
ባሕር ዳር፡ ጥር 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ በአማራ ክልል በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ለተጎዱ ወገኖች የሚውል 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን ያስረከቡት የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሴ ጋጄት አሸባሪው ቡድን በተለይ በትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ ፈጽሟል ብለዋል። “ለተከሰተው ችግር በቂ ምላሽ ባናደርግም ለወገናችን አለኝታነታችንን ለመግለጽ ነው የበኩላችንን ድጋፍ ያደረግነውና እዚህ የተገኘነው” ብለዋል።
ድጋፉ የመጀመሪያ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሴ ለአማራና ለአፋር ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል የወደሙ የትምህርት ተቋማትን ለመደገፍ የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ከጎኑ እንደሚቆም አቶ ሙሴ አረጋግጠዋል። በመጀመሪያ ዙር ድጋፍ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ማስረከባቸውን ገልጸዋል።
አቶ ሙሴ በአማራና በአፋር ክልሎች የደረሰው ውድመት የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን ነው ብለዋል። ድጋፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በአካል በመገኘት የሞራል ድጋፍም ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ እዚህ ተገኝተናል ነው ያሉት።

የተጀመረው የአንድነት ጉዞ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ ሙሴ ገልጸዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ በተደጋጋሚ የህልውናውን ዘመቻ ሲደግፍ እንደነበረ ኀላፊው አስታውሰዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሙላው አበበ የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ላደረገው ድጋፍ በአማራ ክልል ተማሪዎች፣ መምህራንና በትምህርት ተቋማት ሠራተኞች ስም ምስጋና አቅርበዋል። ወራሪው ቡድን በወረረበት አካባቢ ሁሉ የትምህርት ቤቶችን ወንበሮች፣ ፕላዝማዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ መረጃዎችንና ሌሎች ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ ዘርፏል አውድሟል ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ ትምህርት ቤቶችን የመቃብር ቦታ ማድረጉን ምክትል ኀላፊው ጠቁመዋል።

የወደሙ የትምህርት ተቋማትን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የክልሉ መንግሥት ብቻውን ስለማይችለው የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
ድጋፉንም ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንደሚደርስ አስረድተዋል። ይህም የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን አቶ ሙላው ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።