
ጥር 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በዓለም ደምቃ እንድትታይ ከሚያደርጓት በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ አልፏል። በበዓለ ጥምቀቱ የታዩት ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊና ማኅበራዊ ዕሴቶች በዓሉ የኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቀ ውብ አብሮነትንም ለዓለም ያሳየ ሆኗል።
በዓሉ በመላ ሀገሪቱ በሰላም እንዲከበር ኅብረተሰቡና የጸጥታ አካላት ላደረጉት አስተዋጽዖ መንግሥት ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀርባል።
በዓሉ የኢትዮጵያውያንን መፋቀር፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሰላም በሚገልጽ መንገድ እንዳይከበር የተለያዩ አካላት የሸረቧቸውን ሴራዎች ሕዝቡና የጸጥታ አካላት ተናብበውና ተቀናጅተው አክሽፈውታል።
ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ ክንውኖች ከፊታችን አሉ። እነዚህ ክንውኖች እንዳይሳኩ የኢትዮጵያን ገጽታ ማበላሸት የፈለጉ አካላት የጥምቀትን በዓል በመረበሽ ተልኳቸውን ለማሳካት ሞክረው ነበር። ነገር ግን አልተሳካላቸውም።
የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው የመጡት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የማኅበራዊ መስተጋብሩ አካል በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች ተገኝተው በዓሉን አድምቀዋል።
የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ በዓልነቱ ባሻገር ለኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ግንኙነት፣ ለቱሪዝም መስህብነትና ኢትዮጵያን ለዓለም በማሳየት ታላቅ ሚና አለው። በዚህም የተነሣ ከበዓሉ ቀደም ብሎ በተደረገ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት የሃይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው መሥተዳድር አመራሮች፣ የጸጥታ አካላትና ወጣቶች በጋራ በመሥራት በዓሉ በአብዛኛው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ተችሏል።
የጥምቀት በዓል በመላ ኢትዮጵያ በደመቀና በሰላማዊ መንገድ ቢከበርም በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እና በቡራዩ አዋሳኝ ወይ ብላ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ በተፈጠረው ችግር በዓሉ መስተጓጎሉና በሰዎች ላይም ሞትና ከባድ ጉዳት መድረሱ ታውቋል።
በዓሉ በተገቢው መንገድ ባለመከበሩ፣ እንዲሁም በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልፃል። መንግሥት በስፍራው የተፈጠረውን ክስተት በማጣራት ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለሕግ እንደሚያቀርብ ያስታውቃል።
ለዘመናት የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ እንዲሁም የጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብራችን ማሳያ በሆኑ እንደ ጥምቀት በዓል ያሉ ሀብቶቻችንን ለማደብዘዝ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር ይከሽፋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።