የጥምቀት በዓል ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ አጭር ቅኝት፡፡

556

ጥር 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአደባባይ በዓላት አንዱ ጥር 11 ላይ የሚውለው የጥምቀት በዓል ነው፡፡ ዋዜማው ከተራ እና ማግስቱ ቃና ዘገሊላም የአከባበሩ አካል ናቸው፡፡ በዓሉ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እስከ ሦስት ቀናት ይከበራል፡፡ በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በከተራ ዕለት ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው በምዕመናን፣በካሕናትና ዲያቆናት ታጅበው ወደየ ጥምቀተ ባሕሩ ያመራሉ፡፡ ይህ ሁነት ሀገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ የቱሪስት መስህብነትን የተጎናጸፈ ነው።
የካሕናትና ዲያቆናት ልብሰ ተክሕኖ፣ የምዕመናኑ ባሕላዊ የክት ልብስ ድምቀት ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሠርክ አዲስ ነው።
ጥር 10 ከተራ በገጠርም ሆነ በከተማ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ የሚያደርጉት ጉዞና መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ በማግስቱ የጥምቀት ዕለት ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ›› ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ›ን ይዞ የሚኖረው ያሬዳዊ ዝማሬ የበዓሉ ገጽታ ነው፡፡ ጥምቀት ታቦታቱ ከየአድባራቱ ሲወጡ “ዮም ፍስሀ ኮነ” ተብሎ ከተጸነጸለ በኋላ ታቦታቱ ወጥተው “ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት” የሚለው ሰላም በሊቃውንቱ ይዘመራል፤ ይጸነጸላል፤ ይመላለሳል፡፡ የወርቅ ካባና ላንቃ የደረቡ ቀሳውስት፣ መነኮሳት ጥላ የያዙት ከታቦታቱ ጎን መስቀልና ጽና የያዙት ከታቦታቱ ፊት ይሔዳሉ፡፡ እንደ ቀሳውስቱ ተመሳሳይ ልብሰ ተክሕኖ የለበሱት ዲያቆናት ጥላ፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው እያቃጨሉ ከቀሳውስቱ ፊት በመሆን ያጅቧቸዋል፡፡ ከነዚህም ሌላ ካባ፣ ላንቃ ድርብ የደረቡ መዘምራን የብር፣ የነሐስ መቋሚያና ጸናጽል ይዘው “ወረደ ወልድ” የሚለውን አመላለስ እያሸበሸቡ ዲያቆናቱን ቀድመው ይሄዳሉ፡፡ የደብር አለቆችና አበው ካህናት ታቦታቱን ተከትለው ያጅባሉ፡፡

የሰንበት ትምሕርት ቤት ተማሪዎችም በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቁ አልባሳት ተውበው እየዘመሩ “ወረደ ወልድ፣ እግዚኡ መርሐ፣ ሆረ ኢየሱስ” እና ሌሎችንም መዝሙራትን እየዘመሩ፣ እናቶች “ነይ ነይ እምዬ ማርያም” እያሉ ሌሎች ውዳሴዎችን እያቀረቡ ጉዞ በዝግታ ወደ ጥምቀተ ባሕር ይሆናል፡፡
የከተራ በዓል ማክበሪያ ቦታ እንደደረሱ ታቦታቱ በድንኳኑ አጠገብ ቆመው “ወረደ ወልድ” የሚለው ሰላም ተመርቶ በአግባቡ ከተለዘበ በኋላ ጸሎት ተደርጎ የዕለቱ ትምሕርተ ወንጌልና ዝማሬ ይቀርባል፤ ውዳሴ ማርያም፣ መልክዓ ኢየሱስ ተደግሞ ታቦተ ሕጉ ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳን ይገባሉ፡፡

በሁለተኛ የአገልግሎት ክፍል ካሕናቱ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያድራሉ፡፡ በነጋታው የሥርዓተ ጥምቀቱ መርሐ ግብር ይቀጥላል፡፡
ጥምቀት ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝም ባሕላዊ ገጽታውም ጎልቶ ይታያል፡፡ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት፣ አጋጣሚዎችን ከመፍጠሩም ባለፈ በከተማም ሆነ በገጠር ወዳጅ ዘመድን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡ በጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ ሥነ ስርዓቱ ጎን ለጎን የሎሚ ውርወራው፣ የከተራው ሽልምልም ዱላ ባሕላዊ ጭፈራው ይደምቃል፡፡ ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካሕኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ ወደ የአጥቢያቸው ይመለሳሉ።

በጥምቀት በዓል ማግስት ማለትም ጥር 12 ደግሞ ቃና ዘገሊላ በዓል ይቀጥላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ቃና ዘገሊላ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የመጀመሪያውን ታምሩን የገለጸበት ቦታ ነው፡፡ ቃና ዘገሊላ ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንደኛው በገሊላ አውራጃ የምትገኝ ቃና የተባለች መንደር ስትሆን ሁለተኛው ኢየሱስ ክርስቶስ ታዕምር ያደረገበት ነው፡፡ ቃና ዘገሊላ ኢየሱስ ክርስቶስ በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን የቀየረበትና ጋብቻን የባረከበት ዕለት ነው፡፡ ቃና ዘገሊላ በዕለቱ የተደረገውን ተዓምር ይዞ የበዓል ስያሜ ሆኖ መሰጠቱን በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የጉባኤ ቤት መምህር ገብረመድህን እንየው ነግረውናል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በደቀ መዝሙሩ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ሳይውል ሳያድር በገዳመ ቆሮንጦስ ገብቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት ፀለየ፡፡ ከገዳመ ቆሮንጦስ ሲወርድ የካቲት 23 ቀን በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን የቀየረበት ተዓምር ነው ብለዋል መምህር ገብረመድህን፡፡ እንደ መምህር ገብረመድህን ገለጻ በዶኪማስ ቤት ድንግል ማርያም፣ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ተገኝተው ነበር፡፡ ይህ ተዓምር የካቲት 23 ቀን ይፈጸም እንጅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዓሉን ጥር 12 ቀን ከጥምቀት በዓል ጋር አስተሳስራ በደመቀ ሁኔታ ታከብራለች፡፡

የቃና ዘገሊላ በዓልም የውኃ በዓል ስለሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ከጥምቀት በዓል ጋር አስተሳስራ የምታከብርበት ምክንያቱ ይህ መሆኑን መምህሩ ነግረውናል፡፡ የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ በግዙፍ ቅርስነት ከተመዘገቡት ከአክሱም፣ ላልይበላ የጎንደሩ ፋሲል ግቢ ጋር በጥብቅ ተሳስሮ የሚከበር የማይዳሰስ ቅርስ መሆኑ፣ እንዲሁም በዓሉ ከ1 ሺህ 500 ዓመታት በላይ በተከታታይ የሀገሪቱ ትውልዶችና ሥልጣኔዎች እየተከበረ ያለ ሕያው ቅርስ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የባሕልና ትምሕርት ድርጅት (ዩኔስኮ) በወርኃ ጥር የኢትዮጵያ አደባባዮች ደምቀው እንዲታዩ የሚያደርገውን የጥምቀት ክብረ በዓልን በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት በቦጎታ ኮሎምቢያ የማይዳሰሱ ባሕላዊ ቅርሶች የበይነ መንግሥታት ኮሚቴ ታኅሣሥ 1/2012 ዓ.ም. መመዝገቡ ታወሳል፡፡ ተጨማሪ የመረጃ ምንጭ፡-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ድረ ገጽ
በመልሰው ቸርነት
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article❝ሐይቁን ባርካ ትወርዳለች፣ ሐይቁን ባርካ ትገባለች❞
Next articleከተራ፡ ከገሊላ እስከ ዮርዳኖስ!