
ጥር 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሚታየውና የማይታየው ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ አምላክ በማይመረመር ጥበብ ይኖር ነበር፡፡ እርሱ መኖሪያው ረቂቅ ነውና ከዓለማት በፊት በጥበቡ ይኖር ነበር፡፡ ዓለማትን በድንቅ ጥበብ ፈጠራቸው፤ አስዋባቸው፤ ባረካቸው፤ ከዓለም በፊት የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር እርሱ ጌታ ከፍጥረታት መካከል የሰውን ልጅ በአርዓያው በአምሳሉ ፈጠረው፤ አከበረውም፡፡ የመጀመሪያው ሰው አዳም ነበር፡፡ ገነትም ለእርሱ ለመኖር የተመቸች ረቂቅ ሥፍራ ነበረች፡፡
በገነት ሲኖርም ሕግና ስርዓት ያከብር ዘንድ ታዝዟል፤ አዳም ግን ከግራ ጎኑ ከሔዋን ጋር ኾኖ ሕግና ስርዓትን አፈረሰ፤ አትቅመስ የተባለውን ቀመሰ፤ የተከለከለችውን እጽ ጎረሰ፡፡ ሕጉን የሻረው፣ ስህተት የሠራው አዳምም ተፈረደበት፤ ገነት ተዘጋችበት፤ ገነት በተዘጋችበት፣ የክብር ልብሱ በተገፈፈበት፣ ክብርና ሞገስ በራቁት ገዜ አምርሮ አለቀሰ፤ ፈጣሪው ይምረው፣ ይቅር ይለው ዘንድ እያለቀሰ ለመነው፤ ጌታም ልመናውን ተቀበለው፡፡ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ገባለት፡፡
ቃል ኪዳኑን የሚፈጽመበት ዘመን ደረሰ፣ ከማርያም ተወለደ፣ በጥበብና በሞገስ አደገ፣ በምድርም ተመላለሰ፡፡ የነብያት ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ሰላሳ ዘመን ሲሞላው ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወረደ፡፡ አበው ጥምቀት ማለት ʺአጥመቀ” ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ʺመነከር፣ መዘፈቅ፣ ከውኃ ገብቶ መውጣት” የሚል ትርጓሜን የያዘ ነው ይላሉ፡፡ ሚስጥራዊና ሃይማኖታዊ ትርጓሜው ደግሞ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ልጅ መሆን ማለት ነው ይላሉ፡፡
ዲያቢሎስ አዳምና ሔዋንን ቃል ያስገባበት የእዳ ደብዳቤ በባሕረ ዮርዳኖስ ነበረ፣ ክርስቶስም የአዳምና የሔዋንን የእዳ ደብዳቤ ያጠፋላቸው ዘንድ በሰላሳ ዘመኑ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወረደ፡፡ ለምን በሰላሳ ዘመኑ ካሉ አዳም የተፈጠረው እንደ ሰላሳ ዓመት ጎልማሳ ኾኖ ነው፡፡ ጌታም የቀደመ ልጅነቱን ይመልስለት ዘንድ በሰላሳ ዘመኑ ወደ ዮርዳኖስ ወረደ፡፡ በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። በነቢዩ በኢሳይያስ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና። ራሱም ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፡፡ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም የበረሀ ማር ነበረ። ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ ሀገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።
ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ ዮርዳኖስ በወረደ ጊዜ ዮሐንስን አጥምቀኝ አለው፡፡ ዮሐንስ ግን አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን? አገልጋይ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ ጌታ ወደ አገልጋዩ ይሔዳልን ብሎ አይኾንም አለው፡፡ አንተም መጥምቀ መለኮት እየተባልክ ትኖራለህ፤ እኔም በፍጡሩ እጅ ተጠመቀ እየተባኩ ትህትናዬ ይነገራል አለው፡፡ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ያን ጊዜ ፈቀደለት። ኢየሱስ ክርስቶም በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፡፡
ኢየሱስ ክርሰቶስ በእደ ዮሐንስ በባሕረ ዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ ዓለም በብርሃን ተመላች፡፡ ʺአቤቱ፣ ውኆች አዩህ፣ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፤ ጥልቆች ተነዋወጡ፤ ውኆችም ጮኹ። ደመኖች ድምፅን ሰጡ፤ ፍላጾችህም ወጡ። የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበረ፤ መብረቆች ለዓለም አበሩ፤ ምድር ተናወጠች ተንቀጠቀጠችም። መንገድህ በባሕር ውስጥ ነው፥ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፤ አረማመድህም አልታወቀም። በሙሴና በአሮን እጅ ሕዝብህን እንደ በጎች መራሃቸው።” እንዳለ መጽሐፍ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ያየው ውኃ ሸሸ፣ ደነገጠ፡፡
ʺባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ። ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ። አንቺ ባሕር ሸሸሽ፣ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ ምን ሆናችኋል? እናንተም ተራሮች፣ እንደ ኮርማዎች፣ ኮረብቶችስ፣ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ? ከያዕቆብ አምላክ ፊት፥ ከጌታ ፊት ምድር ተናወጠች፤ ድንጋዩን ወደ ውኃ መቆሚያ፥ ጭንጫውንም ወደ ውኃ ምንጭ ለወጠ።” እንደተባለ ድንቅ ነገር ታየ፡፡ መዳኛውን አደረገላቸው፤ ልጅነትን ሰጣቸው፣ ክብርን አወረሳቸው፣ ጸጋውን አለበሳቸው፣ ትዕዛዛትን አስቀመጠላቸው፡፡ መልካሙን ነገር ሁሉ አደረገላቸው፡፡
በኢያሱ ዘመን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮች በውኃ ዳር ሲጠልቁ ከላይ የሚወርድው ውኃ ቆሞ እስራኤል ዮርዳኖስን በደረቅ ተሻግረዋል፡፡ ታቦታት ዛሬም በክብር ሲወርዱ ድንቅ ነገር ይሆናል፡፡ ʺተመልሶ ይምረናል፤ ክፋታችንንም ይጠቀጥቃል፥ ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል።ከቀድሞ ዘመን ጀምረህ ለአባቶቻችን የማልህላቸውን እውነት ለያዕቆብ፥ ምሕረትንም ለአብርሃም ታደርጋለህ።” እንዳለ መጽሐፍ መሠረት ልጅነትን በሚያስገኝ፣ ጸጋን በሚያሰጥ ጥበብ ሁሉንም አደረገ፡፡ በጥምቀቱ በደልን አጠፋላቸው፣ የማያልፈውን ክብር ሰጣቸው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ በእጁ ኾኖ ሳለ ለምን በውኃ መጠመቅን መረጠ ሲባል አበው ማርና ወተት ለባለጸጋ እንጂ ለደሃ አይገኝም፡፡ ውኃ ግን በዙፋን ካለ ንጉሥ በጎዳና እስካለው ጽሉስ (የኔ ብጤ) ይገኛል፡፡ ጥምቀትም መሠረቱ ለሁሉም ነውና ሁሉም በሚያገኙት በውኃ ተጠመቀ፡፡ ውኃ ተክል ቢያጠጡበት ይለመልማል፤ ጥምቀትም ሲጠመቁበት ያለመልማል፤ ወተትና ማር መልክ አያሳይም፤ ውኃ ግን መልክ ያሳያል፤ ጥምቀትም መልከ ነብስን ያሳያል፡፡ ማርና ወተት ልብስ ያሳድፋሉ፤ ውኃ ግን ያነጻል፤ ጥምቀትም እንደሚያነጻ ለማጠየቅ በውኃ ተጠመቀ ይላሉ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ መውረዱን ለማሰብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታቦታትን እየያዘች ወደ ጥምቀተ ባሕር ትወርዳለች፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአባ ሰላማ ከሳቴብርሃን መምሕርነት በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት የክርስትና ሃይማኖት በአዋጅ መሰበክና በዓላት በአደባባይ መከበር ጀመሩ ይላሉ አበው፡፡
በኢትዮጵያ ታቦታት ወደ ባሕረ ጥምቀት እየወረዱ መከበር የጀመረው በአጼ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት እንደነበር ነው የሚነገረው፡፡ በዚሕ ዘመን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የተነሳበትም ዘመን ነበር፡፡ በቅዱስ ወ ንጉሥ ላልይበላ ዘመን ደግሞ የጥምቅት በዓል ደመቀ፡፡ በዘመነ ዘርዓያቆብ ጊዜ ደገሞ የበለጠ በልዩ ሥርዓት መከበር ጀመረ ደመቀ ይባላል፡፡ በዚህ መሠረት የጥምቀት በዓል ታቦታት ሀገርን እንዲባርኩ፣ ለሃገር ሰላም፣ በረከት፣ ጸጋ፣ አንደነት እና መተሳሰብን እንዲጎናጽፉ ወደ ባሕር ይወርዳሉ፡፡
በዓለ ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱን ጠብቆ፣ እሴቶችን ይዞ፣ በሀገር ባሕል ተውቦ በድምቀት ይከበራል፡፡ መልካም በዓል!
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
