በበርሃዋ ገነት የደመቁት እነሞት አይፈሬ!

224

ሑመራ፡ ጥር 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሞት ለሰው ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠ ጸጋ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ስለሀገር መሞት ግን ለእነርሱ ከተራ ሞት የተለየ ትርጉም አለው፡፡ ተደፍሮ፣ ተዋርዶ እና ነፃነትን አጥቶ ከመኖር በጀግንነት መሞትን ያለአማራጭ ይመርጡታል፡፡
ደግሞም ጠላቶቻቸውን ከራሳቸው በላይ አብጠርጥረው ያውቋቸዋል፡፡ በጦርነት ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ በፕሮፖጋንዳ የተጠመዱ ስለመሆናቸውም ይገነዘባሉ፡፡
ጀግኖቹ ላለፉት ስድስት ወራት “ዱር ቤቴ” ብለው ድንጋይ ተንተርሰው እና አሸዋ ለብሰው ስለልጆቿቸው ነፃነት እና ስለሀገራቸው ክብር ከደላ ሕይዎታቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ቆይተዋል፡፡
የአካባቢው ሙቀት ራሱን ችሎ ፈታኝ ጦርነት ነው፡፡ ቦታው የምስራቅ አፍሪካ ኮሪደር እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ስትራቴጂክ የጦር ቀጠና፣ አስቸጋሪ መልካ ምድር እና ለውስጥ መሰሪዎች እና ለውጭ ጎርጓሪዎች ምቹ በመሆኑ የላቀ ትጋትን ይጠይቃል፡፡

ኢትዮጵያ በሕልውና ዘመቻው ያጋጠማት መራር ወረራ ምንጩም ሆነ የስበት ማዕከሉ ይህ አካባቢ ነበር፡፡ ትኩረት ለመሳብ እና አቅጣጫ ለማስቀየር ከወሎ እስከ ሽዋ፣ ከሚሌ እስከ ከሚሴ፣ ከጭና እስከ ነፋስ መውጫ፣ ከአጣየ እስከ ሸዋ ሮቢት የተቅበዘበዙት ወራሪዎቹ ዓላማቸው እና ፍላጎታቸው የሁመራን ኮሪደር መቆጣጠር እንደነበር ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አልነበረም፤ አልቻሉም እንጂ፡፡
ጠላቶቻቸው ከውስጥም ከውጭም የመምጫ ቀዳዳቸው ብዙ ነው፡፡ አካባቢው ለዘመናት መራር ትግል እና ፈታኝ ውጣ ውረድ ታልፎበታል፡፡ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ መዘውር ከዚህ አካባቢ የተቆራኘ ነውና ተመልካቹ ብዙ ነው፡፡ ከዚህ አካባቢ እንዲወሳ የማይፈለግ ማንነት፣ እንዲነገር የማይፈለግ ቋንቋ እና እንዳይሰፋ የሚፈለግ አመለካከት ነበር፡፡ ዛሬ ያ ለዘመናት የተፈራው የአማራ ማንነት ገዢ እሳቤ እና መታገያ መስመር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
ሃምሳ አለቃ ላቀ ጥላሁን ከሚወደው እና ግማሽ እድሜ ዘመኑን ካሳለፈበት የውትድርና ሙያ የነጠለው አማራ መሆኑ ነበር፡፡ በግፍ ከተባረረበት ሙያ የነጠለውን እና ለዘመናት ዋጋ የከፈለበትን ማንነቱን ደግሞ አብዝቶ ይፈልገዋል፡፡

ሰሜን እዝ ግፍ ሲሰራበት እትብቱ በተቀበረበት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አካባቢ ውስጥ ነበር፡፡ የሚወዳቸው ጓደኞቹ እና የትግል አጋሮቹ አሳፋሪ ክህደት ሲፈጸምባቸው ሰምቶ አዝኗል፡፡ ነገር ግን የተፈጠረውን አጋጣሚ በዋዛ ማሳለፍ አልፈለገምና የሽብር ቡድኑ በወረራ ከያዘው አካባቢ እንዲወጣ በርቱ ተጋድሎ አድርጓል፡፡
የሽብር ቡድኑ አካባቢውን ከለቀቀ በኋላ መልሶ ለመምጣት የማይፈነቅለው ድንጋይ እንዳልነበረ እናውቃለን የሚለው ሃምሳ አለቃ ላቀ በሕይዎት እያለን ግን የማይታሰብ ቅዥት ነው ይላል፡፡ ላለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች ያደረገው ወረራ ትኩረቱ የሁመራን ኮሪደር መልሶ መቆጣጠር ቢሆንም ያ እሳቤ ግን የሚሳካ አይደለም ይላል፡፡ እንኳን ቆመን በሕይዎት ሞተን እንኳን አጥንታችን የሽብር ቡድኑን ይቅር አይልም የሚለው ሃምሳ አለቃ ላቀ በየጊዜው የሚሰጠውን ግዳጅ እና ተልዕኮ በላቀ ብቃት ለመፈጸም ዝግጁ ነን ብሎናል፡፡

የአካባቢው የሰላም አሰከባሪ ኅይል ሻለቃ መሪ የሆኑት ነጋሽ ዘለቀ ትህነጎችን ከራሳቸው ከትህነጎች በላይ እንደሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ መክዳት እና ከኋላ መውጋትን ትህነጎች ተክነውበታል የሚሉት ሻለቃ መሪው ፕሮፖጋንዳ ጥርሳቸውን የነቀሉበት ነውና ለመዘናጋት ቀርቶ ለመስማት እንኳን ምን ሲደረግ እድል እንሰጣቸዋለን ነው የሚሉት፡፡
የሽብር ቡድኑ ከደርዘን በላይ ትንኮሳ አድርጎ ነበር የሚሉት ሻለቃ መሪው ነጋሽ ዘለቀ ከመጡት መካከል የተመለሱ ስለመኖራቸው ግን መጠራጠር አይከፋ ባይ ናቸው፡፡ ወልቃይት የሕልውና ዘመቻው ማደማደሚያ እና የናፋቂዎች መቀበሪያ እስክትሆን ድረስም አንዘናጋም ብለዋል፡፡
ላለፉት ስድስት ወራት የበርሃዋ ገነት እና አካባቢው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ይኖረው ዘንድ ዘብ የቆሙት እና ራሳቸውን ስለሚወዱት ማንነታቸው አሳልፈው የሰጡት እነሞት አይፈሬ በበርሃዋ ገነት ሁመራ ከተማ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ደጀኑ ሕዝብ ከጎናቸው እና መንግሥት አብሯቸው እንደሆነ ተነግሯቸው ለቀጣይ ተልእኮ በሚያበቃ መልኩ ተመስግነዋል፡፡
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበኩር ጋዜጣ ጥር 02/2014 ዓ.ም ዕትም
Next article“የጥምቀት በዓልን ስናከብር በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱትን በመደገፍ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን በማቋቋምና ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት በመገንባት ሊሆን ይገባል”ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል