
ባሕር ዳር፡ ጥር 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከልዩ ልዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የዳያስፖራ አባላት በባሕር ዳር ከተማ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል፡፡ የጉብኝቱ ዓላማ የዳያስፖራ አባላቱ በዘርፉ ሙሉ ግንዛቤ ኖሯቸው በከተማዋ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጥሩ ማስቻል ነው፡፡ በተለይ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ዓይተው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈስሱ ፍላጎት መኖሩን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ንጉሤ ተናግረዋል፡፡
እንደ ክልል በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፉ በርካታ ውድመት መድረሱን ያነሱት መምሪያ ኀላፊዋ ዘርፉ ከደረሰበት ኪሳራ እንዲያንሰራራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ለዚህም ዳያስፖራው በከተማ አስተዳደሩ የሚሰማራባቸው ልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር በመግለጽም ሀብትና እውቀታቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የሰጡ የዲያስፖራ አባላት ተስፋ ሰጪ ጉብኝት ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡ ከአትላንታ ጆርጂያ የመጡት አቶ ማንችሎት ገበየሁ ዳያስፖራው ያጠራቀመውን ሃብት ጥቅም ላይ እንዲያውል የሚያነሳሳ ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥትም አጋጣሚውን ሊጠቀምበት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
ሀገራት የበለጸጉት በሥራ መሆኑን በማንሳትም ባሉት አማራጮች ለመሳተፍ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡ ዳያስፖራው ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ትልቅ ነገር መሥራት ይቻላል ያሉት ደግሞ ከቨርጂኒያ የመጡት ጌታማር ተስፋዬ ናቸው፡፡ ለዚህም ያለውን ጸጋ በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡ መንግሥትም ጥሪ ከማድረግ ባለፈ የመጣውን ዳያስፖራ በአግባቡ መጠቀም እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል፡፡ ለዚህም የቢሮክራሲ ውጣ ውረዶችን ማስተካከል፣ ፈጣን አገልግሎት መስጠት፣ በአንዳንድ ተቋማት የሚስተዋለውን የአመለካከት ችግር መቅረፍ እና የንግድ አሠራርን ማዘመን ይገባል ብለዋል፡፡ መነቃቃትን የሚፈጥር ጉብኝት ማድረጋቸውን በማንሳትም ወደ ልማት የመግባት ፍላጎት እንዳላቸውም አንስተዋል፡፡
ሌላው ከቨርጂኒያ የመጡት አቶ ፍቅርማርያም በሀገራችን መዋዕለ ነዋይ እያፈሰስን እንለወጣለን ብለዋል፡፡ በኢኮኖሚ መፈርጠም ከተቻለ የሚገጥሙ ፈተናዎችን ሁሉ በቀላሉ መጋፈጥ ይቻላል ብለዋል፡፡ ኢኮኖሚን መገንባት የመንግሥት ሥራ ብቻ አይሆንም እና ዳያስፖራው በሀገሩ ኢንቨስት እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ መንግሥትም ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡ በጉብኝቱ ከከተማ አስተዳደሩ የተውጣጡ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m