
እንጅባራ፡ ጥር 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በድምቀት ከሚከበሩ ሕዝባዊ በዓላት ውስጥ አንዱ የአገው ፈረሰኞች በዓል ነው። 82ኛውን የአገው ፈረሰኞች በዓል ጥር 23/2014 ዓ.ም በእንጅባራ ከተማ ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቅቋል። የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮም የአገው ፈረሰኞች በዓልን እንደ አንድ የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ በተለይ ለዳያስፖራው ለማስተዋወቅ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጋር በመሆን ከወዲሁ እየሠራ ይገኛል።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚዳንት ዶክተር ጋርዳቸው ወርቁ ዩኒቨርስቲው የቱሪዝም ዘርፉን ለማበረታታት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የአገው ፈረሰኞች ማኅበርንና የዘንገና ሐይቅን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግም እየሠራ ነውም ብለዋል። የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆንና በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ ዩኒቨርስቲው ጠንክሮ እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሂደትን ማስተማር የሚችል ማኅበር መሆኑንም ዶክተር ጋርዳቸው ገልጸዋል። የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የተሻለ አደረጃጀት እንዲኖረውና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን መሠራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።




ጥር 23/2014 ዓ.ም ዳያስፖራውን ጨምሮ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በበዓሉ እንዲታደም ጠይቀዋል።
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ሰብሳቢ ዓለቃ ጥላዬ አየነው ማኅበሩ 82ኛውን ዓመት ክብረ በዓል ለማክበር ዝግጅቱን አጠናቅቋል ብለዋል። የአገው ፈረሰኞች በታሪክ በፈረስ በመዝመት ጠላትን ድል አድርገዋል ነው ያሉት። በጠላት ላይ ከተገኘው ድል በኋላም የሰማእቱን ጊዮርጊስና የፈረሰኞችን ውለታ ለመዘከር የአገው ፈረሰኞች ማኅበር መመስረቱን አስረድተዋል። “እኛም የአባቶቻችን አደራ ተቀብለን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሁሉም ወረዳዎች የፈረሰኛ ማኅበር አባል ማፍራት ችለናል” ብለዋል።
ጠላት አማራ ክልልን ለማጥፋት በተነሳበት ጊዜ የማኅበሩ አባላት መዝመታቸውን አስታውቀዋል። ማኅበሩ በኢኮኖሚ የህልውናውን ዘመቻ መደገፉንም ተናግረዋል። የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዘርፈ ብዙ ገድል እንዳለውም ሰብሳቢው አስረድተዋል። በእድሜ አንጋፋ የሆነው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የተጣላን በማስታረቅ የተለያዩ ማኅበራዊ ተግባራትን እየፈጸመ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
መንግሥት ማኅበሩን በዩኔስኮ በማስመዝገብ ብሔረሰብ አሥተዳደሩን ስም እንዲያስጠራም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ እምቢአለ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የነፃነት ተምሳሌት ነው ብለዋል። ቢሮው በዓሉን እንደ ሌሎች በዓላት ሁሉ የሚንከባከበው፣ የሚያሳድገውና የሚደግፈው በዓል ነውም ብለዋል። ማኅበሩ ከአማራና ከኢትዮጵያ አልፎም የመላ ጥቁር ሕዝቦች መለያ ነውም ብለዋል። በዓሉን ለማክበር ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ነው ያሉት።
ማኅበሩ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
ኀላፊው እንዳሉት ማኅበሩ ከክብረ በዓልነት አልፎ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆንም ይሠራል። ሌሎች የመንግሥት ተቋማትም ከአገው ፈረሰኞች ማኅበር የዴሞክራሲ ሥርዓትን መማር አለባቸው ብለዋል። ማኅበሩ ሁሉንም ያካተተ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የአገው ፈረሰኞች ማኅበርን አስመልክቶ ሳይንሳዊ ጥናት ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል። ሁሉም ዜጋ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ክብረ በዓል ጥር 23 በእንጅባራ መጥቶ እንዲጎበኝ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንግዳ ዳኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በኢትዮጵያ ደረጃ አንጋፋ ማኅበር ነው ብለዋል። ማኅበሩ ከ59 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉትም ጠቁመዋል። ማኅበሩ ለአካባቢው ማኅበረሰብ በሐዘንም ሆነ በደስታ ወቅት የቆመ መሆኑን አንስተዋል። የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ጠላትን ለመደምሰስ በተደረገው ጥረት ሲደግፍ እንደነበረም አስታውቀዋል።
ማኅበሩን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር እየተደረገ ነው ብለዋል። በዓሉ እንዲመዘገብም ሁሉም አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል። በዓሉ የዓለም ቅርስ መሆን እንዳለበት አቶ እንግዳ ገልጸዋል። ማኅበሩ እስከ ፌዴራል ድረስ እውቅና ቢያገኝም በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረት ግን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓሉ የእኔ በዓል ነው በማለት ወደ እንጅባራ በመምጣት እንዲያከብር ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።