“በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ጉቦ የመቀበል ወንጀል ሙከራዎችን አክሽፈናል” የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው

196

ባሕር ዳር፡ ጥር 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የገቢዎች ሚኒስቴር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ጉቦ የመቀበል ወንጀል ሙከራዎችን ማክሸፉን ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌው አስታወቁ።

አቶ ላቀ አያሌው በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በንጹህ እጅ የማይሠሩትን የውጭ እና የውስጥ ሌቦችን እየተከታተለ እርምጃ በመውሰድ የሀገር እና የሕዝብን ሀብት በመታደግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ባለፉት ወራት ሐሰተኛ ደረሰኝ ብቻ እየሸጡ የሀገር ሀብት ወደ ኪሳቸው ሲያስገቡ የነበሩ 63 ድርጅቶችን ማጋለጡን በምሳሌነት አንስተዋል።

ገቢዎች ሚኒስቴር ውስጥም የውስጥ ሌቦች እንዳሉ እሙን ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በዚህም በተለያየ ጊዜያት ሊፈፀሙ የነበሩ እና የከሸፉ ወንጀሎችን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

አንደኛው በገቢዎች ሚኒሰቴር አዳማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 1 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ጉቦ ለመቀበል ተስማምቶ የቅድሚያ ክፍያ 500 ሺህ ብር ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሁለተኛ፣ በገቢዎች ሚኒሰቴር ምሥራቅ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 5 ሚሊዮን ብር ለመቀበል ተስማምተው የመጀመሪያ ክፍያ 200 ሺህ ብር ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል ብለዋል።

ሦስተኛ፣ በኢትጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ሞጆ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 200 ሺህ ብር ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሠራተኛ መኖሩን ገልጸዋል።

አራተኛ፣ በገቢዎች ሚኒስቴር በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሁለት ኦዲተሮች 12 ሚሊዮን ብር ጉቦ ለመቀበል ተስማምተው የመጀመሪያ ክፍያ 100 ሺህ ብር ለመቀበል በሂደት ላይ እያሉ እጅከፍንጅ ለመያዝ መቻሉን ገልጸዋል።

ከላይ በተጠቀሱት እርምጃዎች ያልተማሩ የውስጥ እና የውጭ ሌቦች ዛሬም በተቀናጀ መንገድ የሀገር እና የሕዝብ ሀብት የሆነውን ከፍተኛ የታክስ ገንዘብ ለድርጅቱ እንዲቀር በማድረግ ይህን ለሚሠሩበት ውለታ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወደ ግላቸው ሊያስገቡ ሲሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቀዋል።

የድርጊቱ መፈፀም የታወቀው አንድ የፌዴራል ግብር ከፋይ የሆነ ድርጅት የዕቃ ግዥም ሆነ ሽያጭ ግብይት ሳይፈፅም እንዲሁም አገልግሎት ሳይሰጥ ሐሰተኛ ደረሰኝ ብቻ በማዘጋጀት የሀገር ሀብት እየዘረፈ መሆኑ ጥቆማ በመድረሱ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ይህን ወንጀል የፈፀመው ድርጅት የሀገር ሀብት በመዝረፍ ለግል ጥቅም ማዋል መለያ ባህሪው የሆነ ድርጅት እንደሆነም የገቢዎች ሚኒስትሩ ላቀ አያሌው ገልጸዋል።

የዚህ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ እና ሒሳብ ሠራተኛው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አንድ የታክስ ኢንተሌጀንስ ባለሞያ ጋር በመግባባት የተቋሙ የታክስ ኢንተለጀንስ ባለሙያ ከኦዲተሮች ጋር እንዲያደራድራቸው በማስማማት ወንጀሉን ሊፈፅም ሲል እጅ ከፍንጅ የተያዘ መሆኑንም አሳውቀዋል።

ወንጀሉ እንዲደረስበት መልካም ሥራ ለሠሩ የሥነ-ምግባር መከታተያ ዳሬክቶሬት አመራሮች እና ባለሞያዎች፣ የሕዝብን ሀብት አንነካም በሚል ለኅሊናቸው ላደሩ ኦዲተሮች፣ ድርጊቱን በመከታተል ለውጤት ላበቁ የገቢዎች ሚኒስቴር አመራሮች እና ሠራተኞች እንዲሁም ለፌዴራል ፖሊስ በራሳቸው እና በገቢዎች ሚኒስቴር ሥም አክብሮት እና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ ሙስናን ለመከላከል እና ሌብነትን ለማስቆም የራሱን ጥረት እያደርገ እና ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑንም የገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌው ገልጸዋል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleምሥራቅ ዕዝ በውጊያ የተሻለ ውጤት ላመጡ እና የመቆያ ጊዜያቸውን ለሸፈኑ የሠራዊት አመራሮችና አባላት የማዕረግ ዕድገት ሰጠ፡፡
Next articleየጉብኝት መዳረሻዎችን በማልማት እና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ጠቀሜታ ማሳደግ እንደሚገባ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሣኅሉ (ዶ.ር) ገለጹ፡፡