
ጎንደር፡ ጥር 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጎንደር በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች መካከል አንዷ ናት። ከተማዋ የጥበብ፣ የታሪክ እና የቅርስ መዲና ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የውጭ ጎብኝዎችን ቀልብ ትስባለች። ሁልጊዜም በየዓመቱ ጥር 11 የሚከበረው የጥምቀት በዓል ደግሞ ጎንደርን የተለየች የጎብኝዎች መዳረሻ ያደርጋታል።
ዓለም አቀፋ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረውበት ቆይተዋል። “ልደትን በላልይበላ” እና “ጥምቀትን በጎንደር” በተለያዩ ምክንያቶች ተዳክሞ የቆየውን ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ እንዲያገግም ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። አንዳንድ የውጭ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት እና የሽብር ቡድኖቹ የውጭ ክንፍ አበጋዞች በኢትዮጵያ ሰላም የሌለ ለማስመሠል እና የሽብር እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል በውጭው ዓለም የሌለ እና የተለየ ሥዕል ሲሰጡ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኘችው እና ጥምቀትን በጎንደር ስትታደም ያገኘናት የደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ቺሊ ተወላጇ ካሚላ ፍራንኮቪች “ጥምቀትን በጎንደር የአንዳንድ ምዕራባውያን ሚዲያዎችን ሴራ ያከሸፈ ሁነት ነው” ብላለች። ጎንደር ጥንታዊ የጥበብ እና የባሕል ከተማ መሆኗን እሰማ ነበር ብላለች፡፡ ካሚላ ከቀሪው ዓለም የተለየ፣ ፍጹም ሀገር በቀል፣ ማራኪ እና አስደሳች የጥምቀት በዓል ሥርዓትን አይቻለሁ ብላለች። ካሚላ ፍራንኮቪች ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ አንድነታቸውን ጠብቀው እና ጥንታዊ ቅርሶቻቸውን ጠብቀው እንደሚቀጥሉ ተስፋ አለኝ ብላለች።

ኢትዮጵያ ሲመጣ ይኽ ለሁለተኛ ጊዜው እንደሆነ የነገረን እና ከሀገረ ጣሊያን የመጣው ዲኖ ሉፖ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን እምቅ ተፈጥሮ፣ ታሪክ እና ቱባ ባሕል እንዳላቸው ገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሰላም እንደራቃት ብዙ ጊዜ እንደሰማ የነገረን ዲኖ እውነታው ግን ፍፁም የተለየ እና ጎንደርም የተረጋጋች ከተማ ሆና እንዳገኛት ነው የተናገረው። ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም ሰላማዊ ዜጋ ገብቶ መውጣት እንደሚችልም አረጋግጫለሁ ብሏል።
የተለየ ክስተት እና የሚያስፈራ እንቅስቃሴ በቆይታው እንዳላጋጠመው የገለጸው ጣሊያናዊው ዲኖ ዲፖ በቆይታው ከጎንደር ውጭ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን የመጎብኘት ፍላጎት እንዳለውም ነግሮናል።
ጎብኝዎቹ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ሰላም ራሳቸው ጠብቀው፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለጎብኝዎች ምቹ አድርገው እና ማንነታቸውን ጠብቀው በድጋሜ ለማየት ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። ለሁሉም የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ለጥምቀት በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው -ከጎንደር
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
