
ጥር 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው ኢራንቡቲ፡፡ በዓለ ጥምቀቱ 44 ታቦታት በአንድ ላይ ተሰባስበው ነው የሚከበረው፡፡
በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በኢራንቡቲ ቀበሌ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በ14ኛው መቶ ከፍለ ዘመን በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት/1394 ዓ.ም አካባቢ ጀምሮ/ በየዓመቱ ከጥር 10 እስከ 12 ለ3 ቀናት ሲከበር ቆይቷል።
ላለፉት 620 ዓመታት የጥምቀት በዓል በደማቅ ሥነ ሥርዓት ሲከበር ኖሯል፤ እየተከበረም ይገኛል፡፡ በዚህ ወቅት 44 ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባህሩ በማቅናት ጥምቀትን ልዩ ገፅታ ያጎናፅፉታል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምረው በዚህ ቦታ ሲያከብሩ የነበሩት ቀደምት አብያተ ክርስቲያናትም አሉ፤ ከነዚህም መካከል በሳ ቅዱስ ሚካኤል፣ ራራቲ ቅድስተ ማርያም፣ ቀርሾ አጥር ቅዱስ እግዚአብሔር ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡
በዚህ ቦታ በዓሉ እንዲከበር የኾነበት ዋናው ምክንያትም ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ማምራቱን በማሰብ ተፈጥሮአዊ ወንዝ ፍለጋ እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ይናገራሉ፡፡
በአቅራቢው ያለው የሸንኮራ ወንዝ በአምሳለ ዮርዳኖስ የተፈጠረ ነውና ታቦታቱ ወደዛዉ ያመራሉ፡፡
ቦታው በይበልጥ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት የጥምቀት በዓል በደመቀ ሁኔታ ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱና ዋነኛው ቦታ እየኾነ መምጣቱም ተገልጿል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ 44 ታቦታት በዚህ ቦታ በአንድ ላይ ሆነው ሲያከብሩ 620 ዓመትን አስቆጥሯል፡፡
የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል በደማቅ ሥነ ሥርዓት ለማክበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ከወረዳዉ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የተገኘዉ መረጃ እንደሚጠቁመዉ በምንጃር ኢራንቡቲ ጥምቀትን ማክበር በብዙ መንገድ ለየት ይላል፡፡
1. ወንዙ አምሳለ ዮርዳኖስ መሆኑ፡-ከላይ መነሻው አንድ ኾኖ መሐል ላይ ለሁለት ተከፍሎ ዝቅ ብሎ መገናኘቱ አምሣለ ዮርዳኖስ አሰኝቶታል፡፡
2. ውኃው ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ መፍሰሱና ከመነሻው ጀምሮ የ44ቱም ታቦታት ጸበል መኖሩ
3. ወንዙ ተፈጥሯአዊ መሆኑ
4. 44 ታቦታት በአንድ ላይ ማደራቸው የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ጽላት አብሮ በጥምቀተ ባህር ማደሩ
ለ620ኛ ዓመት በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ ❝ዳግማዊ ዮርዳኖስ❞ የሚከበረው በዓለ ጥምቀት በተለየ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥነ ሥርዓት በደመቀ መልኩ ይከበራል፡፡
ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ። https://ameco.bankofabyssinia.com/
