
ሑመራ፡ ጥር 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብሎም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የገጠማቸውን የሕልውና ስጋቶች ለመሻገር ሚናቸው የጎላ ነበር፤ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት፡፡ ከዳንሻ እስከ ሁመራ፣ ከማይጠብሪ እስከ ግራ ካሶ፣ ከአላማጣ እስከ መሆኒ፣ ከዛታ እስከ አበርገሌ በበርካታ አውደ ውጊያዎች ውድ ስለሆነው ሕይዎታቸው ሳይሰስቱ ግፈኞችን የሃፍረት ካባ አከናንበዋል፡፡
የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በአማራ ሕዝብ የፈተና ወቅት አብሪ ከዋክብት ሆነው ብቅ ያሉ የዘመኑ የአማራ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ዘቦች ሆነዋል፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በዱር በገደሉ፣ በቆላ በደጋው፣ በቀን በሌሊት የአማራ ሕዝብን በንቃት የሚጠብቁ ባላደራዎች ናቸው፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ ለ10ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን የልዩ ኃይል አባላት በባዕከር ወታደራዊ ትምህርት ቤት ትናንት አስመርቋል፡፡ በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ያነጋገርናቸው ተመራቂዎች አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎችን በወረራ ይዞ በነበረበት ወቅት ወደ ስልጠና መግባታቸውን ገልጸው የሰሙት ግፍና መከራ፣ ያዩት የወገን ስቃይ ወደ ልዩ ኃይል እንዲገቡ ምክንያት እንደሆናቸውም ነግረውናል፡፡
በቆይታቸው በቂ ወታደራዊ የንድፈ ሐሳብ እና የተግባር ስልጠና መውሰዳቸውን የነገረን ተመራቂ የልዩ ኃይል አባል ኮንስታብል ኃይሉ አለባቸው የተሰጠንን ትምህርት በላቀ ውጤት አጠናቀናል ነው ያለው፡፡ ስልጠናው በሀገሪቱ የተከሰተውን ወቅታዊ የሰላም ችግር ለመቅረፍ ሥነ ምግባር፣ ሙያ እና ክህሎት እንዳላበሳቸው የገለጸው ኮንስታብል ኃይሉ ወጣቶች የጸጥታ ኃይልን በመቀላቀል የክልሉን እና የሀገሩን ደኅንነት ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጭ ኮንስታብል የኔሃሳብ አያሌው በሽብር ቡድኑ ወረራ የአማራ ሕዝብ የከፈለው መከራ እና ግፍ ልዩ ኃይልን እንዲቀላቀል እንዳደረገው ገልጾ ለአማራ ሕዝብ ክብር እና ሰላም ሲባል እስከ ሕይዎት መስዋእትነት ለመክፈል በቂ ዝግጅት አድርገናል ብሏል፡፡ በቀጣይም የሚሰጠውን ማንኛውንም አይነት ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ነግሮናል፡፡

ኮንስታብል ሃይማኖት ጓዴ በአማራ ፖሊስ ኮሌጅ በባዕከር ወታደራዊ ትምህርት ቤት ለ10ኛ ዙር ካሰለጠናቸው የልዩ ኃይል አባላት መካከል አንዷ ነች፡፡ የ12ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበረች የምትናገረው ኮንስታብል ሐይማኖት ከሕልውና በላይ የሚሆን ምንም ነገር ባለመኖሩ የአማራ ልዩ ኃይልን እንደተቀላቀለች ነው የምትናገረው፡፡
በቆይታቸው በቂ ወታደራዊ እውቀት፣ ክህሎት እና የሥነ ምግባር ትምህርት አግኝተናል ያለቸው ኮንስታብል ሃይማኖት በስልጠና ያገኙትን እውቀት ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ለመጠበቅ በቂ ስንቅ ሆኖናል ብላለች፡፡ ወጣቶች የጸጥታ መዋቅሮችን በመቀላቀል እና ሥልጠና በመውሰድ የሕዝባቸውን እና የክልላቸውን ደኅንነት እንዲያስጠብቁም ጥሪ አቅርባለች፡፡ ተመራቂ የልዩ ኃይል አባላቱ መንግሥት እና ሕዝብ የሰጧቸውን ኀላፊነት በላቀ ግዳጅ ለመፈጸም በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን እና ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከባዕከር
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
