደረጋት። የዘለዓለም ቃልኪዳን ሰጣት። ሰማይና ምድር ሲያልፉ የማይለወጥ የማይናወጥ ቃል ኪዳን። ግሸን ታላቋ ምድር በልዩ ልዩ ሥያሜዎች ትጠራ ነበር። ደብረ ነጎድጓድ፣ ደብረ እግዚአብሔር፣ ደብረ ነገሥት ትባል ነበር። ግማደ መስቀሉ ሲገባ ደግሞ ደብረ ከርቤ ተብላ ተጠራች።
በቀደመው ዘመን በታላቋ ተራራ የካህናትና የነገሥታቱ ልጆች ጥበበ ስጋን ከጥበበ ነብስ ጋር እያዋሃዱ ይማሩበት ነበር። ነገሥታቱ ይማጸኑባታል፣ በረከት ይለምኑባታል፣ ልጆቻቸውን የቤተመንግሥት ሥርዓት ያስተምሩባታል።
በዚያች ሥፍራ የኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ ከለሜዳ፣ ሐሞት የጠጣበት ሰፍነጉ፣ የተገረፈበት ጅራፉ፣ የታሠረበት ገመዱ፣ የድንግል ማርያም የእናቷ የሀና፣ የአባቷ የእያቄም፣ የሀዋርያው የበርቶሎሚዎስ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዘልዳ፣ ሄሮድስ ያስጨረሳቸው ሕፃናት፣ የአርሴማ እና የሌሎች ቅዱሳን አፅሞች፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ የፈረሱ ጭራና እልፍ ምስጢራት በተቀደሰው ምድር ይገኛል ይላሉ አበው።
በሌላው ዓለም የሌለ በተከበረው ተራራ በግሸን ‟መጽሐፍ ጤፉት“ የተሰኘ ታላቅ መጻሕፍም ይገኛል። በየዘመናቱ የተነሱ ነገሥታት ያበረከቱት ሥጦታም በዚህ በተቀደሰው ምድር ይገኛል።
እነሆ በወርሃ መስከረም በ21ኛው ቀን የምትከብረው ግሸን በዘመኑ በተነሱ ክፉ ሰዎች ምክንያት ልጆቿን በብዛት ሳትሰበስብ ቀርታለች፣ የበዙ ልጆቿም በመስለኛው ተራራ እየወጡ ከመስቀሉ በረከት ሳይበሉ ቀርተዋል፣ አዝነዋልም፡፡ የክፉ ሰዎች ቀን አልቆ የመልካም ሰዎች ዘመን ሲመጣ ወደ ዚያች ስፍራ ይሄዱ ዘንድ ተስፋ ሰንቀው ተቀምጠዋል፡፡ ተስፋ ያደረጉት ዘመን መጥቷል፡፡ ክፉዎችም ከአካባው ተጠራርገው ወጥተዋል፡፡ ግሸን ደብረ ከርቤም በበዓለ አስተርዮ ይመጡላት ዘንድ ጠርታለች፡፡ መስቀለኛዋ ተራራ በበዓለ አስተርዮ ትደምቃለች፣ ትክብራለችና፡፡ በዝማሬ ትታጀባለች፣ በሊቃውንቱ ታብባለች፣ በምዕምኑ ትዋባለችና፡፡
❝እንሂድ አምባሰል በሽሎን እንሻገር
ግሸን እንገናኝ ግማደ መስቀሉ ካረፈበት ሀገር❞ ከበሽሎ ማዶ፣ ከመስቀለኛው ተራራ፣ መስቀሉ ካረፈበት ምድር ላይ እንገናኝ፡፡ በወርሃ መስከረም በረከት ያልተቀበሉ፣ ሥፍራውንም ያረገጡ ወደ ተራራው ይውጡ፡፡ በዚያም ሥፍራ ለበረከት ይቀመጡ፡፡ በዚያ እልፍ ነገር አለና፡፡ ወደዚያው አቅኑ፡፡ ድንቁን ነገርም ተመልከቱ፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
Previous articleእናቶች የወሊድ ክትትላቸውን በጤና ተቋማት እንዲያደርጉ ሁሉም የበኩሉን ደርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
Next article❝ድርቅ እንዳይከሰት በዘላቂነት ለመከላከል በቆላማ አካባቢዎች የውኃ ክምችትና አጠቃቀምን ለማሻሻል የጀመርናቸውን የአነስተኛ ግድቦች ግንባታ ፕሮጀክቶች እናፋጥናለን❞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)