ኑና በጎንደር አንድ ላይ ሆነን ቃል እንሰር!

221

ጎንደር፡ ጥር 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) መጪው በዓል ጥምቀት ነውና ጎንደር ገብተናል፡፡ ጥምቀት እና ጎንደር ልዕልት እና ደንገጡር ናቸው፡፡ ጥምቀት በጎንደር በልዩነት ይከበራል፤ ጎንደርም በጥምቀት አጀቧ ብዙ ነው፡፡ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” ይሉ ሀገርኛ አባባል ጎንደርም ለጥምቀት የአዘቦቷን እና የክቷን አውጥታ ትደምቅበታለች፡፡

“እናታለም ጎንደር” እያሉ የሚያቆላምጧት ኢትዮጵያውያን ጥምቀትን በጎንደር ለመታደም የዘውትር ምኞታቸው ነው፡፡ ጎንደርም በጥምቀት 44ቱን ታቦታት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንንም ከአራቱም አቅጣጫ ታሰባስባለች፡፡ በዚህ መልክ መሰባሰብ በጎንደር እጅጉን ይደምቃል፤ ጎንደርም ማሰባሰቡን ተክናበታለች፡፡ የዘንድሮው መሰባሰብ ግን በስሜቱም ሆነ በዓይነቱ ይለያል፡፡ የካሳ ሹርባ ጎንድር ገብቷልና፡፡

እውቁ ፈረንሳያዊ የታሪክ ጸሐፊ ኳንተን ዱለም ጎንደርን እንዲህ ሲል ይገልጻታል “ኢትዮጵያዊ ሆኖ ጎንደርን፤ ፈረንሳያዊ ሆኖ ፓሪስን ያላየ የተሟላ ስብዕና አለው ለማለት ይከብዳል፡፡” ወደ ጎንደር ለመሄድ የቆረጠ ተጓዥ ከአካሉ ቀድሞ ጎንደር የሚገባው ልቡ ነው፡፡ ጎንደር ለመታሰብም ለመሰባሰብም ቅርብ የሆነች ጥንታዊ ከተማ ናት፡፡ እድሜ ጠገቧ ጎንደር ለሚያውቋት ቀርቶ በምናባቸው ለሚያስቧት ልጆቿ እንኳን የልብ ከተማ ነች፡፡

አያሌ ዘመንን ያሳለፉት ኪነ ሕንጻዎቿ፣ የወርቃማ ዘመኗ ንግሥና እና መንፈስን የሚያድሱት የጥበብ ሥራዎቿ ጎንደር ለማያውቋት ሳይቀር ባይተዋር አታደርግም፡፡ ጎንደር ከተማ ብቻ ሳትሆን የጥበብ አውድማ፣ የሀገር በቀል ፍልስፍና መዲና፣ የሥርወ መንግሥት አድባር እና የቱባ ባሕል ሙዚየም ነች፡፡

ጎንደር የምትታወቅ ብቻ ሳትሆን የምትታወስም ከተማ ነች፡፡ ጎንደር ረዥም እና ገናና ታሪክ አላቸው ከሚባሉት ጥቂት የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አንዷ ናት፡፡ ታሪካዊ ኪነ ሕንጻዎቿ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ እና ገናና ሥርወ መንግሥት በየዘመኑ ለሚመጣ ትውልድ ህያው ምስክሮች ሆነው ያወሳሉ፡፡

ጎንደር ለ300 ዓመታት የጥንታዊት ኢትዮጵያ መዲናነቷን የሚያሳብቁት አሻራዎቿ ዛሬም ዘመን ተሻጋሪ እንደሆኑ ከዚህ ትውልድ እቅፍ ውስጥ ደርሰዋል፡፡ በየዘመናቱ የኢትዮጵያ የስበት ማዕከል የሆነችው ጎንደር ልጆቿ ያልፋሉ እንጂ እሷ ግን ለዘላለም አታልፍም፡፡ የነገ ተስፋዋም ስለሀገራቸው ስስት በማያውቁት ልጆቿ ፈርጣማ ክንድ ላይ የጸና ነውና ስጋትም ሆነ ፍርሃት የለባትም፡፡
ጥንታውያኑ ኢትዮጵያውያን ቄስ እና መሐንዲስ፣ ኡስታዝ እና አበጋዝ፣ ወታደር እና አርሶ አደር፣ መምሕር እና ደቀ መዝሙር፣ ዳኛ እና ፍርደኛ፣ አንጥረኛ እና ጥበበኛ፣ ሸማኔ እና ምስለኔ ሆነው የገነቧትን እና አምሳለ ኢትዮጵያ ሆና የቆመችውን ጎንደር ለመጎብኘት ከአሁን የተሻለ ቀን፤ ከጥምቀት የተሻለ ምክንያት አይኖርም፡፡

በታሪኳ ፈተና እና ፈታኝ ነጥፎባት የማታውቀው ኢትዮጵያ በዚህ የፈተናዋ ወቅት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ልጆቿን እንዲመጡ ጥሪ ስታቀርብ በርካቶች በጎ ምላሽ ሰጥተዋት ገብተዋል፡፡ በቆይታቸውም ከሚጎበኟቸው አካባቢዎች ጎንደር አንዷ ነች፡፡ ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር በርካታ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጎንደር እየገቡ ነው፡፡
ከ150 ዓመታት በላይ በሀገረ እንግሊዝ በግዞት የኖረው የዚያ ጀግና ሹርባም ጎንደር ከደረሰ ቀናቶች አልፈዋል፡፡ “አምጡ ቆርጣችሁ ከሹሩባው ላይ፤ ኪዳን እንሰር እንዳንለያይ፡፡” እንዳለ ከያኒው ጥምቀትን በጎንደር እያሳለፋችሁ ከዚያ የአንድነት ሹርባ ጋር ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ኪዳን የምታስሩበት ቀን በእውነትም ዛሬ ነው፡፡

በዚህ ዓመት ጥምቀት 44ቱን ታቦታት በአንድ ቦታ አይታችሁ፣ የንጉሳችሁን ቁንዳላ ሸኝታችሁ እና የሀገራችሁን የአንድነት ቃል ኪዳን አድሳችሁ ለመመለስ “ኑና በጎንደር አንድ ላይ ሆነን ቃል እንሰር!” ተብላችኋል፡፡ መቼም የዓለም ነገር አይሞላምና ከውስጥም ከውጭም ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ካልቻላችሁ ግን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጥምቀትን በጎንደር በሁሉም ሚዲየሞቹ እየተከታተለ ያስቃኛችኋልና አብራችሁን ሁኑ ብለናል፡፡

በታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተላለፈ መልዕክት
Next article“የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ተስማምተው የኅብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።” የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)