“ችግሮቻችን በጉልበት ብቻ ሳይሆን በብልጠትም የሚፈቱ ናቸው፤” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

197

ጎንደር፡ ጥር 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በጎንደር ከተማ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በወቅታዊ የሕግ ማስከበር ዘመቻው የተገኘው ድል አስደሳች እና ለቀጣይ ተልዕኮ የሚያነሳሳ መሆኑን ለርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸውላቸዋል። የክልሉ ሕዝብ ለሕልውና ዘመቻው የሰጠው ምላሽም ታሪካዊ ነበር ብለዋል። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሚሰጡ ውሳኔዎች እና አመክንዮአቸው ለሕዝብ ቀድሞ እና ግልጽ በሆነ መንገድ መነገር ነበረበትም ብለዋል ተወካዮቹ፤ ከአንዳንድ ውሳኔዎች በኋላ በሕዝቡ ዘንድ የሚስተዋለው መወዛገብ ምንጩም ሒደቱን እና ውጤቱን በውል ካለመረዳት መሆኑን አንስተዋል።

ነዋሪዎቹ በሕልውና ዘመቻው የቀጣይ ሂደት፣ ብሔራዊ የምክክር መድረክ ዓላማ፣ በጎንደር ከተማ የወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራ፣ መልካም አስተዳደር፣ የሕግ የበላይነት መከበር፣ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ በሐሰት ፕሮፖጋንዳ እና የከተማ ልማት ጉዳዮች ዙሪያ ለርእሰ መሥተዳድሩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግሮች እና ፈተናዎች ሁሉ የአማራ ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ ናቸው ያሉት ርእስ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የዘመናት የሐሰት ትርክት ውጤቶች ናቸው ብለዋል። ከሀገር ውስጥ ከሃዲዎች እስከ ውጭ አፍራሽ ኅይሎች ድረስ ኢትዮጵያን ለመፈተን እና ለመበተን የትኩረት ማዕከል ያደረጉት አማራን እንደነበር ጠቅሰዋል። የአማራ ሕዝብ የፈተና ምንጮቹ እና ግጭት ጠማቂዎቹ በዙሪያው ናቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ “ችግሮቻችን በጉልበት ብቻ ሳይሆን በብልጠትም የሚፈቱ ናቸው” ብለዋል።

ዶክተር ይልቃል ወዳጆችን ማብዛት፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማሻሻል እና ከምንም በላይ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። መንግሥት ሕዝብን ለመበደል እና ለማስቀየም አመራር በየቦታው አያስቀምጥም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፣ የሕዝብ ሠላምና ደኅንነት፣ የሕግ የበላይነት እና መሰል አንገብጋቢ ጉዳዮችን በተመለከተ በተለየ ትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ በቀጣይም ከሕዝብ ጋር የሚደረገው ምክክር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው የጎንደር ከተማ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከእርሳቸው ጋር ላደረጉት አጭር ምክክር እና ላነሱአቸው ግልጽ ጥያቄዎች ምሥጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው -ከጎንደር

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleአቢሲኒያ ባንክ በአማራ ክልል የመጀመሪያውን የቨርቹዋል ባንኪንግ አገልግሎት ማዕከልን በጎንደር ከተማ አስመርቆ ለአገልግሎት አበቃ።
Next articleጥምቀት ብርሃን