“ምርጫን የሚያሸንፈው በሀሳብ የተደራጀ የሕዝብ ይሁንታ ነው፡፡” በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር

185

“ፓርቲዎች የሚያሸንፉት በሚያነሱት ሀሳብ ብቻ ሳይሆን በዜጎች ይሁንታ መሆኑን ማመንና የስነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ አለባቸው፡፡” ኢዜማ

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ ትናንት ለሁለቱ ምክር ቤቶች ካቀረቧቸው የ2012 በጀት ዓመት ዕቅዶች መካከል የምርጫ ጉዳይ አንዱ ነበር፡፡ በያዝነው ዓመት የሚካሄደው ምርጫ ሦስት እሴቶችን መሠረት ያደረገ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ ባለፉት ጊዜያት ያጋጠሙ ግድፈቶችን በሚያርም መልኩ እንዲከናወን፤ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ተዓማኒ እና ተቀባይነት ያለው፣ የፖለቲካ ልሂቃንን እና የምልዓተ ሕዝቡን ተሳታፊነትም ያረጋገጠ እንዲሆን በመንግስት በኩል መታመኑን አቅርበዋል፡፡

ለመሆኑ በመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ይጠበቃል?፤ ምን ጉድለቶችንስ እንዲያስተካክሉ ይመከራል? አብመድ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና ፖለቲከኞችን አነጋግሯል፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ዘላለም እሸቴ የዘንድሮው ምርጫ ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ ካስተናገደቻቸው የምርጫ ወቅቶች በበለጠ ሰላም እና ደኅንነት ባልተረጋገጠበት ሀገር ላይ የሚካሂድ ነው ብለዋል፡፡ መምህሩ ‹‹ፕሬዝዳንቷ ያቀረቧቸውን ትልሞች ለማሳካት ቢያንስ ቅድሚያ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሁሉም አከባቢዎች ሄደው የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ይችላሉ ወይ? የሚለው ነባራዊ ሁኔታ መመለስ አለበት›› ብለዋል፡፡ ምርጫን የሚያሸንፈው በሀሳብ የተደራጀ የሕዝብ ይሁንታ እንደሆነና ለይሁንታው የሚመጥን ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ መገኘት ደግሞ የሰለጠነ አካሄድ መሆኑን ነው መምህሩ የተናገሩት፡፡

ፓርቲዎች ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ ለምርጫ ራሳቸውን ዝግጁ ያደረጉ ተፎካካሪዎች መሆን  እንዳለባቸው ቢታመንም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ግን በሀሳብ እና በአደረጃጀት ያልተደራጁ፣ ሕዝብን በጋራ የሚጠቅም ፖሊሲ ስለመያዛቸውም የማያስተማምኑ ናቸው ብለዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ለምርጫ ዝግጅት ‹ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ› አካሂድ የሚከተሉ በመሆናቸው ከዚህ መንገድ በመውጣት ሀገርን ወደ ፊት በሚያራምዱ ሀሳቦች ላይ ማተኮርና ስለምርጫ የሕዝብን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም ነው መከሩት፡፡

መጪው የምርጫ ዘመን ስኬታማ እንዲሆን ሕዝቡ የጋለ ብሔርተኝነትን መግታት፣ መረጃዎችን በሰከነ መንገድ ማጣራት፤ መገናኛ ብዙኃንም የሀሳብ የበላይነት እንዲሰለጥን ከአሁኑ መሥራት አለባቸው ብለዋል መምህር ዘላለም፡፡

ሁሉም ፖለቲከኛ መሆን አይችልም ያሉት የሕግ መምህሩ በእኛ ሀገር ውስጥ የሚታየው ግን ሁሉም የፖለቲካ ተንታኝ ሲሆን በመሆኑ ይህ ደግሞ ከዕውቀት እና ከዕውነት ይልቅ  መላምቶች  እንዲሰለጥኑ እና  አብሮነት  ችግር ውስጥ እንዲገባ ያደርጋሉ ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ የመፍትሔ ሀሳቦች እንጂ ለሕዝቡ የስጋት እና የመለያየት መንስኤዎች፣ የሴራ ፖለቲካ  ማራመጃዎች መሆን እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ሀገርን የመምራትና የማስቀጠል መሠረቱ የሀሳብ የበላይነት እንዲሆን መሥራት እንደሚገባም አስምረውበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየወቅቱ በሚፈጠሩ አጋጣሚዎች ከሕዝብ ልብ ለመግባት ጥረት ከማድረግ ይልቅ ዘላቂ ዕቅዶችን በማምጣት የጋራ ተጠቃሚነትን ባሕል እንዲያደርጉም ከትዝብታቸው በመነሳት መክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ የሙያ ማኅበራት ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አቶ ወንድወሠን ተሾመ መጪው ምርጫ ነፃ፣ ተዓማኒ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ የሕዝብ እና የፖለቲካ ልሂቃን ተሳትፎ የተረጋገጠበት እንዲሆን የዴሞክራሲ ተቋማትን አሠራር ማሻሻል ያሰፈልጋል ብለዋል፡፡

ፓርቲዎች የሚያሸንፉት በሚያነሱት ሀሳብ ብቻ ሳይሆን በዜጎች ይሁንታ መሆኑን ማመንና የስነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ ተገቢ እንደሆነም ነው አቶ ወንድወሠን የተናገሩት፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት ‹ለፍች የተመቸ ጋብቻ› መስሎ መቅረብ የሕዝብን ጥያቄ የሚመልስ ባለመሆኑ የፖለቲካ ዝና እና የግል ጥቅምን በመግታት የሕዝብ ጥቅምን ማስቀደም እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡ በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል መደማመጥ አለመኖሩ እንደሚያሳዝናቸው የተናገሩት አቶ ወንድወሠን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (በፓርላማው) ውስጥ የተለያዩ ሀሳቦች እንዲራመዱ ለማስቻል ሁሉም ተፎካካሪዎች ሠላማዊ እንቅስቃሴ ማድረግን ብቸኛ አማራጭ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከንድፈ ሀሳባዊ እንቅስቃሴ ወጥተው የቅድመ ምርጫ ሥራው እንዲጀመር ማድረግ፣ የምርጫ ማሸነፊያ ፖሊሲያቸውንም ከኢትዮጵያዊ እሴቶች እና ከአንድነት ጋር  ማስተሳሰር ተገቢ ነው ብለው እንደሚምኑ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

 

 

Previous article‹‹በሕገ-ወጥ ደላሎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል፡፡›› ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
Next articleተጠርጣሪው ለከፈተው ተኩስ በተወሰደ አጸፋ ህይወቱ ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡