❝ግዮን ወተት ኾኖ ገነትን ካጠጣት የግዮን መነሻ ኢትዮጵያ ምንድን ናት?❞

463

ጥር 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የምስጢራት መገኛ ማኅደር፣ የጥበባት መፍለቂያ ሀገር፣ የረቂቅ ሕብስት መቀመጫ መሶበ ወርቅ፣ ለፈጣሪ የሚበረከት ወርቅ፣ ያልተደረሰባት ረቂቅ፣ በፈጣሪ የተመረጠው አፍላግ የሚፈስስባት፣ በምድሯ የሚፈልቅባት፣ ጥበብ የመላት፣ በረከት የተቸራት፣ ቃል ኪዳን የተሰጣት ድንቅ ምድር፡፡ የማትጠልቀዋ ፀሐይ የምትባለው ታቦተ ጽዮን ያረፈችባት፣ ቅዱስ ጽዋ የተሰጣት፣ ግማደ መስቀሉ ያከበራት፣ ይኖርባት ዘንድ የመረጣት፣ የተመረጠች፣ የተከበረች፣ ለምስክርነት የተዘጋጀች ድንቅ ሀገር፡፡

ዓለት እንደ አሽከር የታዘዘባት፣ ቤተ መቅደስ ከጣሪያ ወደ መሠረት የተሠራባት፣ ገዳማት የተገደሙባት፣ አድባራት የተደበሩባት፣ ቅዱሳን የሚኖሩባት፣ ሳያቋርጡ ጸሎት የሚያደርሱባት፡፡

የአዘኑት መጽናኛ፣ የተቸገሩት መጠለያ፣ የተራቡት መጉረሻ፣ የታረዙት መልበሻ ናት፡፡ ጻዲቃን ይከትሙባታል፣ ተስፋ ያጡት ተስፋ ያደርጉባታል፣ በጨለማ ውስጥ የሚኖሩት ብርሃን አይተውባታል፣ ፍትሕ የራቃቸው ፍትሕ አግኝተውባታል፣ ጥበብን፣ ፍቅርን፣ ክብርን፣ ጽድቅን የሚፈልጉ ይፈልጓታል፣ ዓይናቸውን ይጥሉባታል፣ መልካሙን ኹሉ ያገኙ ዘንድ ይሄዱባታል፡፡ እርሷ ጥበብ የሚፈልቅባት፣ ክብር የሚገኝባት፣ ምስጢር የበዛባት ሀገር ናትና፡፡ ምድሯን ለዞረ፣ መልከዓምድሯን ለመረመረ ኹሉ ጥበብ በዝቶበታል፡፡ በተንቀሳቀሱበት፣ በረገጡት የእርሷ ምድር ኹሉ ያልተደረሰበት፣ ያልተመረመረ፣ ያልተነገረ ድንቅ ነገር ሞልቷል፡፡

ፈጣሪ ገነትን የሚያጠጡ አፍላጋትን ፈጠረ፡፡ ወተት ኾኖ የሚያጠጣውን ታላቁን አፍላግም በዚህችው ድንቅ ምድር ይፈልቅ ዘንድ መረጠ፡፡ ይህችም ምድር ገነትን ያጠጣ ዘንድ ውኃ የፈለቀባት የተመረጠች ድንቅ ምድር ናት፡፡ የአፍላጉም ስም ግዮን ይባላል፡፡ የተመረጠችውም ምድር ኢትዮጵያ፡፡

ግዮንን በኢትዮጵያ ወተትና ማር በሚፈስስበት፣ ነጭ ጤፍ በሚታፈስበት፣ ጥበብ በሚፈልቅበት፣ በጎጃም ክፍለ ሀገር በሰከላ ከግሽ ተራራ ግርጌ ይፈስ ዘንድ የምድርን በር ከፈተለት፡፡ ይህም አፍላግ (ወንዝ) ገነትን ወተት ኾኖ ያጠጣታል፡፡ የሚታየውን ምድርም ያረሰርሳል፡፡ ታላቁ ግዮን ከግሽ ተራራ ግርጌ መንጭቶ፣ ከምስጢራዊ ሐይቅ ከጣና ጋር ተገናኝቶ፣ በጣና ሐይቅ ላይ አልፎ ምድርን እያረሰረሰ ይወርዳል፡፡

ʺእግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን (ዔደን) ገነትን ተከለ፡፡ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፣ ለመብላትም መልካም የኾነውን ዛፍ ኹሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፣ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ። ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፡፡ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር። የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን (ኤፌሶን) ነው፤ እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል፤ የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፤ ከዚያም ሉልና የከበረ ድንጋይ ይገኛል። የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ኹሉ ይከብባል። የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፤ እርሱም በአሦር ምሥራቅ የሚሄድ ነው። አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው። እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው” እንዳለ መጽሐፍ ግዮን ከዔድን የሚመነጭ፣ ገነትን የሚያጠጣ፣ ውኃ ብቻ ሳይሆን ጥበብ የሚፈልቅበት፣ ስልጣኔ የሚገኝበት፣ ታሪክ የመላበት ታላቅ ወንዝ ነው፡፡

ይህ ወንዝ ከኤደን ይወጣል፣ ግዮን የሚወጣባት፣ ድንቅ የኾነች፣ ለታላቁ አፍላግ መገኛ የተመረጠች፣ በጥበብ የተጠበቀች ሀገር ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ግዮን ማለት የሚያስፈራ፣ ትልቅ ነጎድጓድ የመሠለ ድምጸት ያለው ነው ይላሉ አበው፡፡ ግዮን የወንዙን ታላቅነት የሚያስፈራውን ድምጽ፣ ያለውን ግርማ ሞገስ የሚገልጽ ስም ነውም ይሉታል፡፡ “ዐቢይ ወግሩም” ታላቅና የሚያስገርም ታላቅ ወንዝ ነው ግዮን ይላሉ፡፡

ግዮን (ጊሖን) ማለት “ዘየሐውር በኃል ወይርዕም ወደምፀ ማዩ ዐቢይ ወግሩም” ማለት ነው ይላሉ አበው፡፡ የውኃውን ብዛት፣ ያካሄዱን ኃይል የጩኸቱን ግርማ ፏፏቴውንና ተመማው ኃያል የሆነ ወንዝ ነው ግዮን፡፡ የግዮን ስም አንድ ብቻ እንዳልሆነና በቀደሙ ኢትዮጵያዊያን አባዊ፣ ዓባይ ተብሎ እንደሚጠራ ሊቀ ኂሩያን በላይ መኮንን ነግረውኛል፡፡ ይህም የወንዞች ኹሉ ታላቅ፣ ፊት አውራሪ ማለት ነው ይላሉ፡፡ ዓባይ የዛሬም መጠሪያው ነው፡፡ ከግሽ ተራራ ግርጌ በተከፈተለት የምድር በር ወጥቶ ግርማ ለብሶ ጉዞ የሚጀምረው ግዮን በጣና ላይ በማለፍ በግራና በቀኝ ሌሎች ወንዞችን እያስገበረ፣ እንደ ንጉሥ በወንዞች እየታጀበ፣ ጉልበቱን እየጨመረ፣ ውኃ ወደተራበበት፣ በረሃ ወደ ጠናበት ምድር ይጓዛል፣ ያን ምድርም ልምላሜ ይሰጠዋል፡፡

ግዮን ከምድር በር በሚወጣበት በዚያ ሥፍራ አቡነ ዘርዓ ብሩክ የሚባሉ ጻድቅ ሰው ነበሩ፡፡ እኒህ ሰው ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ፣ ሕግጋትን የሚያከብሩ፣ በጾምና በጸሎት የሚተጉ ነበሩ፡፡ እኒህ ጻዲቅ አባት ምስጢራት የተገለጡላቸው፣ በረከት የበዛላቸውም ናቸው፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን እርሳቸው በነበሩበት ዘመን ሀገር ይገዛ የነበረው ንጉሥ ሊያሥራቸው ፈለገ፡፡ ጭፍሮቹንም ያመጧቸው ዘንድ እርሳቸው ወደ አሉበት ላከ፡፡ በጠላቶቻቸው የሚሳደዱት አባት ጥበብን የሚመረምሩባቸው መጻሕፍት ነበሯቸው፡፡ መጻሕፍቱንም ለግዮን አደራ ሰጥተው ሸሹ፡፡ ከዓመታት በኋላም ወደ ሥፍራው ተመለሱ፡፡ በዚያም ጊዜ ʺ ኦ ግዮን ግሥኢ መጻሕፍትየ ” ግዮን ኾይ መጻሕፍቴን መልስ አሉት፡፡ ግዮንም መጻሕፍቱን መለሰላቸው ይላሉ አበው፡፡ ግዮን ታማኝ፣ ረቂቅ ምስጢር ያለበት፣ ውኃ ብቻ ሳይሆን ቅዱስ መንፈስ የሰፈረበት ነው ይባላል፡፡ አደራ መልሷል፣ ፍቅርና ክብርን አልብሷል፣ ስልጣኔን በዥረቱ ልክ አፍስሷል፡፡

ግዮን ታላቅ ክብር የሚሰጠው፣ የሚከበር ወንዝም ነው፡፡ በሠከላ ግሽ ተራራ ግርጌ የሚፍልቀው ግዮንን መምጣቱን የሚናፍቁት፣ አብዝተው የሚጠብቁት፣ ሕይወታቸው በእርሱ ላይ የተመሠረተ ብዙዎች ናቸው፡፡ ግዮን ገነትን የሚያጠጣ፣ የሚታየውን በረሃውን ምድርም ከችግር የሚያወጣ፣ ልምላሜና ደስታን የሚያመጣ ነው፡፡

“ግዮን ወተት ኾኖ ገነትን ካጠጣት
የግዮን መነሻ ኢትዮጵያ ምንድን ናት?” የኢትዮጵያን ምድር የሚያካልለው፣ ገነትን ወተት ኾኖ የሚያጠጣው ግዮን የተቀደሰ ወንዝ ከኾነ የተቀደሰውን ውኃ ያፈለቀችው፣ የተቀደሰውን ውኃ የታቀፈችው፣ በእልፍ ቅዱሳን ነገሮች የተከበበችው፣ አስቀድማ የተመረጠችው፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ተደጋግማ የተጠራችው ምድር ኢትዮጵያስ ምንድን ናት? ወተት የሆነ ውኃ ያፈለቀች፣ ገነትን ያጠጣች፣ መልካሙን ኹሉ የያዘች፣ በጥበብ የተጠበቀች፣ በኩራት የኖረች፣ ለማንም ያልገበረች፣ ለማንም ያልተንበረከከች፣ በአሸናፊነት ብቻ የተመረጠች ኢትዮጵያስ ምንድን ናት? የግዮን መነሻ፣ የታሪክ መዳረሻ፣ የስልጣኔ መናገሻ ኢትዮጵያስ ምንድን ናት?

በወርሃ ጥር በ13ኛው ቀን በታላቁ ወንዝ መነሻ የግዮን በዓል በድምቀት ይከበራል፡፡ በዚያው ቀን የአቡነ ዘርዓብሩክም ክብረ በዓልም ይከበራል፡፡ በዚያም ቀን ወደ ግዮን የሚጓዙት ብዘዎች ናቸው፣ የግዮን ምስጢር ሊመረምሩ ዓይናቸውን ወደ ግሽ ተራራ ግርጌ ያደርጋሉ፣ ጀሯቸውን ምስጢር ወደሚነገርበት፣ ጥበብ ወደሚፈስስበት ያዘነብላሉ፣ ልቦናቸውን በውበቱ ያስገዛሉ፡፡

ግዮን የኢትዮጵያን የረዘመ ታሪክ የሚዘክር፣ ቅድስናን፣ ታማኝነትን፣ ቀዳሚነትን የሚመሰክር፣ ምስጢሩ የረቀቀ፣ በዓለም ዳርቻዎች ኹሉ የታወቀ፣ ስልጣኔ እንደ ውኃው ሁሉ የሚፈስስበት፣ ከዥረቱ ጋር የሚጓዝበት፣ ዕውቀት የሚቀዳበት፣ ጥበብ የሚጠጣበት ነው፡፡ ለግዮን መፍለቂያ ከተከፈተው ከግሽ ተራራ ግርጌ መነሻን አድርጎ ታላቁን ወንዝ ቢከተሉት፣ በጥበብ ቢመረምሩት፣ በአስተውሎ ቢመለከቱት እልፍ ምስጢር አለ፡፡

ወተት ኾኖ ገነትን ከሚያጠጣው ከግዮን ጋር አብሮ የፈለቀ፣ አብሮ የረቀቀ፣ ጥበብ፣ ታሪክ፣ ስልጣኔ፣ አሸናፊነት፣ አንድነት፣ ቀዳሚነት አለና፡፡ ገነትን ከሚያጠጣው ወንዝ ለመጠጣት፣ ጥበብን ከምንጩ ለመቅዳት የሚሻ ኹሉ ወደ ሠከላ ግሽ ተረራ ግርጌ ይገስግስ፡፡ በዚያ ውስጥ የኢትዮጵያ ውበት፣ የምድር በረከት አለና፡፡ በዚያ ውስጥ ፍልስፍና ተጀምሮበታል፣ ስልጣኔ መሠረቱን አድርጎበታልና፡፡

ጥበብን ለማግኘት፣ የጥንት ስልጣኔዎችን ለመረዳት፣ ከወተቱ ለመጎንጨት ወደ ግዮን መነሻ፣ ወደ ግሽ ተራራ ግርጌ አቅኑ፡፡ ግዮንን ማየት፣ እርሱን መጎብኘት፣ ትናንትን መመልከት፣ የኢትዮጵያን ውብ መልክ መፈለግ ነውና፡፡ በቅዱሱ መጽሐፍ የሠፈረውን፣ የኢትዮጵያን ምድር የሚከበውን አፍላግ መመርመር ነውና፡፡ ሂዱ ጥበብን ተከተሏት፣ ሂዱ የግዮንን መነሻ መርምሩት፣ ሂዱ የኤደንን በር አንኳኩት፡፡

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ። https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ተቀጥቅጦ የተቀበረበት የካራ ምሽግ ድል እየተዘከረ ነው።
Next article❝ከሱዳን ጋር ተቀራርበን መሥራት እንደሚገባን መግባባት ላይ ደርሰናል❞ የሀገር መከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ.ር)