“ተነጣጥሎ ከመቆም በሕብረት መቆም የአሸናፊነት ሚስጥር መሆኑን አይተናል፤ በተገኘው ድልም እንዳንታበይ እና እንዳንዘናጋ ድሉን ጠብቆ እና ተንከባክቦ ማስቀጠል ተገቢ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

118

አዲስ አበባ፡ ጥር 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለመገናኛ ብዙኀን ተቋማት እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በኅልውና ዘመቻ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የምስጋና እና እውቅና መርኃ ግብር ተዘጋጅቷል።

“ዘማች የሚዲያ እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች!” በሚል መሪ ሐሳብ በተዘጋጀው መርኃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት ኅላፊዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በጦርነቱ ኢትዮጵያ አሸንፋለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣዮቹን ሂደቶች በስኬት ለማጠናቀቅ የተገኘውን ድል መጠበቅ፣ ማስቀጠል እና የአሸናፊነት ሥነ ልቦናን መገንባት የቀጣይ ጊዜ ትኩረት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የኅልውና ስጋቱ የተቃጣው በኢትዮጵያዊን ላይ ነበር፤ ያሸነፍነውም ኢትዮጵያዊያን ነን እና ድሉን በጋራ መጠበቅ ይኖርብናል ነው ያሉት።

በየጊዜው የሚፈጠረውን ወጀብ ለመሻገር ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን መርከብ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መርከቧ እያለች ለጀልባ መዘጋጀት እንደማያሻግር ትናንት ዓይተናል” ነው ያሉት። የመርከቧ ባለቤት ኢትዮጵያዊያን መርከቧን ከማጠናከር እና ከማበርታት ወጥተው ለጀልባ ቢዘጋጁ ማነስ ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እኔ” ከሚል እሳቤ ወጥቶ “እኛ” ማለት እና በጋራ መቆም መርከቧን ከወጀቡ ያጸናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው “ተነጣጥሎ ከመቆም ወጥቶ በጋራ እና በሕብረት መቆም የአሸናፊነት ሚስጥር መሆኑን አይተናል። በተገኘው ድል እንዳንታበይ እና እንዳንዘናጋም ድሉን ጠብቆ እና ተንከባክቦ ማስቀጠል ተገቢ ነው” ብለዋል።

በኅልውና ዘመቻው የኢትዮጵያ ጠላቶች አሸናፊ ሆነው ቢሆን ኖሮ ድላቸውን የሚገልጹበትን መንገድ መገመት አይከብድም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያዊያን የአሸናፊነት ሥነ ልቦናቸውን የበለጠ በመገንባት ለቀጣይ ሥራ ሊተጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የብዙኀን መገናኛ ተቋማት እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም የትውልዱን የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ለማስቀጠል እና በኢትዮጵያዊነት ስሜት ቀርጾ ለመገንባት ኅላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው -ከአዲስ አበባ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበኩር ጋዜጣ ጥር 16/2014 ዓ.ም ዕትም
Next articleበደረሰ የትራፊክ አደጋ የ20 ሰዎች ሕይዎት አለፈ፡፡