
ጥር 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያናት በጦርነት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ያሰባሰቡትን 15 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ድጋፍ ለክፍለ ከተማው አስተዳደር አስረከቡ፡፡
በክፍለ ከተማው የሚገኙ ሰባት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናት ከምዕመናን ያሰባሰቡትን 15 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው የተለያዩ ቁሳቁስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ እና ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጸዴቅ ለቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው አስረክበዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጸዴቅ በርክክቡ ላይ ባደረጉት ንግግር የቦሌ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያናት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ባደረጉት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ ሀገረስብከት በሞዴልነት የሚወሰዱ መሆናቸውን አውስተዋል። ለወገን ደራሽ ለመሆን የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ምስጋና እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
ድጋፉ ወደፊትም እንደሚቀጥል የገለጹት ብጹዕነታቸው፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደርም በድጋፍ ማሰባሰብ እንቅስቃሴው ላይ ላደረገው መልካም ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው በበኩላቸው የቦሌ ክፍለ ከተማ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናት በኅልውና ዘመቻው ወቅት ከፍተኛ ድጋፍ ማበርከታቸውን ተናግረዋል። የእምነት ተቋማት ለሀገር ሰላም ከመጸለይ ጎን ለጎን የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍ ምዕመናኑን አስተባብረው የሚያደርጉት ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን በመግለጽ ለተደረገው ድጋፍ በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የክፍለ ከተማው ቤተክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችም ለቀረበው ሀገራዊ የድጋፍ ጥሪ ምላሽ በመስጠታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። ወደፊትም አቅማቸው የፈቀደውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/