‹‹በሕገ-ወጥ ደላሎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል፡፡›› ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

257

ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2012 ዓ/ም (አብመድ) በሕገ ወጥ ደላሎች ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ ትልልቅ ከተሞች በአገልግሎትና በመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ የተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ንረት በአቅርቦት ችግር ሳይሆን የሕገ ወጥ ደላሎች ጣላቃ ግብነት መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የዋጋ ንረቱ በተለይም በዝቅተኛ ነዋሪው ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ከማሳደሩም ባሻገር ጥቂቶች አላስፈላጊ ንዋይ በመሰብሰብ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲፈጠር አድርጓል›› ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሕገ-ወጥ ደላሎች አማካኝነት አየር በአየር በመኪና ላይ ሕገ ወጥ ግብይት ሲያካሂዱ የተገኙ 59 መኪኖች አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም 52 መኪኖች ጤፍና ሌሎች እህሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ‹‹ይህ የቁጥጥርና እርምጃ የመውሰድ ሥራ በሁሉም የሀገሪቷ ክልሎች ተጠናክሮ ይቀጥላል›› ብለዋል፡፡

የኢ.ፕ.ድ ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ እንዳሚያመለክተው ደላሎችን ከሰንሰለት ውጪ በማድረግና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራቾችና ተጠቃሚዎች በቀጥታ የሚገናኙበትን አግባብ ለመፍጠር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የረጅም ጊዜ እቅድ አቅዶ እየሠራ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

Previous article‹‹ሀገራዊ ምርጫና የምርጫ ባለድርሻ አካላት ሚና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ›› በሚል ርዕስ አዲስ አበባ ላይ ምክክር እየተካሄደ ነው፡፡
Next article“ምርጫን የሚያሸንፈው በሀሳብ የተደራጀ የሕዝብ ይሁንታ ነው፡፡” በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር