የኢትዮጵያዊነት ደወል!

121

ጎንደር፡ ጥር 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጠባብ የዘረኝነት መንፈስ ለናወዙ ሰነፎች ጥምቀትን በጎንደር መመልከት ድንጋጤን ይፈጥራል። ኢትዮጵያዊነት በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በገቢርም ነፍስ ዘርቶ ሥጋ ነስቶ በጥምቀት ይታያል። ብርዱና ቅዝቃዜው ያልበገራቸው ምዕመናን ታቦታቱን ከበው በዙሪያው ተቀምጠዋል።
ወጣቶች እና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ዝማሪያቸው እና ውዳሴያቸው እስከ አፅናፍ ዘልቆ ይሰማል። የካሕናቱ ዝማሬ አስፈሪውን ጽልመት የብርሃን ጸዳል አላብሶታል።

የፋሲል መዋኛ በኢትዮጵያዊነት ግርማን ተጎናጽፏል። ከመላክ ሠገድ እስከ አጥናፍ ሠገድ፤ ከሥልጣን ሰገድ እስከ ዓለም ሰገድ፤ ከአዕላፍ ሰገድ እስከ አዲያም ሰገድ፤ ከልዑል ሰገድ እስከ ራሥ ሰገድ፤ ከፀሐይ ሰገድ እስከ አድባር ሰገድ፤ ከመሲህ ሰገድ እስከ ብርሃን ሰገድ፤ ከአድማስ ሰገድ እስከ ኃይል ሰገድ የበዙ ሥመ መንግሥታትን ያፈራረቀችው ጎንደር ዛሬ ደግሞ ሥመ መንግሥቷ ኢትዮጵያዊነት ሆኗል።

ኢትዮጵያዊነት ከምሽት እስከ ንጋት፤ ከቀን እስከ ሌሊት አብዝቶ ሲጎሰም እና ሲሰበክ ውሏል፤ አድሯል። የሌሊቱ ማሕሌት እንቅልፍ እና ቅዝቃዜ ላልበገረው ምዕመን ተጨማሪ ጉልበት ሆኖታል። የንጋቱ ቅዳሴ የረጅሙ ጽልመት መገባደድ ተብሲር ነው።

የጠዋቷ ፀሐይ መውጣት በጥምቀተ ባሕሩ ለተሰባሰቡት እንግዶች ምክንያት ሆኗል። ትምሕርት በቤተ ክርስቲያን አባቶች እና መልዕክት በእንግዶች አብዝቶ ይሰማል። በመጨረሻም ጥምቀቱ በብጹዓን አባቶች ቡራኪ ተጀምሮ በአራቱም አቅጣጫ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ደረሰ። ጥምቀትም እስከቀኑ የታቦታት ሽኝት ድረስ በዚህ መልኩ ደምቆ ተጠናቀቀ።

ዘጋቢ፡-ታዘብ አራጋው-ጎንደር

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“የ2014 ዓ.ም ጥምቀትን ስናከብር መለያየትን በአንድነት፣ ጥላቻን በፍቅር፣ መፍረስን በመገንባት፣ ክፋትን በደግነት፣ ተንኮልን በቀናነት፣ ድህነትን በብልጽግና ድል በማድረግ ሊሆን ይገባል” የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ
Next articleየኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡