
ጎንደር፡ ጥር 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጎንደር እንደ በኩር ልጅ ሥያሜዋ ብዙ ነው። በብዙሃኑ ዘንድ እናታለም የሚል የፍቅር መጠሪያ የተቸራት ጎንደር “አበቅ የለሽ” በሚል መጠሪያም ትታወቃለች። በርካቶች አበቅ የለሽ የሚለው መጠሪያ ለግለሰብ እና ስለግለሰብ የተቸረ ይመስላቸዋል። ነገር ግን አበቅ የለሽ ግዕዝን ከአማርኛ ያጣመረ ሚስጥረ ብዙ ሌላኛው የጎንደር ከተማ የፍቅር ሥም ነው።
አበቅ የሚለው ቃል የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም “እንከን” ማለት ነው ይሉናል ሊቃዎንተ ቤተ ክርስቲያን አበው። “የለሽ” የአማርኛ ቃል ሲሆን “አበቅ የለሽ” ግዕዝ ከአማርኛ ተዋህደው “እንከን አልባ ከተማ” የሚል ትርጓሜ ይሰጣል ብለውናል።

ይኽች እንከን አልባ ከተማ ለብዙ ጊዜ የለፋችበትን “ጥምቀትን በጎንደር” ያለእንከን እያጠናቀቀች ነው። ከመላው ዓለም የተሰባሰቡት ወዳጆቿ በተዋበች ቀሚስ እና በካሳ ጃኖ እጂጉን አድምቀውታል።
ዛሬ በጎንደር ካሰቡት ቦታ መድረስ እውነት ለመናገር “የህልም እሩጫ ነው” ትራንስፖርት ዝግ ነው፣ እግረኛው ብዙ ነው፤ በእነዚህ ሁሉ ላይ የጎንደር ሕንፃዎች አምሳያ ቀለም ይበዛቸዋል። በዚህ ሁሉ መካከል ግን “ዮሐንስ ሰላም ገባ? ባታ ወደ ባዕቷ በሰላም ተመለሰች?” ለሚል የእኔ ቢጤ እንግዳ ጠያቂ “ጎንደር ሁልጊዜስ ሠላም አይደለች!” የሚል መላሽ መሥማት እንዴት ያበረታል!
በጎንደር 44ቱ ታቦታት ተረት ሳይሆን እውነት ነው። ከ44ቱ ታቦታት ወደ ፋሲል መዋኛ የሚወርዱት ታቦታት 8 ናቸው። ከመንበረ መንግሥት መድኃኒዓለም እስከ የፊት ቅዱስ ሚካኤል፣ ከአጣጣሚ ቅዱስ ሚካኤል እስከ እልፍኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ከደብረ ህሩያን አባጃሌ ተክለ ሃይማኖት እስከ ቅዱስ ፋሲለደስ፣ ከቀሃ ኢየሱስ እስከ ደብረ ጽጌ ዮሐንስ መጥምቅ በአንድ ላይ ያድራሉ። ከሥምንቱ ስድስቱ በሰላም ወደ መንበራቸው ተመልሰዋል።

ፊት ቅዱስ ሚካኤል እና አጣጣሚ ቅዱስ ሚካኤል ዛሬም በጥምቀተ ባህሩ ያድራሉ። ነገ ሁለቱ ታቦታት ወደ መንበራቸው በሠላም ይመለሳሉ። ጎንደርም ከፀሐይ እስከ ጨረቃ ብዙ የለፋችበትን ጥምቀት በክብር አጠናቃ “የከርሞ ሰው ይበለን” ትላለች።
ማታም በእንኮየ መሥክ ተንከራተን እና በጃን ተከል ተንከላውሰን አዲስ ያልነውን ሁሉ እናደርሳለን። የንጉስ ራት ዘገባም ይኖረናል።
ታዘብ አራጋው -ጎንደር
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
