ጎንደር “የመማጸኛ ከተማ”

289

ጎንደር፡ ጥር 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የድሮ ነገሥታት የክብራቸው ልክ የሚገለጥባት ከተማ ነበረች፡፡ አንዱ በሠራው ግንብ ሌላው የንግሥና ዘመኑን አያሳልፍም፡፡ የራሳቸውን ሠርተው ዘመናቸውን ዋጅተው በጥበብ እና በሞገስ እስከዚህ ትውልድ የተንሰላሰለ አሻራ አስቀምጠው አልፈዋል፡፡ ጎንደር ስለግንብ የተፈጠረች ከተማ እስክትመስል ድረስ በግንብ የተከበበች ከተማ ናት፡፡ ከአፄ ሠርጸ ድንግል እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ከ350 ዓመታት በላይ ስለዘለቀው መዲናነቷ፣ በነገሥታቶቿ ስለተፈጸሙት ፍቅር፣ ጥበብ እና ይቅርታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጎንደርን “የመማጸኛ ከተማ” ሲሉ ይጠሯታል፡፡

በሀገረ እስራኤል በተመረጡ ስድስት ከተሞች ንጉሥ ለሕዝቡ ይቅርታ እና ቸርነትን እንደሚያደርግ ሁሉ በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ጎንደር የይቅርታ ከተማ እንደነበረች ይነገራል፡፡ ጎንደር የገባ ተሳዳጅ እና አሳዳጅ በይቅርታ ምህረትን ያወርዱ ነበር ይባላል፡፡ የመማጸኛዋ ከተማ በጥምቀት ልዩነትን ትፈጥራለች፡፡ ምድሪቷ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ተዘርተውባት ሰንደቅ ዓላማ የምታፈራ ይመስል የከተማዋ ንፍቀ ክበባት በቀስተ ዳመና ያብባሉ፡፡

በጥምቀት ጎንደር በበረዶ እና በጉም እንደተሸፈነች ሁሉ በሀገር ልብስ ያጌጡ እናቶች እና ወይዛዝርት የተለየ ስሜት ያጎናጽፋሉ፡፡ ካሕናተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሊቃውንት፣ መምሕራን እና ደቀመዛሙርቶቻቸው በእግራቸው እያሸበሸቡ፣ በእጃቸው እያጨበጨቡ እና በጥምጣማቸው እያረበቡ ጎንደርን ምድራዊ ገነት ያደርጓታል፡፡ ይኽው አሁንም ታቦታት ከመንበራቸው እና ካሕናት ከደብራቸው እየወጡ ነው፡፡ እናቶች በእልልታ እና ወጣቶች በሆታ የውዳሴ ዳርቻን ያሳዩበታል፡፡ ምሥጋናቸው ሰማይና ምድርን ሊያገኛኝ እንደመሰላል ከእጣነ ሞገሩ ጋር ወደ አርያም ያቀናል፡፡ በጠዋት የታጠበው ጎዳና በሚነሰነሰው ቄጤማ እና በሚነጠፈው ስጃጋ ፍጹም ምድራዊነትን ያስረሳል፡፡

ቤተሰቦች፣ ጓደኛሞች እና እንግዶች በቡድን በቡድን እየሆኑ ወደ ፋሲል መዋኛ ያመራሉ፡፡ ተሸከርካሪዎች ቀስ በቀስ ከእይታ እየጠፉ፣ የካሕናት ዝማሜ እና ውዳሴ እያየለ እና የእናቶች የእልልታ ድምጽ የኢያሪኮን ታሪክ እያስታወሰን ከተራ በጎንደር በቃል ለመናገር የሚከብድ ድባብን ፈጥሯል፡፡ በቀሃ እና አንገረብ ወንዞችን የታቀፈችው ጎንደር ጥምቀትን በአፄ ፋሲል መዋኛ ገንዳ በድምቀት ታከብራለች፡፡

ጎንደር ከአራቱም አቅጣጫ የሚመጡት 44 ታቦታት አዳራቸው በዚሁ የጥንት ግን ደግሞ በዘመናዊ ዓለም እንኳን ባልተደገመው እና ብቸኛው የአፄ ፋሲል መዋኛ ገንዳ ዙሪያ ያሳልፋሉ፡፡ ከጎንደር ከመናገሻነቷ በፊት የተተከሉትን ጎንደሮች ማሪያም፣ ጎንደሮች ጊዮርጊስ፣ አርባቱ እንስሳ እና ቀሃ ኢየሱስን ጨምሮ 44ቱ ታቦታት በአንድ ያድራሉ፡፡ በውዳሴ፣ በአንድነት እና በዝማሜ የሚያልፈው የዛሬ ሌሊት ዓለማዊነት አብዝቶ ለፈተናት ዓለም የመንፈሳዊነት እፎይታን ይሰጣታል፡፡

ጥላቻ በፍቅር፣ መሳሳብ በመተሳሰብ፣ መገፋፋት በመረዳዳት፣ መለያየት በአንድነት እስኪተካ ድረስ የዮርዳኖስ በረከተ ጥምቀት በጎንደር እና መላው ኢትዮጵያ ላይ አብዝቶ ይፈሳል፡፡ እኛም ጥምቀትን ከጎንደር ያየነውን በምስል፣ የሰማነውን በፊደል እያቀናበርን እናደርሳችኋለን፡፡ መልካም የከተራ በዓል!

ዘጋቢ፡-ታዘብ አራጋው -ከጎንደር

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“ሀገራችን ያሉ የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት ጥራት ያለው ትምሕርት በመስጠት ብቁ ዜጋ መፍጠር እስካልቻሉ ድረስ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች አንከፍትም” ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
Next articleምዕመኑ ያንን ሁሉ መከራ አሳልፎ ለዚህ በመብቃቱ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ገለጹ፡፡