
ጥር 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያዊያን የዘመን ቀመር በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው የጥምቀት በዓል በዋዜማው መድመቅ ይጀምራል፡፡ ዋዜማውም የከተራ በዓል በመባል ይታወቃል፡፡ ጥር 10 ቀን ታቦታቱ ከመንበራቸው ሲወጡ ‹‹ዮም ፍስሀ ኮነ›› ተብሎ ከተዜመ በኋላ ወደ ማደሪያቸው ሲያመሩ ‹‹ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት›› የሚለው ሰላም በሊቃውንት እየተዘመረ ይጓዛል፡፡ በወንዝ ዳር ወይም በሰው ሰራሽ የውኃማ አካባቢ ድንኳን ተክለው ዳስ ጥለው ለአዳር በዚያው ይከትማሉ፡፡ ታቦታቱ የሚያድሩበት ቦታም ባህረ ጥምቀት በመባል ይታወቃል፡፡
በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ ታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ እና የባህረ ጥምቀቱ መዘጋጀት ሃይማኖታዊ ታሪክ እና ምሳሌ አለው፡፡ የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብሮ መጓዝና ወደ ወንዝ መውረድ የተጀመረው በአሮን ልጅ በአልዓዛር ጊዜ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል፡፡

በፃዲቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (1203-1204 ዓ.ም) አሳሳቢነት በኢትዮጵያ እንደተጀመረ የሚነገርለት የጥምቀት በዓል በአፄ ይኩኑ ዓምላክ ዘመነ መንግሥት (1260-1275 ዓ.ም) በአዋጅ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቅዱስ ላልይበላ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር እየተመላለሱ በብሕትውና እና በስብከተ ወንጌል ያገለግሉ የነበሩት ፃዲቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ባህረ ጥምቀቱን ይባርኩ እንደነበር ታሪክ ያወሳል፡፡
ከአፄ ገብረ መስቀል ጀምሮ የአደባባይ በዓል የኾነው የጥምቀት በዓል በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉሠ ነገሥት አፄ ዘርዓ ያዕቆብ (1426-1460 ዓ.ም) አማካኝነት ታቦታቱ በዕለቱ ወጥተው እንዳይመለሱ፤ በምትኩም በዋዜማው ወጥተው እንዲያድሩ በዐዋጅ ወሰኑ፡፡ ይህንን ተከትሎም አፄ ናዖድ (1486-1500 ዓ.ም) ሕዝቡ በከተራ የበዓል ቀን ታቦታቱን ወደ ባህረ ጥምቀቱ አውርዶ አሳድሮ በዕለተ ጥምቀት ሲመለሱ ደግሞ አጅቦ እንዲመልሳቸው ዐዋጅ አስነገሩ፡፡
ከተራ የጥምቀት በዓል ዋዜማ ነው፡፡ ከተራ የሚለውን ቃል ሰርገው (1981፤1) ሲገልፁት ‹‹ከተረ ወይም ከበበ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል እንደመጣ ይናገራሉ፡፡ ሰርገው የቃሉን ትርጉምም ሲያስቀምጡ ከተራ ማለት ውኃ መከተር ወይም መገደብ ማለት ነው ይላሉ፡፡ ተፈጥሯዊ ምንጮች አቅም ስለሚያጥራቸው እና ስለሚደርቁ ውኃው ይገደባል ወይም ለጥምቀት በዓል ይከተራል፡፡

ካህናት እያሸበሸቡ፣ በድምፃቸው እያዜሙ፣ እናቶችና ልጃገረዶች በእልልታ፣ አባቶችና ወጣቶች በሆታ ታቦታቱን ከየአድባራቸው አውጥተው ወደ ማረፊያቸው ያደርሷቸዋል፡፡
የከተራ በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ፈለገ ዮርዳኖስ ወንዝ በ30ኛ ዓመቱ ያደረገውን ጉዞ ለማዘከር ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን በየዓመቱ ጥር 10 ቀን በሚያከብሩት የከተራ በዓል በየአጥቢያቸው የሚገኙ ታቦታትን አጅበው ረጋ ባለ የእግር ጉዞ ወደ ማረፊያቸው ያደርሳሉ፡፡ አባቶች፣ ሹርባ የተሠሩ እናቶች፣ እንሶስላ የሞቁ ኮረዶች እና በባህላዊ አለባበስ የደመቁ ወጣቶች በልዩ ልዩ የጎዳና ላይ ትርዒት እና ጭፈራ ከተራን እያደመቁ ታቦታቱን አጅበው ማረፊያቸው ያደርሳሉ፡፡
ታቦታቱ ባረፉበት ቦታ አባቶች፣ ካህናት፣ ወጣቶችና ዲያቆናት እና ምዕመኑ ሌሊቱን በዝማሬ ያሳልፋሉ፡፡ ከተራ ምንጊዜም በጾም ይከበራል፡፡ ጥምቀት ማክሰኞ ከዋለ ገሀዱ ሰኞ፤ አርብ ከዋለ ደግሞ ገሀዱ ሐሙስ ቀን ይሆናል፡፡ ጥምቀት ረቡዕ ወይም አርብ ቀን ቢውል ፆም አይኖረውም፡፡
በታዘብ አራጋው
