
ጎንደር፡ ጥር 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ለሀገር ሕልውናና ለሕዝብ ነጻነት የተጋደሉና ጀብድ የሠሩ ፋኖዎችን የበለጠ ያደራጃል እንጂ ትጥቅ አያስፈታም ሲሉ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ተናገሩ፡፡
አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንደገለጹት፤ በአማራ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የአማራን ሕዝብ ከጠላት የሚከላከል፣ ከውርደት የሚታደጉና በልማትና በፖለቲካው መስክ ተጠቃሚ እንዲሆን ዋጋ የሚከፍሉ ሁሉ ፋኖዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለሀገር ሕልውናና ለሕዝብ ነጻነት የተጋደሉና ጀብድ የሠሩ ፋኖዎችን የበለጠ ያደራጃል እንጂ ትጥቅ አያስፈታም ብለዋል፡፡
የአሸባሪው ሕወሓት ቡድንን ወረራ ለመቀልበስ ፋኖዎች ትልቅ ጀብድ ፈጽመዋል፤ የሕይወት መስዋዕትነትም ከፍለዋል ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ መንግሥት ለእነዚህ ሰዎች እውቅና ሰጥቶ ይሸልማል እንጂ ትጥቅ የሚያስፈታበት ምክንያት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ሃሳብ ለሀገሩ ሲዋደቅ ጉዳት የደረሰበትን ፋኖ ለሌሎች ኃይሎች በሚደረገው አግባብ እንዲታገዝ ፣ ለሀገር ክብር ለተሰዋውም ለሌላው እንደተደረገው ማድረግ እንጂ ትጥቅ እንዲያወርዱ ማድረግ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡
ፋኖ የታጠቀ ኃይል በመሆኑ በክልሉ ላይ አደጋ በተቃጣ ጊዜ እንደማንኛውም ሰው በራሱ አደረጃጀት መሰረት ከሌላው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ጋር ተቀናጅቶ ጠላትን እንደሚመክት አመልክተው፤ በሰላም ጊዜ ደግሞ አርሶ አደር የሆነው አርሶ አደር፣ ነጋዴውም ንግድ ሥራ ላይ የሚሰማራበት እና ወደመደበኛ ሥራው ተመልሶ ሥራውን የሚከውን ኃይል ነው፡፡ በሰላም ጊዜ አብዛኛው ፋኖ ሥራ ላይ ያለ ነው፤ ሥራ የሌለው ካለ ደግሞ መንግሥት ይህንን ኃይል ጠጋ አድርጎ ወደሥራ እንዲገባ የሚያደርግበት ሁኔታ እንደሚኖር አስረድተዋል፡፡
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ ፋኖ ሥርዓት የሚያከብርና ለአማራ ሕዝብ ጥቅም ራሱን መስዋዕት የሚያደርግ ነው፡፡ ሥርዓት አልበኛ የሆነ፣ ለመዝረፍ ለመስረቅና ሌላ ብጥብጥ ለማንሳት የሚንቀሳቀስ ኃይል ካለ ፋኖን የሚወክል ስላልሆነ የክልሉ መንግሥት በሕጉ መሰረት ሥርዓት እንደሚያስከብር ገልጸዋል፡፡
ፋኖ ከመንግሥት አቅም በላይ የሆነ ኃይል ሳይሆን ከመንግሥት ሥር ሆኖ እንደሌላው ማኅበረሰብ የሚዳኝ ነው ያሉት አቶ ግዛቸው፤ ከዚህ ያፈነገጠና ሌላ ፍላጎት ያለው አካል ካለ በፋኖ ስም መጠራት የለበትም ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከፖለቲካ አመራሩ ጀምሮ ትጥቅ እንዴት ነው የሚያዘው ፣ በትጥቁ የሆነ ነገር ቢፈጽም ምን ይሆናል የሚሉና መሰል ጉዳዮች ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲመራ ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህ ግን ትጥቅ ከማውረድ ጋር የሚገናኝ ሳይሆን የትጥቅ አስተዳደሩ በሂደት ታይቶ በሥርዓት መመራት አለበት ከሚል እሳቤ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ፖለቲካዊ ፍላጎትን አንግበው ማሕበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ምንጫቸው ያልታወቁ ውዥንብሮችን በመንዛት እርስ በርስ እንድንከፋፈልና እንድንጠላላ፤ በተለይም የአማራ ሕዝብ ደግሞ እንዳይጠናከር የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፤ ሕዝቡ ለእነዚህ ኀይሎች ጆሮ ሳይሰጥ መረጃን ከትክክለኛው ምንጭ ብቻ መውሰድ እንዳለበትም መግለጻቸውን የዘገበው ኢፕድ ነው፡፡
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
