
ጎንደር፡ ጥር 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ጎንደር ጥምቀት በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ለክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ሁሉ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡ የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል በአንጻራዊ ሰላም እና እፎይታ እንዲከበር ላደረጉ ጀግኖቹ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ፋኖ፣ ሚሊሻ እንዲሁም ለአፋር እና ለመላው የክልል ልዩ ኀይሎች ምስጋና እና አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጥምቀትን በጎንደር ማክበር መልዕክቱ እና ስሜቱ የተለየ ድባብ እንዳለው ነው የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ፤ ጥምቀት በጎንደር በፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር ሳይቋረጥ ድምቀት እና ውበቱ የበለጠ እየሰፋ እና እያደገ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ጥምቀትን በጎንደር ማክበር ትዕይንቱን፣ አውዱን፣ አቀራረቡን፣ አፈጻጸሙን፣ በተሳታፊው ብዛት እና ስብጥር የሚፈጥረው የተለየ ድባብ የሚያስደስት፣ የሚመስጥ እና የተለየ እንደሚያደርገውም አንስተዋል፡፡
ዶክተር ይልቃል ጎንደር የከተማነት የሥልጣኔ፣ የሥነ ሕንጻ፣ የሥነ መንግሥት እና የኪነ ጥበብ ታሪካዊ መሰረቶች ጋር ተዋህዶ ጥምቀትን በጎንደር ማክበር ልዩ ውበት ይፈጥራል ብለዋል፡፡ የዘመናዊ ኢትዮጵያ ጅምር፣ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ፍላጎት፣ የአንድነት አስፈላጊነት ድምጽ ፈልቆ የተናኘው በአፄ ቴዎድሮስ አፍላቂነት ከጎንደር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የጎንደር ባሕረ ጥምቀት ተብሎ ይጠራ የነበረው ሥፍራ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ቀድሞ መጠሪያው ፋሲለደስ ባሕረ ጥምቀት ተብሎ እንዲጠራም ተወስኗል ብለዋል፡፡
ዲያስፖራው በሀገሩ ላይ የሚደረገውን ጫና በመቃወም እያደረው ላለው እንቅስቃሴም ርእሰ መሥተዳደሩ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
መላው ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን አጠናክረው በመቀጠል በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን መርዳት እና ተቋማትን መልሶ መገንባት ይገባልም ብለዋል፡፡
ጥምቀት በጎንደር ከፍተኛ የፌዴራል፣ የክልል እና በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ እንግዶች እና ዲያስፖራው በታደሙበት በድምቀት ተከብሯል፡፡
ዘጋቢ፡-የማነብርሃን ጌታቸው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com
