“ጎንደር አባ ጃሌ ከግንቡ ደርሼ፤ ያለዕድል አይሆንም መጣሁ ተመልሼ።”

225

ጎንደር: ጥር 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አባ ጃሌ ተክለሐይማኖት በጎንደር አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ጣራው ታድሶ ቆርቆሮ ሲለብስ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን ነው ይባላል። ታሪኩን በሌላ ጊዜ በሰፊው የምናየው እና በኖህ መርከብ አምሳል የተሠራው ጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ጎንደርን ከሸዋ አንሰላስሎ ዘመናትን እንደዘለቀው ሁሉ አባ ጃሌ ተክለሐይማኖትም ላስታን ከበጌምድር ያቆራኘ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ነው።
ጎንደር ስትነሳ አብረው ከሚወሱት ነገሮች መካከል አንዱ “ኧረ ባባጃሌው” የሚለው የጎንደሮች ተረክ ነው። ጎንደሮች በነገሮች ሁሉ ሲደመሙ ወይም በዘፈኖቻቸው ለጎንደር ውዳሴ ሲያንቆረቁሩ “ኧረ ባባጃሌው” ማለትን ያዘወትራሉ። ለመሆኑ አባጃሌው ማን ነው? የሚል በሳል ጠያቂ ይኖራል።
ኢትዮጵያውያን “ነገርን ከሥሩ፤ ውኃን ከጥሩ” ይላሉ። አባ ጃሌ ተክለሐይማኖት ከጎንደር ጥንታዊ እና ታሪካዊ አብያተክርስቲያናት መካከል አንዱ ነው። የተመሠረተውም በአድያም ሰገድ እያሱ ልጅ በሆኑት በመናኔ መንግሥት ተክለሐይማኖት በ1763 ዓ.ም እንደሆነ ይነገራል። የላስታ ገዥ የነበሩት ደጃች (ደጅ አዝማች) ወንድወሰን መሸሻ ንጉሡን ለማግኘት እና ግብር ለመክፈል ወደ ጎንደር ጎራ ይላሉ። በርካታ አሽከሮቻቸውን እና ጭፍሮቻቸውን ያስከተሉት ደጃች ወንድወሰን ንጉሡን ለእርሳቸው እና ለጭፍሮቻቸው ማረፊያ ድንኳን የሚተክሉበት ቦታ እንዲሰጧቸው ጥያቄ ያቀርባሉ።
ንጉሡም ለደጃች ክብር የሚመጥን ቦታ ለመስጠት አስበው በእጨጌ ቤት እና በእርግብ በር መካከል ያለውን ክፍት ቦታ ይሰጧቸዋል። ደጅ አዝማች ወንድወሰንም በተሰጣቸው የክብራቸው መገለጫ ቦታ ድንኳናቸውን አስተክለው እርሳቸው እና ልዑካቸውን በዚያ ያሳርፋሉ። ቦታውን አብዝተው የወደዱት ደጃችም ለማረፊያ በተሰጣቸው ቦታ ላይ ለጎንደሮች ፍቅር እጅ መንሻ እና ለስማቸው ማስታወሻ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ንጉሡን ፈቃድ ጠይቀው ጥያቄያቸው በንጉሡ ዘንድ ሞገስን ያገኛል።

ደጅ አዝማች ወንድወሰንም በተሰጣቸው የክብር ቦታ ባለአምድ ወርቅ ቤተክርስቲያን ያስገነባሉ። የእኛ ሰው እንደሚለው አጋጣሚው “ሰኔ እና ሰኞ” ይሆንና በአቡኑ ተባርኮ የገባው ጽላት በመናኔ መንግሥት ተክለሐይማኖት ዘመነ ንግሥና የተክለሐይማኖት ታቦት ይሆናል። የደጅ አዝማች ወንድወሰን የፈረስ ሥም “አባ ጃሌ” ይባል ነበርና የቤተ ክርስቲያኑ ስያሜም አባ ጃሌ ተክለሐይማኖት ተባለ ይሉናል ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን።
150 ሊቃውንት የሚያገለግሉት አባ ጃሌ ተክለሐይማኖት በ1880 ዓ.ም አካባቢ ድርቡሽ ገብቶ ሳለ ቤተ ክርስቲያኑን ሲያዩት ሰፊ ስለነበር ግምጃ ቤት አድርገውት ነበር ይባላል። በዘመኑ በብዙው የተጎሳቆለው የአባ ጃሌ ተክለሐይማኖት ቤተ ክርስቲያን እድሳት ይፈልግ ነበር። በ1925 ዓ.ም የደብሩ አለቃ የነበሩት አለቃ እልፍነህ ወልደተክሌ የራስ ካሳ ዳርጌ ልጅ ወንድወሰን ካሳ ጎንደርን እንደሚያስተዳድሩ ሲሰሙ ከፊታቸው ቀርበው “ጎንደር አባ ጃሌ ያባትዎ ቤተ ክርስቲያን ነው። አሁን ሊፈርስ ተቃርቧልና እንዲያሳድሱት” ሲሉ ይነግሯቸዋል። (ያባትዎ ያሉት ታላቅዎ ለማለት እንጂ የስም መመሳሰል መሆኑን ልብ ይሏል)
ደጅ አዝማች ወንድወሰንም ቤተ ክርስቲያኑን በአካል ተገኝተው ከጎበኙት በኋላ እንዲታደስ ይወስናሉ። በደጅ አዝማች ወንድወሰን ትዕዛዝ ቀኝ አዝማች ተክሌ በየነ አማካኝነት በጥንታዊው የአማራ ምድር ሰቲት ሁመራ በኩል ቆሮቆሮ በግመል አስጭነው አስገብተው በ1926 ዓ.ም ታደሰ። ይኽም አባ ጃሌ ተክለሐይማኖት በጎንደር የመጀመሪያው የቆርቆሮ ክዳን ያለው ቤተ ክርስቲያን ለመሆን በቃ ይባላል።
አባ ጃሌ ተክለሐይማኖት ቤተ ክርስቲያን በመላው በጌምድር ሥሙ የናኘ ቤተ ክርስቲያን ሆነ። ጎንደር ስትነሳ አባ ጃሌ ሳይወሳ የማይታለፍ ነው። አባ ጃሌ በጎንደሮች ዘንድ መማያም ማምረሪያም ስም ነው። ሲምሉ “አባ ጃሌን!” ይላሉ፤ ሲያመሩም ሆነ ሲያቀነቅኑ “ኧረ ባባጃሌው” ማለት የተለመደ ነው።
ከዕለታት በአንድ ቀንም አንዲት ወይዘሮ ከወገራ ጎንደር ትመጣና ዘመዶቿን ጠይቃ እና የፋሲል ግቢን ጎብኝታ “አጃይብ ከተማ” እያለች ወደ ወገራ ትመለሳለች። በአካባቢዋም በጎንደር ስላየችው ሁሉ ስታወራ በወቅቱ ሥመ ገናና የነበረውን እና የቆርቆሮ ክዳን የለበሰውን ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን አባ ጃሌ ተክለሐይማኖት ቤተ ክርስቲያንን አየሽ ወይ? እየተባለች በብዙ ሰው መጠየቋ የከነከናት እና አባ ጃሌን አለማየቷ ያበሳጫት ያች ወይዘሮ
“ጎንደር አባ ጃሌ ከግንቡ ደርሼ፤
ያለዕድል አይሆንም መጣሁ ተመልሼ።” ስትል ተቀኘች፡፡

ጎንደር ታይታ የማትጠገብ፤ ተመርምራ የማትገለጥ ሚስጥር ከተማ ነች። በአንድ ጥምቀት ጎንደርን መረዳት “ዓባይን በጭልፋ” እንደሚሉት ብሂል ነው። ጎንደር የታሪክ ድርሳን፣ የቅርስ ሙዚየም እና የባህል አውደ ርዕይ ናት። ያለትርጉም የወጣ ሥም የለምና ለምን ተባለ? ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል። ያለምክንያት የከበረ ቦታም አይኖርምና መቼ እና እንዴት? እያሉ ማንሰላሰልን ይጠይቃል። ጎንደር የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ መናገሻ ብቻ ሳትሆን የጥንቱ ማስታወሻ ከተማም ናትና መመርመር፣ መፈተሽ እና ስለጎንደር ጉባኤ መቀመጥ ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል።
ጎንደርን መመርመር ለጎንደር ሳይሆን ለኢትዮጵያም ይበጃል። ጥምቀትን ብቻ ታድሞ መመለስ ግን እንደዛች የወገራ ወይዘሮ “…ያለዕድል አይሆንም መጣሁ ተመልሼ” ሳያስብል አይቀርም። ጎንደርን “ዐይናሚት ጎንደሬ” እያላችሁ ከፒያሳ እስከ አዘዞ፣ ከጎሃ እስከ ቀሃ፣ ከምንዝሮ እስከ ቸቸላ፣ ከወለቃ እስከ አንገረብ፣ ከማራኪ እስከ ጃን ተከል ተንከራተቱባት።
ታዘብ አራጋው -ጎንደር
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበፊንላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።
Next article❝የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ያደርጋል❞ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ