❝ሐይቁን ባርካ ትወርዳለች፣ ሐይቁን ባርካ ትገባለች❞

203

ጥር 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የምስጢር መጠቅለያ፣ የጥበብ መሶበ ወርቅ፣ ያልተመረመረ፣ በረቂቅነት የኖረ፣ ለዘመናት ጥበብን፣ ጠቢባንና ምስጢራትን አቅፎ ያሻገረ፡፡ ገዳማት የበዙበት፣ መነኮሳት የሚኖሩበት፣ ቅዱሳን አበው በየቀኑ የሚባርኩት፣ በላዩ የሚመላሱበት፣ እርሱ በከለላቸው ደሴት ውስጥ የሚኖሩበት ነው፡፡ በፍቅር አምሳል በሆነው በልብ ቅርጽ አርፏል፣ የዓለማት አፈጣጠር፣ የዓለማትን አኗኗር፣ የዓለማትን አፈጻፀም ምስጢር ታቅፏል፣ የተዘጉ የሚመስሉት መንገዶች፣ ያልተመረመሩ ጥበቦች፣ ያልተደረሳባቸው ምስጢሮች መፍቻ ቁልፋቸውን ይዟል፡፡
ስጋቸውን ቀጥተው፣ ነብሳቸውን አርክተው የሚኖሩ፣ አላፊዋን ዓለም የናቁ፣ ሕገ እግዚአብሔርን የጠበቁ ቅዱሳን፣ ቅዱሰ ቅዱስ እያሉ፣ ባዕታቸውን ዘግተው፣ በእግራቸው ቆመው ለፈጣሪ ምስጋና ያቀርባሉ፣ ምድር ከጥፋት ትድን ዘንድ ይማጸናሉ፡፡ በደልና መከራ በምድር እንዳይመጣ፣ መልካም ዘመን እንዲመጣ አቤቱ ጌታ ሆይ ምድርን አስባት፣ በቸርነትህ ጠብቃት፣ በድልን ሁሉ አርቅላት እያሉ ይለምናሉ፡፡ ሳይቋረጥ ምስጋና ይቀርብበታል፣ ሳይቋረጥ ይጸለይበታል፣ ቅዱስ መንፈስ በላይ ላይ ይረብበታል፣ ነብሴን ለሥላሴ ስጋዬን ለመነኩሴ ያሉ መነኮሳትና መነኮሳይት ወገባቸውን አስረው ሳያቋርጡ ለመልካም ነገር ይተጋሉ፡፡ በዚያ ቅዱስ ስፍራ ስጋ ረሃብተኛ ነው፣ ነብስ ግን አብዝታ ትጠግባለች፣ ከማያልቀው ቅዱስ መንፈስ ትመገባለች፡፡ አበው ቅዱሱን ሐይቅ ረቂቅ ነገር ሁሉ በውስጡ አለበት ይላሉ፡፡ ልዩ ጥበብ ያለበት በጥበብና በጠቢባን የሚጠበቅ ነው ምስጢራዊው ሐይቅ ጣና፡፡ ፍጥረታት የጥፋትን ውኃ የተሻገሩባት መርከብ በዚሁ ሐይቅ አናት ላይ አርፋለች ይላሉ አበው፡፡
ምስጢር የጠፋባቸው፣ ዕውቀት የተደበቀባቸው፣ ጥበብ የራቀቸው ሁሉ ዓይኖቻቸውን ወደ ቀደምቲቷ ሀገር ኢትዮጵያ ያዞራሉ፣ ጀሮዎቻቸውን ወደ እርሷ ያዘነብላሉ፣ ጉዟቸውን እርሷ ወደአለችበት አቅጣጫ ያደርጋሉ፣ በእርሷ ሁሉም ነገር አለና፡፡ ውቅያኖስ አቋርጠው በልብ ቅርጽ ወደ አረፈው ሐይቅ ይጓዛሉ፣ የብስ ሰንጥቀው ወደ ሐይቁ ይተምማሉ፤ በዚያ ውስጥ ያለው በየትኛውም ሀገር የለምና፡፡ በጠለቀው ሐይቅ ውስጥ በእጅጉ የጠለቀ ምስጢር አለና ወደ ዚያው ያቀናሉ፡፡ በዚህ ሐይቅ ውስጥ ሁልጊዜም ረቂቅ ነገር ሞልቷል፡፡

ዝጉሃን አባቶችና እናቶች ዓለምን ትተው፣ በበዓት ተወስነው፣ የሰማዩን እያሰቡ ፀሎት ያደርሱበታል፣ በሐይቁ ምስጢራዊ ስፍራዎች ውስጥ ይመላለሱበታል፣ ሐይቁ በመዓበል እየተገፋ ወዲያና ወዲህ ሲማታ፣ አዕዋፋት በሕብረ ዝማሬ ሲዘምሩ፣ ቀሳውስቱ ሲያዜሙ፣ ደበሎ የለበሱ አባቶች በተመስጦ ሲሄዱ፣ እፅዋት ሲያረግዱ ሲታዩና ሲሰሙ ግሩም ያሰኛል፡፡
እነሆ ጥምቀት ደርሷል፡፡ ታቦታት ከየአድባራቱ ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር ሊወረዱ ነው፡፡ ወንዞች ሊባረኩ ነው፣ ምዕምናንም ሊጠመቁ ነው፡፡ በተቀደሰው ሐይቅ ውስጥ የሚኖሩ ገዳማትና አድባራትም ብርሃን የታየበትን፣ ሐጥያት የተደመሰሰበትን፣ የእዳ ደብዳቤ የተቀደደበትን በዓል ያከብሩታል፡፡ ከእነዚህ ገዳማት መካከል አንደኛዋ ሐይቅ እየባረከች ወርዳ፣ ሐይቅ እየባረከች ትገባለች፡፡ በተቀደሰው ሥፍራም ለዘላለም አርፋ ትኖራለች፡፡
ዓባይ ጣናን ረግጦ ከሚያልፍበት፣ ድንቅ የተፈጥሮ ጥበብ ከታየበት፣ በረከት ከመላበት የምትገኛዋ ደብር በሐይቅ ከተከበበው ቤቷ ወጥታ ሐይቁን እየባረከች ወደ የብስ ታቀናለች፡፡ በየብስ የሚኖሩ ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባሕር ሲወርዱ፣ እርሷ ደግሞ ከሐይቅ አቋርጣ ወደ የብስ ትወጣለች። በዚያች ቅድስት ሥፍራ የተገኘ ሁሉ ዓይኑ መልካም ነገርን ታያለች፣ ጆሮው መልካም ነገርን ትሰማለች፣ ልቦናው ድንቅ ምስጢርን ትመረምራለች፡፡ ነብሱ ሐሴትን ታደርጋለች፡፡ እርሷ ረቂቅ ናት፣ እርሷ ድንቅ ናትና፡፡ ታይታ አትሰለችም፣ በተመስጦ ከማድነቅ ውጭ አትገለጽም፡፡
ኢትዮጵያ የማትመረመር መሶበወርቅ፣ የማትዝግ ወርቅ፣ ከክብርም በላይ የሆነች ጌጥ፣ ቃል ኪዳን የሆነች የልብ ፈርጥ ናት፣ ፈጣሪ ያከበራት፣ በፈቃዱ የፈጠራት፣ በፈቃዱ ያኖራት፣ በፈቃዱ የሚያኖራት፣ ለምስክር ያዘጋጃት ናት ኢትዮጵያ።
ማን ይሆን ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ሐሴት የማያደርግ? በተለየችው ምድር ተፈጥሮ ማን ይሆን ፈጣሪውን የማያመሰግን? እኔ ፈጣሪን ተመስገን እለዋሁ፡፡ በተመረጠችው ምድር ተፈጥሬያለሁና፡፡ በክብሯ እክበራለሁ፣ በሠንደቋ ሥር እጠለላሁ፣ በሞገሷ ሞገስን አገኛለሁ። ጥንታዊቷ ገዳም ደብረማርያም በዓለ ጥምቀት ሲደርስ ትደምቃለች፣ ልዩም ትሆናለች፡፡ አካባቢው አምሳለ ቀስተ ደመና በሆነው ሠንደቅ ይዋባል፣ ሊቃውንቱ ይሰበሳበሉ፣ ምዕምናኑ ሐይቅ እያቋረጡ በረከት ለማግኘት ይገዟሉ፡፡ በገዳሙ ዙሪያ የቆሙት እፅዋት በነፋስ እየተገፉ ያረግዳሉ፣ ይወዛዋዛሉ፡፡

የታቦት መውጫ ጊዜው ሲደርስ ደወል ይደዋላል፣ ጥሩንባው ይነፋል፣ ቀሳውስት ይዘምራሉ፣ ምዕመናን እልል ይላሉ፣ ከበሮው ይመታል፣ በዚያች ደብር የተገኙ ሁሉ በደስታ ይከንፋሉ። ሐሴትንም ያድጋሉ፡፡ በታቦቷ ፊት ለፊት የተገኙት ምዕምናን ከወገባቸው ጎንበስ እያሉ በግንባራቸው እየተደፉ ይሰግዳሉ፣ ምስጋናም ያቀርባሉ፡፡ እንኳን ሰዎቹ ዛፎቹም ምስጋና የሚያቀርቡ ይመስላል፡፡ ጽናጽል ሲጸነጽኑ፣ ከበሮ ሲመቱ አይታይም እንጂ አብረው የሚያሸበሽቡ ይመስላሉና፡፡ የደበሩ አጫዋችም ሿሿሿሿ ….. እያለ ምስጋና የሚያቀርብ ይመስላል፡፡ ትዕይንቱን ያደምቃል፡፡
ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። በተቀደሰው የጣና ሐይቅ ውስጥ ካሉ ገዳማትና አድባራት መካከል ቀዳሚዋ ናት ይሏታል። ይህች ቤተክርስቲያን በአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት እንደተሠራች ይነገራል። በተቀደሰችው ሥፍራ የተቀደሰችውን ደብር የደበሩ፣ የእግዚአብሔርን ማደሪያ የሠሩ፣ ሕግጋትን ያሰፈሩ፣ ቃል ኪዳንን ያኖሩ አቡነ ታዲዮስ ናቸው ይላሉ አበው። ሕንፃ ቤተክርስቲያኗ ከቅድስቲቱ ሀገር ኢየሩሳሌም በመንፈስ ቅዱስ ከመጣ ድንጋይና አፈር እንደተሠራች ይነገራል። ቤተክርስቲያኗ በመንፈስ ቅዱስ የተሠራች እፁብ ናት። በዚች ጥንታዊት ቤተክርስቲያን አያሌ ምስጢራት ይገኛሉ። ጥንታዊ የብራና መጽሐፍትና ቅዱሳን ቅርሶችን አቅፋለች።
ደብረ ማርያም ድንቋ እመቤት፣ የሐይቋ ሙሽራ፤ ዳሩ እንደ ጥንታዊነቷ፣ እንደ ውበቷ፣ እንደ ምስጢራዊነቷ አይደለም፤ የሚያውቋት ብዙዎች አይደሉም፡፡ ብዙዎች አይተው አላደነቋትም፣ አይተው የመንፈስ እርካታ፣ የነብስ እፎይታ አላገኙባትም፡፡ አይተው ጥበብን አልመሰከሩም፡፡ በዚሕች ቅድስት ሥፍራ በዓለ ጥምቀት በልዩ ትዕይንት ይከበራል፡፡ በበዓለ ጥምቀት ደብረ ማርያምን ማዬት ከደስታም ደስታ ከሐሴትም ሐሴት ነው።
ልባቸው በእናታቸው ፍቅር የተሞላ፣ አንደበታቸው በመልካም ቃላት የሰላ፣ ልባቸው ንጹሕ የሆኑ ሕጻናት፣ ንጹሕ በሆነው ሐይቅ፣ ንጽሕት ወደሆነችው እናታቸው እየቀረቡ ʺማርያም ሆይ እንወድሻለን፣ ማርያም ሆይ የአስራት ሀገርሽን ኢትዮጵያን ጠብቂያት” ይሏታል። ለምስጋና የተዘጋጁ ካህናት በታቦቷ ዙሪያ ቆመው በድንቅ ዝማሬ ያመሰግናሉ፡፡ የታንኳው ሽርሽር፣ የምዕምናን ክብር፣ ለእናታቸው ለማርያም፣ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ያላቸው ፍቅር የሚገርም ነው። ማገልገል ከልብ ሲሆን፣ ለጽድቅና ለክብር ሲነሱ ነገሩ ሁሉ ረቅቅ ነው።

ለእናታቸው ክብር ሕጻናቱ ታንኳ እየቀዘፉ እልል እያሉ ታቦቷን ይዞሯታል፡፡ በምስጋና በክብር ያደምቋታል፡፡ እኒሁ ሕጻናትና ታዳጊዎች ፍቅራቸውንና ክብራቸው አብዝተው ለመግለጽ ሲሹ ከታንኳ ወርደው ወደ ሐይቁ እየጠለቁ፣ በተባከረው ሐይቅ እየተጠመቁ፣ በታቦቷ ዙሪያ ገባ እየተመለላሱ ምስጋና ያቀርባሉ፣ እልል ይላሉ። ታቦተ ማርያም በክብርና በእልልታ ከመንበሯ ከወጣች በኋላ በክብርና በእልልታ ወደ ሐይቁ ትወርዳለች፣ በሐይቁ ላይም ታቦቷን ያጀቡ ካሕናት ወደ ተዘጋጀላቸው ጀልባ ይገባሉ፡፡ አንተ ጀልባ ሆይ ታድለሃል፣ ተመርጠሃል፣ ተለይተሃል፣ የታቦት ማረፊያ፣ የሐይቅ መሻገሪያ ሆነሃልና፡፡
ጀልባዎች ታቦተ ማርያምን እየዞሩ ያጅባሉ። በጀልባውና በታንኳው ያሉ ምዕምናን እልል እያሉ፣ እያጨበጨቡ፣ በልባቸው እያደነቁ ታቦቷን ያጅባሉ። የማርያም ታቦት ከመንበሯ ወጥታ ሐይቅ እስክትገባ፣ ከሐይቅ ወጥታ እስከ ማደሪያዋ ድንኳን እስክትደርስ ድረስ በየብስ ላይ ስትጓዝ ለአገልግሎት በሚፋጠኑ ወጣቶች ስጋጃ እያነጠፉ፣ ስለ ክብሯ እየሰገዱ በክብር እንድታልፍ ያደርጓታል። ይህ ከማደሪያዋ አድራ ወደ መንበሯ ስትመለስም ይደረጋል፡፡ ደገኞች ያከበራቸውን ያከብሩታል፣ የጠበቃቸውን ይጠብቁታል፣ ዝቅ ብለው ሰግደው ከፍ ብለው ይከብራሉ።
ያን ያዩ ሁሉ አንቺ ምድር ኢትዮጵያ ሆይ ምንኛ የታደልሽ ነሽ ማለታቸው አይቀርም። ከታደሉት የታደለች፣ ከተመረጡት የተመረጠች፣ ከተቀደሱት የተቀደሰች ውብ ሀገር – ኢትዮጵያ። የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ የቅዱሳን ሀገር፣ የታሪክ ማህደር፣ የኃያልነት መንበር፣ የስልጣኔ መውጫ የምሥራቅ በር ናት ኢትዮጵያ። ኢትዮጵያን አይቶ የጠገበ፣ በቀላል መርምሮ የደረሰ፣ የኢትዮጵያን የኃይልነት ክንድ የገረሰሰ የለም፣ አይኖርምም፡፡
ኢትዮጵያ ለምስጋና አታርፍም፣ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ አታጥፍም። በንጽሕና እየለመነች፣ በቅድስና እየተቀበለች፣ ቃል ኪዳኗን እያከበረች ትኖራለች እንጂ። ደብረማርያምን የተመለከተ ሁሉ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የነበረውን ሁሉ ያዬ ይመስለዋል። ታላቁ ሐይቅ ጣና ይደምቃል፣ መጥፎ ነገር ሁሉ ይርቃል፣ በደስታና በቅዱስ መንፈስ ይመላል፡፡
ፈጣሪ ውኃን በውኃ ላይ አሳልፎ በሰደደበት ተዓምራዊ ቦታ አጠገብ የምትገኝ የምድርና የሰማይ እመቤት ደብረ ማርያም፣ የፈጣሪን ልዩ ጥበብ ያዩባታል፣ ደስታና በረከትን ይመለከቱባታል፡፡ ዓባይ በጣና ላይ አልፎ ይሄድበታል፣ ጣናም ዓባይን ለዘላለም ያሳልፈዋል፣ ለዘላለምም ይሸከመዋል፡፡ ዓባይ በጣና ላይ አልፎ ሲሄድበት የተመለከተ ሁሉ መቻልን፣ መጽናትን ይማራል፡፡ ጣና ሆደ ሰፊ ነው፣ ጣና ብርቱ ነው፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ብሎ አያውቅም፡፡
አበው የጣናን ደግነት አይተው
❝አብርሃም ነው ጣና እንግዳ ተቀባይ
ከቤቱ ቢመጣ ረጅሙ ዓባይ
ሌባ እኮ ነህ ሳይል ባሕሪውን ሳያይ
መንገዱን አሳየው እንዲያልፍበት በላይ❞ እያሉ ተቀኝተውበታል፡፡
በዓለ ጥምቀት በደብረ ማርያም ድንቅ ነው፡፡ አከባበሯ እፁብ ነው፣ ምስጋናዋ ግሩም ነው። ደስታም፣ ሐሴትም፣ ፍቅርም፣ ክብርም፣ ተድላም፣ ታሪክም ያለው በዚያ ውስጥ ነው።
ሐይቁን ሰንጥቀው ይገስግሱ፣ ከተቀደሰችው ስፍራ ይድረሱ፣ ከተቀደሰው ማዕድ ይቋደሱ፣ ከክብሩ ካባ ይልበሱ፡፡ ይይዋት ይረኩባታል፣ ያክበሯት ይከብሩባታል፣ የመንፈስም ስንቅ ይገበዩባታል። የማይረሳ ትዝታ ይሰንቁባታል፡፡ ሐይቁን እየባረከች ወጥታ ሐይቁን እየባረከች ወደ ምትገባዋ ደብር ይገስግሱ፣ ከመልካሙ ፍሬ ይቅመሱ፡፡ መልካም በዓል!
በታርቆ ክንዴ

Previous articleሕዝብ እና መንግሥት የሰጧቸውን ኅላፊነት በላቀ ግዳጅ ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውን ተመራቂ የልዩ ኃይል አባላት ተናገሩ፡፡
Next articleየጥምቀት በዓል ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ አጭር ቅኝት፡፡