“የታጠቅነው ዘመናዊ መሳሪያና ቴክኖሎጂ ዒላማውን ለይቶ የሚመታ በመሆኑ ሰላማዊ ዜጎች የጥቃት ሰለባ አይሆኑም”ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

149
ጥር 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ)አየር ኃይላችን የታጠቀው መሳሪያና ቴክኖሎጂ ዒላማውን ለይቶ የሚመታ በመሆኑ ሰላማዊ ዜጎች የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ አይችሉም ሲሉ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ፡፡
አሸባሪው ህወሃት “የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው” ሲል የሚያቀርበውን ውንጀላ ከእውነት የራቀ ብለውታል።
በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ ደማቅ መርኃግብር በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የኅልውና አደጋ በመመከት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እውቅናና ሽልማት መበርከቱ ይታወሳል።
በመርኃግብሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የላቀ አመራርነት ላስመዘገቡ የጦር መኮንኖች የ’ዓድዋ ጀግና ሜዳይ’ የሸለሙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አንዱ ናቸው፡፡
ሌተናል ጄኔራል ይልማ ከጦር መኮንንነት በተጨማሪ ምርጥ አብራሪ መሆናቸውም በሽልማት መርኃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአየር ኃይሉን ዝግጁነትና ብቃት የሚያጎለብቱ የለውጥ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህም አየር ኃይሉ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የኅልውና አደጋ በብቃት በመመከት ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲያበረክት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
አየር ኃይሉ በኢትዮጵያ የአየር ክልል ከየትኛውም ወገን የሚቃጣን ጥቃት ለመመከትና አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ በሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰው ኃይልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይበልጥ እየተደራጀ ነው ያሉት ዋና አዛዡ፤ ‘የታጠቅነው ዘመናዊ መሳሪያና ቴክኖሎጂ የተሰጠውን ዒላማ በብቃት የሚመታ በመሆኑ በምንም መልኩ ሰላማዊ ዜጎች የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ አይችሉም’ ብለዋል።
ከዚህ አኳያ የአሸባሪው ህወሓት አመራሮችና ደጋፊዎች የኢትዮጵያ አየር ኃይል “በትግራይ ክልል በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው” በሚል የሚያሰራጩት መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አየር ኃይሉ ሕዝባዊ መሰረት ያለውና በጠንካራ ሥነ ምግባር የተገነባ በመሆኑ የትኛውም አይነት ኦፕሬሽኖች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡
የአየር ኃይሉ ዘመናዊ ትጥቆች ማንን እና ምን መምታት እንዳለብን በዓይናችን አይተን እንድንወስን የሚያደርጉ በመሆናቸው በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ሊፈጸም አይችልም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ህጻናትን የያዙ እናቶችን ጭምር አስገድዶ በጦር ካምፕ ውስጥ በማስገባትና የጥቃት ዒላማ እንደሆኑ አስመስሎ ፊልም በመቅረጽ እንደሚያሰራጭ ሌተናል ጄኔራል ይልማ ተናግረዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎችም የራሳቸው የኾነ መለዮ የሌላቸው በመሆኑ የቡድኑ አመራሮች በጦርነቱ የሞቱባቸውን ታጣቂዎች አስከሬን በመሰብሰብ ሰላማዊ ዜጎች እንደተገደሉ አስመስለው ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማደናገር እየጣሩ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
የአየር ኃይሉ ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያን በሚመጥንና ኢትዮጵያዊያንን በሚመስል መልኩ የተገነባ እንዳልነበረ፤ በአንድ አካባቢ ሰዎች ታጥሮ ለአንድ ፓርቲ ኅልውና ሲሠራ እንደቆየም አንስተዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በአጭር ጊዜ ለታላቅ ሀገር የሚመጥንና የኹሉም ኢትዮጵያዊያን የኾነ ተቋም መገንባት መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
ይህን ተከትሎ ከኹሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ወጣቶች ተቋሙን በመቀላቀል ስልጠና እየወሰዱ መሆኑንም ሌተናል ጄኔራል ይልማ ተናግረዋል፡፡
የአየር ኃይሉ የኢትዮጵያ የአየር ክልል ከደኅንነት ስጋት ነጻ እንዲኾን በመጠበቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያለምንም ችግር የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ ቀን ከሌት እየሠራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ተቋሙን በጥናትና ምርምር በመታገዝ ይበልጥ ለማዘመን አዳዲስ አሠራሮች ወደ ትግበራ እንደሚገቡም አንስተዋል፡፡
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
Previous articleበጥምቀት በዓል ላይ በቡራዩ ከተማ አስተዳደር ወይብላ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ላይ የተፈጸመውን አስነዋሪ ድርጊት እንደሚያወግዝ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።
Next articleበስድስት ወራት ብቻ ከ2 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች ተሞክረዋል።